Tuesday, September 22, 2015

በ5 ደቂቃ ውስጥ ጸጉርን አጥቦ የሚያደርቅ የፈጠራ ማሽን


ወዳጄ ቼንግ ጎንግኬን ይተዋወቁት፡፡ መኖሪያውን በቻይናዋ ሲሹዋን ግዛት ውስጥ ያደረገ የ38 አመት ጎልማሳ ቻይናዊ ነው፡፡ የዛሬ 16 አመት ገደማ ወጣቱ ቼንግ አያቱ ታመውበት፤ እጆቻቸውን ማዘዝ ተስኗቸው ወይም ፓራላይዝ ሆነው፤ ጸጉራቸውን የመታጠብ ነገር አሳር እየሆነባቸው ሲንገላቱ መመልከቱ እንቅልፍ ይነሳዋል፡፡ “አያቴን ከዚህ ችግሯ የሚገላግላት መላ መፈለግ አለብኝ!” ሲልም ‘እችላለሁ!’ ብሎ ከተነሳ ምንም መስራት የማይሳነውን ጭንቅላት “በል መላ ፈልግ!” ሲል ወጥሮ ይይዘዋል፡፡
ሲያወጣና ሲያወርድ፤ ሲሰራና ሲሰብር 16 አመታትን ያለመታከት የአያቱን ችግር ለመፍታት የታተረው ቼንግ በስተመጨረሻ ተሳክቶለት በአምስት ደቂቃ ውስጥ አጥቦ፣ አለቅልቆና አድርቆ ጸጉርን ፏ የሚያደርግ ማሽን ለመስራት ችሏል ሲል ያስነበበው ሚረር ድረገጽ፤ ለአዲሱ የስራ ፈጠራው ቼንግ እውቅናና የባለቤትነት ምስክር ወረቀትም እንደተቸረው ነው ያሰፈረው፡፡
ጸጉር ማጠቢያ ማሽኑ ከሞተር ብስክሌት የብረት ቆብ እና ሁለት ጀሪካኖች የተዋቀረ ሲሆን መቆጣጠሪያ ሳጥንም የተገጠመለት ነው፡፡ እናም አንድ ጸጉሩን መታጠብ ለፈለገ ሰው ማሽኑ በውሀ ጸጉርን ራስ ከማድረግ ጀምሮ ፈሳሽ ሳሙና አፍስሶ በማሸት ሙልጭ አድርጎ የማጠብ ስራ ይሰራል፡፡ አጥቦ ካለቀለቀ በኋላም ሙቅ አየር ወደ ጸጉር በመልቀቅ የማድረቅ ስራም ይሰራል፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ብቻ የሚከናወን ነው፡፡ ቼንግ ይህንን ማሽን ለመስራት 18 የሞተር ብስክሌት የብረት ቆቦችን እንዳልነበሩ አድርጎ ሰባብሮ ድምጥማጣቸውን አጥፍቷል፡፡
ከ16 አመታት በፊት የአያቱን ችግር ለመፍታት ቆርጦ የተነሳው ቼንግ ምንም እንኳ የፈጠራ ስራ ውጤቱ ለመጠናቀቅ ጊዜያትን ወስዶበት አያቱ ችግራቸውን ደህና ሰንብት ብለው እንዳሸቸው ጸጉራቸውን ሲታጠቡ እየተመለከት ለመደሰት፤ አያቱ በማለፋቸው ሳቢያ፤ ባያድለውም “ማሽኑ የሌሎች በርካታ ሰዎችን ችግር እንደሚቀርፍ እምነት አለኝ” ብሏል፡፡ ማሽኑ በትክክል እንደሚሰራም ለማሳየት አባቱ እንዲታጠብበት አድርጎ ሞክሮታል፡፡
ወዳጄ ቼንግን እንዴት አገኙት ታዲያ፡፡ በዘመንኛው አነጋገር ‘እናሸንፋለን’ የሚል ስያሜ ከተሰጠውና፤ በጆግ ከባሊ ውሃ እያመላለሱ አናትዎት ላይ በማፍሰስ ከመታጠብ፤ አሊያም ደግሞ ጸጉር ቤት አዘውትሮ ከመመላለስ ገላግሎ ጸጉርዎትን በአምስት ደቂቃ ፏ አድርገው እንዲሄዱ የሚያስችል መላ ዘይዷል፡፡
ቼንግ አያቱን ከችግር ለመታደግ ቆርጦ በመነሳቱ የሰራው ማሽን ምንም እንኳ ለአያቱ ባይደርስላቸውም ለበርካቶች ችግር መፍትሄ እንደሚሆን ግን ጥርጥር የለውም፡፡ ቼንግ የአያቱ ችግር ይህን ማሽን አሰርቶታል፡፡ ወዳጄ የኛስ አያቶች በርካታ ችግሮች የሉባቸውም? ችግሮቻቸውንስ እኛ መፍታት አንችልም?... እንችላለን!!! እንሚሉኝ አልጠራጠርምና ሁላችንም ለጭንቅላታችን እንዲህ ያሉ ችግሮችን መፍቻ ዘዴዎች አፍልቅ ብለን እናስጠብበው መልእክቴ ነው፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍኤም 96.3

No comments:

Post a Comment