Wednesday, September 2, 2015

ከበሰበሰ ማንጎ ዝንጥ ያለ የቆዳ ቦርሳ እየተሰራ ነው



ወዳጄ መቼም አዲስ አበባችን እንደ ስሟ አበባ እድትሆን የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም አሁንም የጽዳት ችግር በብዙ አካባቢዎች ላይ ይስተዋላል፡፡ እንዲህ የጽዳት ነገር አሳሳቢ ከሆነባቸው ቦታዎች መካከል ደግሞ በተለምዶ አትክልት ተራ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ተጠቃሽ ነው፡፡ እናልዎት ይህ ቦታ ጽዳት ለማጣቱ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት በአካባቢው ከሚሸጡ አትክልትና ፍራፍሬዎች እየተመረጡ የሚጣሉ የበሰበሱ ወይም በሰፈርኛ ስማቸው ‘ማርች’ የሆኑ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ናቸው፡፡

“የአትክልት ተራችሁን ጽዳት ችግር እስከወዲያኛው የሚገላግል መፍትሄ ከወደ ኔዘርላንድ አካባቢ ተግኝቶላችኋል” ያለ የሚመስለው ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ኔዘርላንዳውያን ተማሪዎች የበሰበሱ ፍራፍሬዎችን ዝንጥ ወዳሉ የፍራፍሬ ቆዳ ውጤቶች ቀይረዋችል የሚል ዘገባ አስነብቧል፡፡ ለአካባቢ ስነ ምህዳር በጣም ምቹ ነው የተባለው የተማሪዎቹ ፈጠራ የበሰበሱ ፍራፍሬዎችን ወደ ሌዘር በመቀየር የተለያዩ ነገሮችን መስራት የሚያስችል ነው፡፡

ስድስት አባላት ያሉት በሮተርዳም የሚገኘው የዊለም ደ ኩኒንግ አካዳሚ ተማሪዎች ቡድን የተሰራውና ‘ፍሩት ሌዘር ሮተርዳም’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ አዲስ የፈጠራ ስራቸው ለረዥም ጊዜ መቆየት የሚችል ጠንካራ ሌዘር መሰል ሲሆን በቀለላሉ የተለያዩ ነገሮችን ለመስራት የሚያስችልም ነው፡፡ 
በትምህርት ቤታቸው የቤትስራ የተሰጣቸው ተማሪዎቹ የቤት ስራቸውን ብቻም ሳይሆን እግረመንገዳቸውን የምግብ ብክነትን ለመከላከልም ይወስናሉ፡፡ “ሮተርዳም ውስጥ የሚገኘውንና በየሳምንቱ ማክሰኞና ቅዳሜ ግብይት የሚካሄድበትን ‘ቢኔንሮት አደባባይ’ በደንብ እንድናጤነው አካዳሚው ጥሩ ጥቆማ ሰጠን፤ እናም ስንመለከተው በገበያ ቀናቱ ማታ ላይ አካባቢው በወዳደቁ ምግቦች በጣም እንደሚዝረከረክ ለመረዳት ቻልን” የሚለው የተባሪዎቹ ቡድን አባል ኢውጎ ደ ቡን፤ “እናም ይህን ተመልክተን ነው ይህ ችግር በኛ አቅም እንዴት ባለ መልኩ መፈታት ይችላል? ብለን ወደ ስራ የገባነው ብሏል፡፡
ተማሪዎቹ ባደረጉት ጥናትም በገበያ ቦታዉ ላይ በየቀኑ 28 ኩንታል ገደማ ምግብ አለአግባብ ባክኖ እንደሚቀር ያረጋግጣሉ፡፡ በርካታ ነጋዴዎችም የበሰበሱ ፍራፍሬዎችን በአግባቡ ለማስወገድ ገንዘብ ላለማውጣት ሲሉ በየሜዳው እንደሚደፏቸው ያረጋግጣሉ፡፡ ይህ መልካም አጋጣሚ ሆኖ ያገኙት ተማሪዎቹ እነዚህን የበሰበሱ፤ እንደ ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ፖምና ሌሎች መሰል ፍራፍሬዎችን ከነጋዴዎች ላይ እየሰበሰቡ ነው ሌዘር ቆዳ መሰል ቁስ ማምረት የጀመሩት፡፡
እንዴትና በምን መልኩ እንደሰሩት ግን የቡድናችን ምስጢር ነው ሲሉ መናገር አልፈለጉም፡፡ ሆኖም የአሰራር ሂደቱን ደ ቡን ሲያስረዳ “በቅድሚያ ከፍራፍሬዎቹ ላይ ፍሬዎችን በማስወገድና ፍሬ የወጣላቸውን አንድ ላይ በመፍጨት፤ ባክቴሪያዎችን ለመግደል እንደሚያፈሉት… ከዛም ከቀዘቀዘ በኋላ ለዚሁ ስራ ተብሎ በተዘጋጀ ቦታ ላይ በማፍሰስ እንደሚያደርቁት… በመጨረሻም ሌዘር እንደሚሆን ነው” የተናገረው፡፡ 


ለጅማሬ ያክል በሌዘሩ ቦርሳዎችን የሰሩት ተማሪዎቹ ነገር ግን የፈጠራ ውጤታቸው አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለመስራት እንደሚያስችል ነው የሚናገሩት፡፡ “በርካቶች ቦርሳ ብቻ የምንሰራ ይመስላቸዋል… ነገር ግን ይህ ማሳያ ነው እኛ የሰራነው ቦርሳውን ብቻ ሳይሆን ቦርሳው የሚሰራበተን ጥሬ እቃ ነው” ሲል የሚናገረው ደ ቡን “የበርካታ አምራቾች ቀልብን መሳብ የቻለውን የፈጠራ ውጤታችንን በብዛት ለማዳረስና የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ እንደ ቡድን እቃውን በተመለከተ መመለስ ያለብንን ጥያቄ እየተነለከትን ነው” ብሏል፡፡ 

“በዚህ ስራችን ማሳካት የምንፈልገው እየባከነ ያለውን ምግብ መጠን በተመለከተ ግንዛቤ መፍጠርና መፍትሄውን ማሳየት ነው” የሚለው የተማሪዎቹ ድረገጽ “ምግብ ቆሻሻ አይደለም፤ ነገሮችን በተለየ መንገድ መመልከት ብቻ ነው የሚያስፈልገው! እኛ ያለንን እውቀት ተጠቅመን ለችግሩ መፍተሄ በዚህ መልኩ አበጅተናል፡፡” የሚል መልእክት ሰፍሮበታል፡፡ ወዳጄ ይህ የኔዘርላንዳውያን ተማሪዎች ፈጠራ እዚህ እኛ ጋርም ቢፈጠር የአትክልት ተራ ችግር ብቻ ሳይሆን የከተማችን የጽዳት ችግር ዳግም ላይመለስ የሚፈታ አይመስልዎት? አንድም ለራስ ጥቅም በሌላ መልኩ ለጽዳቱ ችግር መፍትሄ የፈጠራ ባለሙያዎች ፈጠን ፈጠን ብላቻሁ ይህን ነገር በደንብ አጢኑት ብያለሁ፡፡

ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.

No comments:

Post a Comment