“ያልተረዳሽው አለ አንድ ነገር
የእንባ በረዶ ባይን እስኪጋገር…”
ብሎ ነበር ድምጻዊው ፍቅሯ ክንፍ
አድረጎት ሲያያት ለሚሳሳላት ቆንጆ ያዜመላት፡፡ እርግጥ ይሄ ድምጻዊ የፍቅር ስሜቱን ለመግለጽ “የእንባ በረዶ በአይን
እስኪካገር…” ብሎ ስንኝ ቋጠረ እንጂ በእርግጥም እንባው ልክ እንደ ላውራ ፖንስ አይኑ ላይ በረዶ ሆኖ ተጋግሮበት አይደለም ግጥሙን
ከዜማ አወዳጅቶ ማቀንቀኑ፡፡
ምናልባት እርሰዎ ወዳጄ እንዳው
ጨዋታን ጨዋታ አንስቶት ስለ እንባ ጨዋታ ቢጤ ቢጀመርና በረዶ አለቀስኩ የሚል ሰው ቢገጥምዎት “ኧረ ወግድልኝ… ምንስ ቢዋሽ
እንዲህም ተብሎ፤ እንባዬ ከአይኔ ሲፈስስ እንደ ‘በረዶ’ ጠጥሮ ነው፤ ተብሎ ይዋሻል እንዴ?” ሊሉ እንደሚችሉ መገመት
አይከብደኝም፡፡ አደራዎትን እንዲህ ያለችዎት ብራዚላዊቷ ላውራ ከሆነች እንዲህ ያለ ምላሽ እንዳይሰጧት፡፡ ምክንያት ቢሉ “እንደ
በረዶ የጠጠረ እንባ አነባለሁ” ብትልዎት እውነቷን ነው፡፡
ላውራ ፖንስ በብራዚሏ ሊንስ ውስጥ
የህጻናት መምህርት ሆና ህይወትን እየመራች የምትገኝ ሴት ናት፡፡ ባልተለመደ መልኩ ጠጣር እንባ እያነባች ዘመናትን ያስቆጠረች
እንስት፡፡ ላውራ ከአይኗ የሚወጣው ‘የእንባ በረዶ’ መጀመሪያ በእርጥብ ፈሳሽ መልክ ነጭ ከለር ይዞ መውጣት የሚጀምር ሲሆን
ከአይኖቿ ልታስወጣው አይኗን ማርገብገብ ስትጀምር ግን እየረጋና እየተጋገረ ይሄዳል፡፡ አንዱ ሲወጣ በአንደኛው እየተተካም
ለሳምንታት ያክል እንዲሁ የምትዘልቅባቸው ጊዜያቶችም በርካታ ናቸው፡፡
ላውራ በቀን እስከ ሰላሳ የሚደርሱ
ግግር እንባዎችን ያለቀስችበት ወቅትም ነበር፡፡ “በመጀመሪያ እንባው አይኔን እየሞላ እየሞላ ይሄዳል… ከዛም አይኔን ከፍቼ
ላወጣው ስል እየጠነከረና እየደረቀ ይሄዳል፤ የዚያኔ ህመሙ አይጣል ነው!” ስትል ስለ ጠጣር እንባዋ የምትናገረው ላውራ ላለፉት
20 አመታት በዚህ መልኩ የተጋገረ እንባ ከአይኗ እየወጣ ነው የኖረችው፡፡
የ15 አመት ታዳጊ እያለች ለመጀመሪያ
ጊዜ ይህ ነገር የገጠማት ላውራ በወቅቱ ደንግጣ እናቷን እትዬ ማሪሳን ነበር የጠራቻቸው፡፡ አብጦ ከሚታየው አይኗ ላይ ጠጣሩን
እንባ ቢያወጡትም ታዲያ በዚያው አልቀረም፤ ከዚያን ጊዜ አንሶት እስከዛሬ ድረስ ከላውራ አይኖች ላይ እየተፈነቀለ ይወጣል፡፡
“ካወጣነው በኋላ በጣም ነበር
የደነገጥነው” ሲሉ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የሚያስታውሱት እትዬ ማሪሳ “እየተንደረደርን ያመራነው ወደ ሆስፒታል ድንገተኛ
ክፍል ነበር… ታዲያ በሆስፒታሉ የነበሩት ዶክተሮች ልክ እንደኛው ሁሉ በጣም የደነገጡ ሲሆን ነገሩ እንቆቅልሽ ነበር የሆነባቸው”
ሲሉ በትዝታ ሀያ አመታትን ወደኋላ ተጉዘው ሁኔታው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከሰት እንዴት እንደነበር አውስተዋል፤ እንደ ኦዲቲ
ሴንትራል ዘገባ፡፡
ዛሬ ላይ የ35 አመት ጎልማሳ
የሆነቸው ላውራ ምንም አይነት መፍተሄ አግኝታ ‘የእንባ በረዶ’ ከማንባት ልትገላገል አልቻለችም፡፡ በወራት ልዩነትም ይህ ግግር
እንባ የላውራን አይን እየደጋገመ ይጎበኘዋል፡፡ “ከዶክተር ዶክተር እየዞርን መፍትሄ ብንፈልግም ‘ችግሩ ከዚህ የተነሳ ነው’ ‘ይሄ
ነገር እንዲህ ስለሆነ ነው’ የሚል ማብራሪያ ቢጤ የሚሰጠን እንኳ አላገኘንም” ሲሉም ነው እመት ማሪሳ አስተያየታቸውን
የሰጡት፡፡
“የህጻናት መምህርት ነኝ፡፡ ግን በቃ
ስራዬን በአግባቡ መከወን አለመቻሌ በጣም ነው የሚያበሳጨኝ… ከ2 አመት በፊት ለ6 ወራት ያክል በየቀኑ 30 ጠጣር እንባዎችን
ከአይኔ እያወጣሁ አሳልፌያለሁ” የምትለው ላውራ ዛሬ ላይ ህክምናዋን ዶክተር ራውል ጎንካልቭስ ዘንድ እየሄደች በመከታተል ላይ
ትገኛለች፡፡ ዶክተር ራውልም ቢሆኑ ታዲያ እንዲህ ያለው ጉዳይ ገጥሟቸው እንደማያውቅና በህክምና ታሪክ መዛግብት ውስጥም መሰል
ክስተት ስለመፈጠሩ የተባለ ነገር አለመኖሩን ነው የሚናገሩት፡፡
25 አመታትን በአይን ህክምና ላይ
በመስራት ያሳለፉት ዶክተሩ “የላውራን ጉዳይ ለማጥናትና ማብራሪያ ለመስጠት የቻልኩትን ያህል እየሞከርኩ ነው፡፡ እንደዚህ ቶሎ
ቶሎ የሚፈጠሩት ጠጣር እንባዎች መፈጠሪያ መንስኤያቸው ኬሚካል ሊሆን እንደሚችል ብቻ ነው መናገር የሚቻለው” ብለዋል፡፡ “በላውራ
እንባ ውስጥ ያለው የፕሮቲን መጠን አይኖቿን ከባክቴሪያ መጠበቅ ስላልቻለ አይኗ ሌላ መከላከያ እያመረተ ሊሆን ይችላል” የሚል
ግምታቸውንም ነው ያሰፈሩት፡፡
ላውራ ከዚህ ህመሟ የምትፈወስበትን
ቀን በተስፋና በጉጉት እየጠበቀች ሲሆን “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አይኖቼ ከዚህ ችግር እንዲላቀቁ ነው ምኞቴ” ስትልም ነው
አስተያየቷን የሰጠችው፡፡ ለላውራ ፈጣሪ ምህረቱን ያወርድላት ዘንድ እየተመኘን “አያድርስ” ከማለት ሌላ ምን ማለት ይቻላል ወዳጄ!!!
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ
ኤም 96.3
No comments:
Post a Comment