Tuesday, September 1, 2015

የሚጠጣ መጽሃፍ ታተመ፡፡



አዎ ወዳጄ… እርግጥ ነው መጽሃፍ ይነበባል እንጂ አይጠጣም፡፡ እንደው አንዳንድ ጊዜ አንድን መጽሃፍ ምንም ሳላስቀር በደንብ አንብቤዋለሁ ለማለት “መጽሀፉን ጥጥት አድርጌዋለሁ!” የሚል ብሂል ብንጠቀምም መጽሃፍ እንደማይጠጣ ሀቅ ነው፡፡ ነገር ግን ዶክተር ትሬሳ ዳንኮቪች ለአመታት ደክመውበት የጻፉት መጽሀፋ “በደንብ አንበብቤዋለሁ” ለማለት ሳይሆን በእርግጥም የሚጠጣ መጽሃፍ ነው፡፡
በአለማችን ላይ በሚሊየኖች የሚቆጠርን ህይወት ከሞት ይታደጋል የተባለው ይህንን የሚጠጣ መጽሀፍ ካናዳ በሚገኘው ማክጊል ዩኒቨርሲቲና በአሜሪካ ቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ ለበርካታ አመታት የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግና በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በመሞከር ውጤታማነቱን አረጋግጠው ነው ዶክተር ትሬሳ ዳንኮቪች በስተመጨረሻ ያሳተሙት፡፡ እርስዎ ወዳጄ ነገሩ ግራ ግብት ቢልዎት “ቆይ ለመሆኑ እንዴት ተደርጎ ነው መጽሀፉ የሚጠጣው?” የሚል ጥያቄ ማንሳትዎት አይቀርምና ምላሹን ዋቢ ካደረግኩት ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽን እነሆ ብያለሁ፡፡
ዶክተር ትሬሳ የጻፉትና ያሳተሙት መጽሃፍ ገጾቹ እንደማንኛውም መጽሃፍ የወረቀት ገጾች ብቻ ሳይሆኑ አንዱን ገጽ አንስተው ውሃ ውስጥ ሲጨምሩት በውሃ ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎችን 99 በመቶ በመግደል የማከም ስራን ይሰራል፡፡ በሌላ አነጋገር ውሃን አክሞ ለመጠጣት እንደሚያስችሉ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች፤ የዚህ መጽሃፍ ገጾችም ልክ በዚያ መልኩ ውሃን የማከም ብቃት እንዲኖራቸው ተደርገው ነው የተሰሩት፡፡
“የሚጠጣውን መጽሃፍ ለመጠቀም በጣም ቀላል ነው” የሚሉት ዶክተር ትሬሳ “ከመጽሃፉ ላይ አንድ ገጽ አንስተው ገጹን እንደ ማጥለያ በመጠቀም ከወንዝም ይሁን ከኩሬ ብቻ ያገኙትን ውሃ ወደሚፈልጉት እቃ ላይ ያንቆርቁሩት በገጹ ላይ ያለፈው ውሃ ኩልል ጥርት ያለ ምንም አይነት የጤና ስጋት የማይፈጥር ሆኖ ያገኙታል” ሲሉ ስለሚጠጣው መጽሃፋቸው አጠቃቀም አስረድተዋል፡፡
እርግጥ የዶክተር ትሬሳ ውሃን የማከም ፈጠራ ሙሉ በሙሉ አዲስ ነው ባይባልም፤ ነገር ግን በመሰል መልኩ በመጽሃፍ ገጾች አማካኝነት ውሃን የማከም ፈጠራ ከዚህ ቀደም በማንም አልተሞከረም፡፡ የዶክተሯ የሚጠጣ መጽሃፍ በተደረገለት የላብራቶሪ ሙከራም አንዱ ገጽ ብቻ እስከ 100 ሊትር ውሃ ድረስ የማከም ብቃት አለው፡፡ አንድ መጽሃፍ ቢገዙ ታዲያ ለአራት አመት ካለምንም ስጋት በተጣራው ውሃ ጉሮሮዎትን እያራሱ መዝለቅ ይችላሉ ማለት ነው፡፡
በአለማችን ላይ 663 ሚሊየን ህዝቦች ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንደማያገኙ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን  ይህን ችግር ለማቃለል የዶክተር ትሬሳ የሚጠጣ መጽሃፍ አይነተኛ መፍትሄ መሆኑም ታምኖበታል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ጋና እና ባንግላዲሽ አካባቢ ባሉ 25 ገደማ የተበከሉ ውሃ ምንጮች ላይ የሚጠጣው መጽሃፍ ሙከራ ተደርጎበትም በእርግጥም 99 በመቶ ባክቴሪያዎችን መግደል እንደሚችል ከላብራቶሪ ውጪ ተረጋግጧል፡፡ 
የሚጣጣ መጽሃፋቸውን በብዛት ለማተም ጥረት እያደረጉ የሚገኙት ዶክተር ትሬሳና ጓደኞቻቸው በቅርቡ መአት የሚጠጡ መጽሃፍ ቅጂዎችን ለበርካቶች እንደሚያዳርሱ ነው የተናገሩት፡፡ የመጽሃፉን ዲዛይንም ለማስተካከል ከባለሙያዎች ጋር እየሰሩ ሲሆን “በርካታ ዲዛይኖች አሉን” የሚሉት ዶክተሯ “እናም የሚጠጣውን መጽሃፍ አነስና ቀለል ባለ መልኩ ለማቅረብ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡ 

ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment