ወዳጄ አሁን
የምንገኘው ቬትናም ውስጥ ነው፡፡ ታዲያ በቬትናም መንደሮች ሽርሽር ሲሉ እንደው ከወደ እግሩ አካባቢ አጓጉል የሆነ ዶሮ
ቢመለከቱ ‘ቡልቺና’ እንዳይመስልዎት አደራ፡፡ በዶሮ ነጋዴዎች ዘንድ አንድ ዶሮ ‘ቡልቺና’ ነው ማለት የታመመነው ማለት
እንደሆነ የዶሮ ተራ መዝገበ ቃል እንደሚያስረዳ ልብ ይሏል፡፡ እናማ በቬትናም መኖሪያውን ያደረገው የዶንግ ታኦ ዶሮ ዝርያ
እግሩ የዛፍ ስር መስሎ ቢመለከቱት ልዩ መለያው ሆኖ እንጂ ህመም ቢጤ ገጥሞት እንዳልሆነ ይወቁት፡፡
አመት በአል በመጣ
ቁጥር ዋጋው እየናረ፤ አንድ ሰሞን በአስርና በሀያ ብር ይገዛ የነበረ ወደል ዶሮ ዛሬ ላይ በመቶ የሚቆጠር ዋጋ እየተቆረጠለት “ምነው
አሁንስ አልበዛም እንዴ… ባይበላስ ቢቀር!” ሳያስብልዎት እንደማይቀር እገምታለሁ፤ የዶሮ ዋጋ፡፡ “መቶ ምን አላትና… እኛ ጋር
ቢመጡ አንድ ዶሮ በ50 ሺ ብር እንኳ ተለምነን ካልሆነ አንሸጥም” ይሉዎታል ቬትናማውያን፡፡
በቬትናም ዝነኛ
የሆነው ዶንግ ታኦ እየተባለ የሚጠራው የዶሮ ዝርያ ለንጉሳውያን ቤተሰቦችና እንዲሁም ለትላልቅ ክብረ በአሎች ማድመቂያነት ነው
እንጂ እንዲሁ እንደማንኛውም ተራ ዶሮ በቀላሉ ተገዝቶ ለምግብነት የሚውል አይደለም፡፡ ይህን ተወዳጅነቱን ተከትሎም የዶሮ
አርቢዎችን ቀልብ ክፉኛ መሳብ ችሏል፤ እንደ ኦዲቲ ሴንትራ ድረገጽ መረጃ፡፡ ዶንግ ታኦ የዶሮ ዝርያ ስያሜውን ያገኘው ከትውልድ
ከተማው ከሃንግ የን ግዛት ዶንግ ታኦ ከተማ ነው፡፡
በጎረምሳነት
የእድሜ ዘመኑ ከ3 እስከ 6 ኪሎ የሚመዝነው ዶንግ ታኦ ዶሮ እጅዎትን የሚያክል እግሩ ላይ ቆሞ ሲንጎማለል ሊታዘቡት ይችላሉ፡፡
ታዲያ ክሽን ተደርጎ የተሰራ ዶንግ ታኦ ቢፈልጉ ቅድሚያ ኪስዎትን መፈተሸ አለብዎት፤ ምክንያቱም ዶንግ ታኦ መገኛውን ያደረገው ኪሳቸው
ዳጎስ ባሉ ቱጃሮች ብቻ በሚዘወተሩ ትላልቅ የቬትናም ምግብ ቤቶች ብቻ ስለሆነ ነው፡፡
አንድ ኪሎ የሚመዝን
ዶንግ ታኦ እስከ አራት መቶ ብር ዋጋ የሚቆረጥለት ሲሆን ይህ ዋጋ ግን የቬትናማውያን ዘመን መለወጫ በተቃረበ ቁጥር እየናረ ይሄዳል፡፡
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2013 ሆ ቺ ሚኒህ ከተባለችው ከተማ ዶንግ ታኦን ሸክፎ የመጣ ገበሬ ለሁለት ዶሮዎቼ ባንገቴ ገመድ
ይገባል እንጂ ከ50 ሺ በታች በተአምር አልቀበልም ማለቱም በዘገባው ሠፍሯል፡፡
እንደ ሌሎች
ዶሮዎች አነስ ባለች ቦታ ላይ ታጉሮ መኖር የማይወደው ዶንግ ታኦ፤ በዚህ መልኩ ካስቀመጡት እርስ በእርሱ እየተፋጀ ምድርን
ቀውጢ ማድረግ ልማዱ ነው፡፡ በአብዛኛው ጊዜ ዶንግ ታኦ ዶሮዎች ነጭ ሲሆኑ ወንዶቹ ግን በተለያዩ ቀለማት የተዥጎረጎሩ ላባዎች
አሏቸው፡፡ ከእንቁላልነት ወደ ዶሮ ወጥነት ለመድረስ አንድ አመት ያክል ጊዜን የሚፈጅ ሲሆን እያደገና እድሜው እየጨመረ ሲሄድም
ስጋው እየጣፈጠ እንደሚሄድ ዶንግ ታኦን በማርባት የሚተዳደሩ ገበሬዎች ይመሰክራሉ፡፡
መቼም የዶንግ
ታኦን ነገር ቀምሰን ባናውቀውም የሀበሻ ዶሮ ተከሽና ስትሰራ ከፈረንጁ ይልቅ ጣእሟ ልዩ እንደሆነ እኛ ኢትዮጵያውያን
እናውቃታለን፡፡ ወዳጄ እንግዲህ አመት በአል እየመጣም አይደል ታዲያ በአላት ሲመጡ የደሮዎቻችን ዋጋ ሽቅብ እየዘለለ እንደ ዶሮ ሊያስጮኸን አይደል… “ዶሮአችን ከዶንግ
ታኦ ጋር ተዋውቃ ይሆን እንዴ ወደ መቶዎች ጠጋ ጣጋ እያለች ያለችው? ይሁን ምንም አይደል በሺዎች ልግባ እንዳትል እንጂ ይሄንንስ
እንደምንም እንችለዋለን 50 ሺ ዋጋ ይቆረጥልኝ ያለች ቀን ነው ጉድ የሚፈላው ሳያስብል የሚቀር አይመስለንም” ወዳጄ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ
ኤም 96.3
No comments:
Post a Comment