Friday, September 18, 2015

2.3 ሚሊየን ህንዳውያን ስራ ፈላጊዎች 368 ሰራተኞችን ብቻ ለመቅጠር አንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ላወጣው ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ ማመልከቻ አስገቡ



ወዳጄ መቼም ከትምህርቱ አለም ተመርቀው የወጡ ከሆነ የስራ ፍለጋን ነገር ጠንቅቀው እንደሚያውቁት እርግጠኛ ነኝ፡፡ እናም ምናልባት ይሄን የስራ ቅጥር ነገር ማስታወቂያዎችን እየተከታተሉ አመልክተው ተቀጥረው እንደሁ፤ ወይ ደግሞ አሁንም በመሞከር ላይ ከሆኑ በእስከዛሬው ልምድዎት እንደው በዛ ቢባል ስንት ሰው ተፈልጎ ከስንት ሰው ጋር ተወዳድረው ይሆን? ትዝታዎችዎትን ወደ ኋላ መለስ ብለው ማሰላሰልዎትን ለኋላ ያቆዩትና “ምን ቁጥሩ ቢበዛ በተአምር ለአንድ ስራ ከሚሊየን ሰዎች ጋር ተወዳድረው አያውቁም! ህንዳዊ ካልሆኑ በስተቀር!” የሚል የሚመስለውን የቢቢሲ መረጃ እኔ ልንገርዎት፡፡
ሀገረ ህንድ፤ በህዝብ ብዛቷ ወደር በማይገኝላትና ከ200 ሚሊየን በላይ ህዝቦች ይዛ በምትገኘው፤ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ውስጥ ነው፡፡ አንድ የመንግስት መስሪያ ቤት “ክፍት የስራ ቦታዎች አሉኝ… ብዛታቸውም 368 ነው፡፡ እናም እውቀቱና ችሎታው እኛ ጋር አለ የምትሉ ስራ ፈላጊዎች ማስረጃችሁን ይዛችሁ ወደኔ ኑ፤ አወዳድሬና ፈትኜ እቀጥራችኋለሁ” የሚል ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ 
ይህን ማስታወቂያ ያየ ስራ ፈላጊ እንዳለ ታዲያ እየተግተለተለ ማስታወቂያውን ወደአወጣው መስሪያ ቤት ማስረጃዎቹን እየያዘ መቅረብ ይጀምራ፡፡ እናም በመስሪያ ቤቱ ባሉት 368 ክፍት የስራ ቦታዎች ላይ ለመቀጠር 2.3 ሚሊየን ስራ ፈላጊዎች መስፈርት አሟልተው መመዝገባቸው የመስሪያ ቤቱን ሰዎች አጀብ አሰኝቷቸዋል፡፡
እናልዎት ወዳጄ ነገሩን እንዲሁ በቀላል ሂሳብ ብናሰላው በመስሪያ ቤቱ ለመቀጠር ካመለከቱ 6250 ሰዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው ስራውን የማግኘት እድል የሚኖረው እንደማለት ነው፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ይህ ብቻም አይደለም ታዲያ መስሪያ ቤቱ ለስራው የሚመጥኑ ሙያተኞችን ማወዳደሪያ መስፈርት ይሆነኛል ብሎ ያወጣው ቅድመ መመዘኛ፤ ‘አንድ ለመወዳደር የሚመጣ ስራ ፈላጊ በትንሹ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የተማረና ብስክሌት መንዳት የሚችል መሆን አለበት’ የሚል ነበር፡፡ 
መስሪያ ቤቱ ይህን ይበል እንጂ ታዲያ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎችና ደረጃዎች የተመረቁ፣ ሁለተኛ ዲግሪ ወይም ማስተርስ ያላቸውና 255 የሚሆኑ ዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ስራ ፈላጊዎች መስሪያ ቤቱን ቅጠረን ሲሉ ለመወዳደር ማመልከቻ ማስገባታቸው ነው ጉዳዩን ይበልጥ በግርት ጣትን አፍ ላይ እንዲያስጭን ያደረገው፡፡  
የስራ አጥነት ችግር ክፉኛ በተንሰራፋባትና በአስር ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿ ስራ አጥ በሆኑባት የህንዷ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት፤ መቼም የቸገረው እርጉዝ ያገባል እንደሚባለው ሆኖ ሳይሆን አይቀርም፤ ታዲያ እነዚህ ዶክተሮችና በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ምሩቃን ሳይቀሩ የተወዳደሩበት ይህ ስራ እድሉን አግኝቶ ለሚቀጠር አንድ ግለሰብ የሚያስገኘው የወር ገቢ በህንድ ገንዘብ ሩፒ 16 ሺ፤ ወደ ብር ስንመልሰው ደግሞ 4800 ብር ገደማ ብቻ ነው፡፡
እናልዎት ወዳጄ “እነዚህን 2 ሚሊየን 300 ሺ ስራ ፈላጊዎች አወዳድሮ ለመቅጠር ምን ያክል ጊዜ ይሆን የሚፈጀው?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አልቀረምና በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት የመስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊ አቶ ፕራባት ሚታል ለቢቢሲ ሲመልሱ… “ያው አመልካቾቹን ቃለ መጠይቅ ነው የምናደርግላቸው… እናም እያንዳንዱን አመልካች ቃለ መጠይቅ አድርገን እንጨርስ ብንል 4 አመታት ሳይፈጅብን አይቀርም!” ነው ያሉት፡፡ ታዲያ ይህም የሚሆነው 10 ቃለ መጠይቅ አድራጊዎች ተመድበው በአንድ ቀን 2 መቶ አመልካቾችን ቃለ መጠይቅ እያደረጉላቸው፤ በወር ለ25 ቀናት ከሰሩ እንደሆነም ነው ሀላፊው ያስረዱት፡፡
ወዳጄ እንግዲህ ምናልባት ነገሩን በሌላ መልኩ እንየው ካልን መስሪያ ቤቱ ላወጣው ክፍት የስራ ቦታ - እንደነ ጅቡቲ፣ ሌሴቶ፣ ጊኒ፣ ቦትሱዋና፣ ናሚቢያና ጋቦንን የመሳሰሉ የአፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ ሌሎች ከመቶ በላይ የሚደርሱ፤ የህዝብ ብዛታቸው 2.3 ሚሊየን የማይሞላ፤ ሀገራት ከያዙት - ከአንድ ሀገር ሙሉ ህዝብ በላይ ነው ቅጠረኝ ሲል ማመልከቻውን ያስገባው፡፡ 
ታዲያ ምናልባት ለቃለ መጠይቅ እድሉ ቢሰጠው አንድ ሰው ዛሬ ላይ ላስገባው ማመልከቻ ከአራት አመታት በኋላ ሊሆን ይችላል ቀጠሮው የሚደርሰው፡፡ ሊያውም ከአንድ ሀገር ሙሉ ህዝብ ቁጥር በላይ ከሆነ ስራ ፈላጊ ጋር ሊወዳደር ማለት ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ግን አራት አመት ለመቀጠር ከመጠበቅ ስራ ለመፍጠር ቢታትር አንድ ሰው የተሸለ ገቢ የሚያገኝበትን ስራ የሚፈጥር አይመስልዎትም ወዳጄ፡፡

ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment