Tuesday, September 29, 2015

እንዲህም አድርጎ መንገድ ማቋረጥ አለ

ወዳጄ እንደው በስከዛሬው ህይወትዎ የመኪና መንገድ ሲያቋርጡ መንገዱን ተግረው ለመጨረስ በጣም ትንሽ እርምጃ ተራመዱ ቢባል ስንት እርምጃ ይሆን የፈጀብዎት? አለ አይደል እንደው የእግርዎትን አጣጣል ሰፋ ሰፋ አድርገው እመር እመር እያሉ ተራመዱ ወይም ሮጡ እንበል፤ ወይ ደግሞ ከቻሉ ተለባብጠው አክሮባት እየሰሩም ይሁን ብቻ ግን አስፓልቱን ለመሻገር ስንት እርምጃ ወይም ግልብጫ ይፈጅብዎታል? ጥያቄ ይሁንዎትና እኔ ከመኪና መንገድ አንድ ጠርዝ ተግሮ በዚያኛው ጥግ ለመቆም አንዴ ብቻ እንጣጥ ያለውን እንግሊዛዊ ላስተዋውቅዎት፡፡

ሀገረ እንግሊዝ ለንደን ውስጥ ነው ይላል ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል ድረገጽ፡፡ ኮኖር ኮንትሪክስ የተባለ ተገለባባጭ ወይም አክሮባተኛ ወጣት ነው፡፡ እና እዛ ለንደን መሀል በሚገኝ ጎዳና ላይ ከጓደኞቹ ጋር የተከሰተው ኮኖር 5 ሜትር ገደማ ስፋት ያለውን የመኪና መንገድ ለማቋረጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የዘለለው፡፡ ተንደርድሮ ከአስፓልቱ አንደኛው ጫፍ ላይ ተስፈንጥሮ የተገለበው ኮኖር በሰማይ ተንሳፎ ማረፊያውን ያደረገው ከመንገዱ በዚያኛው ጥግ ካለ የእግረኞች መንገድ ላይ ነው፡፡
ወዳጄ በእርግጥ ኮኖሮ ያለውን ድንቅ ብቃት ተጠቅሞ በአንድ ግልብጫ ብቻ እንዲህ የመኪና መንገድ ማቋረጥ መቻሉ የሚደነቅ ቢሆንም በቅድሚያ ልምምድ አድርጎ እንዲሁም ደግሞ መኪና አለመኖሩን አረጋግጦና ጥንቃቄ አድርጎ ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

እናም እርስዎ ወዳጄ የኮኖር ልዩ ችሎታ አድንቆ ከማለፍ በዘለለ አንድም የትም ቦታ ቢሆን እንዲሁ ያለልምምድ ተነስተው ልገልበጥ እንዳይሉ ምክንያቱም ከመሰበር አንስቶ እስከሞት የሚዳርግ አደጋ ያስከትላልና ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ መኪና መንገድን አይደለም እንዲህ ተገልብጦ ማቋረጥ በአግባቡ እየተራመዱም ቢሆን ጥንቃቄ ካላደረጉ አደጋው የከፋ ነውና እራስዎትን ከመኪና አደጋ ጠብቀው ለራስዎት፣ ለሚወዷቸውና ለሚወዱዎት ሁሉ በጤናና በህይወት ቆይተው ብዙ ብዙ ማድረግ እንዲችሉ በተገቢው ቦታ ተጠንቅቀው መንገድ ያቋርጡ መልእክቴ ነው፡፡

ዳንኤል ቢሠጥ

No comments:

Post a Comment