እንደ’ነ ዝንጀሮ ልክ
እንደ’ነ ጦጣ
ያለግብሩ ሊኖር ፍየል
ዛፍ ላይ ወጣ
ወዳጄ የአውሮፕላን
እግር ጥሎዎት እንደው ሞሮኮን የመርገጥ እድል ቢያገኙና… ወዲያ ወዲህ በሚሉበት አጋጣሚ ወደ አንዱ ዛፍ ቢማትሩ ከዛፉ ቅጠሎችና
ፍሬዎች በተጨማሪ ዛፉን መኖሪያቸው ያደረጉ አእዋፋትን ወይ ደግሞ እነ ጦጣንና እነ ዝንጀሮን ብቻ አይደለም የሚመለከቱት፡፡
ይልቁንም “እንዴ ምን ሊሰሩ ወጥተው ነው!?” የሚል አግራሞትን የሚያሸክምዎት የፍየል መንጋ ዛፍ ላይ ሰፍሮ፤ ቅርንጫፎች ላይ
ቆሞ፤ ቅጠል ሲበጥስም ጭምር በመደነቅ አይንዎትን እስከጥግ፤ አፍዎትን ደግሞ ገርበብ አድርገው ከፍተው ነው የሚመለከቱት፡፡
እናልዎት ወዳጄ
በእርግጥ ፍየል በባህሪዋ ቅጠል እየበጠሰች ወደ አፏ ለማድረግ፤ ገደል አፋፍ ላይ ሳይቀር፤ በሁለት እግሮቿ ተንጠራርታ የቻለችውን
ያክል ጉርሻ ወደ አፏ ማስገባቷ የተለመደና በየጊዜው የትም ፍየሎች ያሉበት ቦታ የምንታዘበው ጉዳይ ቢሆንም በሀገረ ሞሮኮ
የሚገኙ ፍየሎች ግን “ይሄም ይድነቃችሁ” ብለው ነው መሰል ልክ እንደጦጣ የዛፍ ቅርንጫፎች ላይ ቆመው ቅጠል ሲበጥሱ በካሜራ
ቀራጩ ሚካኤል ቺኒች እይታ ውስጥ ገብተው፤ እሱም በቪዲዮ ክሩ ቀድቷቸው “እኔ አንደው ድንቅ ብሎኛል ነገሩ… እናንተ ደግሞ
አይታችሁ የምትሉትን በሉ” ሲል ለአለም ማጋራቱን ነው ሜትሮ ድረገጽ ያስነበበው፡፡
በዛፍ ቅርንጫፎች
ላይ ያለምንም እክል ቆመው ቅጠል ሲበጥሱ የሚታዩት ሞሮኮአውያኑ ፍየሎች ዛፍ ላይ መከተማቸው ታዲያ በቦታው ለነበረው ካሜራ
ቀራጩ ሚካኤልና ሌሎች ቱሪስቶች አጀብ ይሁንባቸው እንጂ ለአካባቢው ነዋሪዎችና እንዲሁም ለራሳቸው ለፍየሎቹ ብርቅ ነገር ሳይሆን
የእለት ተእለት ውሏቸው ሆኖ ነው መሰል ለሰው ትኩረት ቁብ ሳይሰጡ ፍየሎቹ ዛፍ ላይ እንዳሉ ቅጠላቸውን ብቻ ነበር በጥሞና
የሚኮመኩሙት፡፡
ፍየልነት
ሰልችቶኛል እንደ ጦጣና ዝንጀሮ ዛፍ ለዛፍ እያልኩ ህይወትን ልሞክራት ያለ የሚመስለው የሞሮኮን ፍየል ነገር ሰምታ ሳይሆን
አይቀርም ሰውኛ ድምጽ ተውሳ እሪሪሪ ብላ የጮኸችውን ፍየል ቪዲዮ ይመልከቱ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን
እና ለኤፍ ኤም 96.3
No comments:
Post a Comment