Tuesday, September 29, 2015

መበየጃ ማሽንን እንደ ብሩሽ፣ ብረትን እንደ ሸራ ተጠቅሞ የሚስለው ወጣት

ወዳጄ ብየዳ ያውቃሉ አይደል፤ ብረት እየተቆረጠና እየተቀጠለ የተለያዩ ነገሮች የሚሰሩበትን ሙያ! መቼም እስከዛሬ በር ሊያሰሩም ይሁን የአልጋ ብረት ሊያስበይዱ ወይ ደግሞ የሚዘውሯት መኪናም ካለችዎት እሷን ለማስጠገን ወይም በሌላ አጋጣሚ ከብየዳ ጋር ተገናኝተው እንደሚሆን እርግጥ ነው፡፡ ምናልባት የብየዳ ሙያተኛ ከሆኑ ደግሞ ያው ብየዳ ከእለት ተእለት እንቅስቃሴዎት ጋር የተገናኘ ነው ማለት ነው፡፡ እናልዎት ታዲያ የብየዳ ነገር ሲነሳ የሚታወቀው፤ ብረት የተፈለገውን ቅርጽ እንዲይዝ ተደርጎ በእሳት ሲጠበስ ነው እንጂ በብየዳ ‘ስእል’ ይሳላል ‘ቅርጻ ቅርጽ’ ይሰራል ቢባል ለማመን እንደሚያዳግት አልጠራጠርም፡፡
እናማ ወዳጄ “አንድ የብየዳ ባለሙያ ስእል ይስላል” ቢባሉ “ታዲያ ምን ችግር አለው… ሁለት ሙያ አለው ማለት ነዋ! መቼም የሚስለው በትርፍ ጊዜው ነው” ብለው ሊመልሱ ይችላሉ “ኧረ የለም እንደሱ አይደለም እዚያው እየበየደ ነው ስእል የሚስለው… ማለት መበየጃውን እንደ ብሩሽ ብረቱን እንደ ሸራ ተጠቅሞ ነው ብረት ላይ በተለያዩ ቀለማት የተዋቡ የጥበብ ስራዎችን የሚሰራው” ቢባሉ ደግሞ “ይሄማ በጭራሽ ሊሆን አይችልም!” ብለው መከራከርዎት አይቀርም ምክንያቱም አንድም ብረት ወረቀት እንዳልሆነና መበየጃ ማሽን እሳት እንጂ ቀለም እንደማይተፋ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በሌላ በኩል ደግሞ ሪቻርድ ላውትን አያውቁትምና ነው፡፡

ሪቻርድ ላውት መኖሪውን በአሜሪካ ቺካጎ ውስጥ ያደረገ የ23 አመት ወጣት ነው፡፡ ጥበብ “ሪቻርድውው…” ብላ ጮክ ብላ የጠራችው ሪቻርድ የብየዳ ማሽንና ብረትን ብቻ ተጠቅሞ ለየት ያሉ፤ በተለያዩ ቀለማት የተዋቡ ስእሎችንና ቅርጻ ቅርጾችን አስጊጦ በመስራት የተካነ ሙያተኛ ነው፡፡ በእርግጥ በስራው ኢንጂነር ቢሆንም ሪቻርድ “የለም እኔ የብየዳ ጥበበኛ ነኝ” ሲል ነው የሚናገረው፡፡ ከስራው የሚተርፈውን ጊዜ ብረት ላይ በመጠበብ የሚያሳልፈው ሪቻርድ ከብረት ውስጥ ጥበብን ፈልፍሎ ማውጣት እጅጉን እንደሚያስደስተውም ይናገራል፡፡

ሪቻርድ መበየጃ ማሽንን እንደ ብሩሽ፤ ማሽኑ የሚተፋውን እሳት እንደ ቀለም፤ ብረትን ደግሞ እንደ ሸራ ተጠቅሞ ከሚሰራቸው የጥበብ ስራዎች መካከከል የተለያዩ እንስሳት አምሳያዎችና በእለት ተእለት የህይወት ኡደት ውስጥ የምንገለገልባቸው ቁሳቁሶች የሚጠቀሱ ሲሆን በተለያዩ ፊልሞች ላይ ያሉ ታዋቂ ገጸባህርያትንም በብየዳ ጥበብ ብረት ላይ ስሏቸዋል፡፡ እንደ ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ዘገባ፡፡


ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍኤም 96.3

No comments:

Post a Comment