Thursday, September 3, 2015

ቻይናውያን ጦጣዎች ወፍ አባራሪ ሆነው ስራ ጀመሩ

የታረሰው መሬት እህል ተዘርቶበት ጊዜውን ጠብቆ ሰብሉ ሲደርስ እህሉን ከወፍ ከዝንጀሮና ከጦጣ እህሉን መጠበቅ ግድ ነው፡፡ ሰብሉን እንዳይበላ የሚጠብቁ ታዳጊዎች ከማማ ላይ ተቀምጠው ወፎች ዝንጀሮዎችንና ጦጣዎችን በወንጭፍ እያካለቡ ሲያባርሩ ይውላሉ፡፡ ይህ እንግዲህ እዚህ እኛ ሀገር ነው፡፡ “ኧረ እኛ ጋር ‘ወፍ የለም’ እንዲ የሰው ሰብል ምናምን ነገር አይመቸንም” ያሉ የሚመስሉት ቻይናውያን ጦጣዎች ግን “እኛ እራሳችን ወፍ እናባርራለን፤ ብቻ የእለት ጉርሳችንን እና ትንሽ ስልጠና ቢጤ ስጡን… የምን ያልዘሩትን ማሳ ለማጨድ መክለፍልፍ ነው” ሳይሉ አልቀሩም፡፡
ወዳጃችን ቻይና የሁለተኛው አለም ጦርነት በድል መጠናቀቅን አስመልክታ የምታከብረው የድል ቀኗን በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅና በእለቱ በሚደረገው ወታደራዊ ሰልፍ ላይ የሚደረጉ የተለያዩ የአውሮፕላን በረራ ትርኢቶችን ወፎችና እርግቦች እንዳያስተጓጉሉ ስትል “እንደው በዚህ ነገር ላይ ብታግዙኝ ምን ይመስላችኋል?” ብላ የጦጣዎችንና የጭልፊቶችን በር አንኳኩታለች ይላል አሶሼትድ ፕሬስ ያስነበበው ዘገባ፡፡
በቂ ስልጠናን የወሰዱት ጦጣዎች የእርግቦችን ማደሪያ ጎጆ እንዳልነበር አድርገው በማፈራረስ የተካኑ ሆነዋል፡፡ ጭልፊቶቹም ቢሆኑ አንዲትም ወፍ ወታደራዊ የአውሮፕላን ትርኢቱ በሚካሄድበት አካባቢ ዝር እንዳትል እያሳደዱ የገባችበት ገብተው እንዲያድኗት ነው ተልእኳቸውን የተቀበሉት፡፡ እነ ጦጢት ተልእኳቸውንም ወታደራዊ ሰላምታ ሰጥተው ነው ተቀብለው ወደ ስራ የተሰማሩት፡፡
“ባለፈው አመት ነበር ከሄናን ግዛት ሁለት ጦጣዎችን የገዛነው… ለአንድ ወር ካሰለጠንናቸው በኋላም የወፍ ጎጆ የሚባልን ነገር ድራሹን የማጥፋት ክህሎት በደንብ ማዳበር ቻሉ፡፡” የሚሉት የአየር ሀይሉ ባለስልጣን ዋንግ ሚንግዢ “ሌሎች ሶስት ጦጣዎችም የወፍ ጎጆ አፍራሽ ግብረሀይሉን ተቀላቅለውታል፡፡ እናም ይሄ የጦጣዎች ቡድን በቀን ውስጥ እስከ 60 የሚደርሱ የወፍ ጎጆዎችን ድምጥማጣቸውን አጥፍቶ የመመለስ ብቃት አለው፡፡ ተልእኮውን ፈጽሞ ሲመለስም የተዘጋጀለትን ሽልማት ይቀበላል፡፡” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
ነገሩ… “ያላረሰውን መሬትና ያልዘራውን እህል፤ ሰብል ሲደርስ ቀን ጠብቆ ሊፈጅ የሚመጣው ያገሬ ጦጣና ዝንጀሮ ከቻናውያን አጎቶቹ እንዲህ ያለውን በጎ ስራ ቢማር ምናለበት!?” የሚል ቁጭት ቢጤ የሚያሳድር ነው መቼም… አይደል እንዴ ወዳጄ? ቻይናውያኑ ጦጣዎችና ጭልፊቶች አንደበት ቢኖራቸው ኖሮ ስራቸውን ሰርተው ከጨረሱ በኋላ ይቺ እዚህ እኛ ሀገር ሰሞንኛ ሆና በርካቶች ሲሏት የምንሰማትን… ምናልባት ደግሞ እኛም የምንላትን ‘ወፍ የለም’ የምትል አባባል የሚጠቀሟት ይመስለኛል፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment