Sunday, September 6, 2015

ቀለም ቀቢዋ ጥበበኛ የ87 አመት አዛውንት፤ እማማ አግኔስ ካስፓርኮቫ



እድሜ የቁጥር ጉዳይ ነው ይባላል፡፡ ልክ ነው ለዚህ ማሳያ ደግሞ እመት አግኔስ ካስፓርኮቫ አይነተኛ ምሳሌ ናቸው፡፡ የ87 አመት የእድሜ ባለጸጋዋ ቼካዊት እመት ካስፓርኮቫ ጥበብ ጮክ ብላ የጠራቻቸው አያት ናቸው፡፡ 

ምንም እንኳ እድሜያቸው ቁጥሩ ጨምሮ እንደ ልብ ተፍ ተፍ እንዳይሉ ቢገድባቸውም አሁንም ከልብ የሚወዱትን ስራ ባለቻቸው ትርፍ ጊዜ ከመስራት አልገደባቸውም፡፡ በመንዳራቸው ዘወር ዘወር እያሉ የጎረቤቶቻቸውን ቤቶች በድንቅ የቀለም ቅብ ጥበባቸው ተጠቅመው የተለያዩ ስእሎችን በመሳል ግድግዳዎችን የማሳመር ስራ ይሰራሉ፡፡
ከ30 አመት በፊት ከግብርና ስራቸው በጡረታ የተገለሉት እመት ካስፓርኮቫ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ይህን ቤቶችን ለየት ባለ የቀለም ቅብ የማሳመር ስራቸውን እያቀላጠፉ ነው ዛሬ ላይ የደረሱት፡፡ 
እማማ ካስፓርኮቫ ምንም እንኳ እጆቻቸው ቢዝሉም ዛሬም ድረስ ውስብስብ ባሉ ጥበቦችን ተጠቅመው በሰማያዊ ቀለም ደምቀው የሚታዩ ስእሎችን የመሳል ተግባራቸውን በንቃት ይከውናሉ፡፡ “የምወደውን ስራ ነው እየሰራሁ ያለሁት!” የሚሉት እማማ “እንዳው ትንሽ አለማችንን ባሳምራት ብዬ ነው እየጣርኩ ያለሁት” ማለታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል፡፡
“ህይወትን ካለስራ ፈጽሞ አላስባትም” የሚሉት አሜቴ ካስፓርኮቫ “እቤት ውስጥም በሉት… መናፈሻ ውስጥም ይሁን ወይ ደግሞ ቀለም እየቀባሁ ብቻ ስራ እሰራለሁ” ሲሉም ነው ቆፍጠን ብለው የሚናገሩት፡፡ እማማ ካስፓርኮቫ የቀለም ቅብና የስእል ጥበባቸውን የተማሩት ማናኮቫ ከተባሉ ሴት ነበር፡፡ እሳቸው በሞት ሲለዩአቸው ስራውን ቀጥ አድርገው ለመስራት የወሰኑት፡፡ ታዲያ ስራቸውን ሲሰሩ ውድ የሆነ ቀለም መጠቀምን ይመርጣሉ፡፡
“እንዳው አነሰ ቢባል ለሁለት አመት ያክል ውበቱ ቅንጣት ሳይደበዝዝ መዝለቅ ይችላል” ሲሉም “ዋስትናውን በኔ ጣሉት” እስከማለት ድረስ በስራቸው ይተማመናሉ፡፡ አበቦች የሚበዙበት የቀለም ቅብ ስራቸውን፤ እማማ ካስፓርኮቫ፤ አስቀድመው አስበውት ወይም አቅደው አይደለም ወደ ስራ የሚገቡት ይልቁንም ስራውን ከጀመሩት በኋላ በቃ እንዲው የጥበብ ጅረት በብሩሻቸው በኩል አድርጎ ግድግዳው ላይ እየፈሰሰ ውበትን ይስላል፡፡
እድሜ ያልገደባቸው እመት ካስፓርኮቫ የቀለም ቅብ ስራቸው ምንም አልከበዳቸውም ብቻ የክረምት ወራት ግን ትንሽ ያስቸግሯቸዋል፡፡ እነሱም ቢሆኑ ግን ታዲያ ከመስራት አይገድቧቸውም፡፡ በየአመቱ ግንቦት ወር በመጣ ቁጥርም በአካባቢያቸው ያለውን ቤተመቅደስ በጥበባቸው ያሳምሩታል፤ መሰላል ላይ እየወጡ ጭምር፡፡ ከእማማ ካስፓሮቫ ለስራ ፍቅርን፤ ለእድሜ ሸክም አለመበገርን መማር አንችልም ታዲያ ወዳጄ፡፡ “ሊያውም ግጥም አድርገን ነዋ!!!” ብለው እንደሚመልሱልኝ አልጠራጠርም፡፡

ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment