Thursday, September 17, 2015

“ትልቅ ጡት” የቬንዙዌላውያን እንስቶችና የልብስ ቤት አሻንጉሊቶች ትልቅ ሀሳብ

በእርግጥ መቼና እንዴት እንደተጀመረ ለማወቅ አዳጋች ቢሆንም ዛሬ ዛሬ በየአልባሳት መሸጫ ሱቆች በራፍ ላይና ወደ ውስጥ ዘለቅ ሲሉ ትከሻቸው ሰፋ፤ ሰውነታቸው ፈርጠም ያሉ በወንድ አምሳል የተሰሩና እንዲሁም ሸንቀጥቀጥ ያሉ፤ ተክለ ቁመናቸው ያማረ በሴት አምሳል የተሰሩ አሻንጉሊቶች ሽክ በልክ በሆነ መልኩ ተሽቀርቅረው በየእለቱ አንዱን ልብስ በሌላ እየቀያየሩ ቆመው መታየታቸው ከተለመደ ሰነባብቷል፡፡
ይህ የአሻንጉሊቶች ነገር ታዲያ እዛ በአገረ ቬንዙዌላ በሚገኙ የልብስ መሸጫ ሱቆችም የተለመደ መሆኑ እንዳለ ሆኖ የቬንዙዌላ የልብስ ቤት አሻንጉሊቶች፤ በተለይም በሴት አምሳል የተሰሩቱ፤ ከኛዎቹ ለየት የሚያደርጋቸው ከወደ ደረታቸው አካባቢ ዳጎስ ብለው በመታየታቸው ነው፡፡ “ይህ ለምን ሆነ?” የሚል ጥያቄ አያነሱም ወዳጄ፡፡ ለምን መሰልዎት ከቬንዙዌላውያን እንስቶች መካከል ከሶስቱ አንደኛዋ ከወደ ደረቷ አካባቢ ጎላ አድረገው የሚያሳዩአት ጉች ጉች ያሉ ጡቶች እንዲኖሯት አብዝታ ትፈለጋለች፡፡ ይህ ፍላጎቷ እንዲሁ ፍላጎት ብቻ ሆኖ እንዲቀር ደግሞ አትፈቅድም፤ ለዚህ ጉዳይ መላዎች አሉን ወደሚሉ የህክምና ጠቢባን ጋር ጎራ ብላ በፍቃዷ የቢላ ሲሳይ በመሆን በቀዶ ጥገና ጡቶቿን እንደ አዲስ አፍርሳ ታሰራቸዋለች፡፡ “ይህስ ለምን ይሆናል?” ሌላኛው ጥያቄዎት ከሆነ “ለቬንዙዌላዊት ሴት ከደረቷ ግድም በዛ ብላ መታየት የውበቶች ሁሉ ውበት ነውና ነው” የኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ምላሽ ነው፡፡
የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና በቬንዙዌላውያን እንስቶች ዘንድ እጅጉን የተለመደ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ነገሩ የቡና ወሬም ሆኖ ሴቶቹ ስላከናወኑት ቀዶ ጥገና በልበ ሙሉነት ነው በየቦታው ሲያወሩ የሚደመጡት፡፡ ወጪውን ለመሸፈን አቅማቸው አልፈቅድ ያላቸው ሴቶችን እንኳ ከእለት ጉርሳቸው ቀንሰው፣ ቆጥበውና እቁብም ካላቸው ጥለው ቀዶ ጥገና ለማድረግ ሲጥሩ መታየታቸው የተለመደ ነው፡፡ አንዲት ቬንዙዌላዊት እንስት ጡቶቿ ተልቀው እንዲታዩ በኛ ወደ 130 ሺ ብር ገደማ ሆጭ አድረጋ መክፈል ይጠበቅባታል፡፡ ይህ ገንዘብ ለአንድ ቬንዙዌላዊ የሶስት ወር የኑሮ ወጪ  መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ይህን ያዩ የልብስ ቤት አሻንጉሊቶች ታዲያ “እኛስ በምን እዳችን ከወደ ደረታችን አነስ ብለን እንታያለን!” ሲሉ ነው በሚመረቱበት ፋብሪካ ያሉ ሙያተኞች ዳጎስ ዳጎስ ያሉ ጡቶችን በደረታቸው እያስታቀፏቸው እንዲወጡ ለመደረግ የተገደዱት፡፡ ይህ ጉዳይ በቬንዙዌላ የሚገኙ ልብስ ለባሽ አሻንጉሊት አምራቾችንም በምርቶቻቸው ላይ በዛ ያለ ጡት እንዲጭኑባቸው አስገድዷቸዋል፡፡
ቬንዙዌላውያን እንስቶች ከደረታቸው በኩል በዝተው ለመታየት ወደ ህክምና ተቋማት ሲያመሩ አሻንጉሊቶቹ ደግሞ የሚያመሩት ወደ ዶክተራቸው ማኑኤን ቦኒላ ነው፡፡ የአሻንጉሊቶች ዶክተር የሚል ማእረግ የተቸረው ማኑኤል ለአሻንጉሊቶች ቀዶ ጥገና የሚሰጥ ተቋም ከፍቶ እየሰራ የሚገኝ ስራ ፈጣሪ ነው፡፡ መንደሪን የምታክል ጡት ይዛ እሱ ጋር የመጣች አሻንጉሊት ሀብሀብ የሚያክል ጡት ተገጥሞላት ነው የምትወጣው፡፡ “ጥበብ ብለው ይጥሩት አይጥሩት አላውቅም… እሱን ለሌሎች እተወዋለሁ፡፡ ነገር ግን እኛ ለየት ያለ ስራን ነው እየሰራን ያለንው ምክንያቱም የደንበኞቻችንን ፍላጎት ለማሳካት እየሰራን ነው” ሲል ነው ማኑዌል ስራውን አስመልክቶ አስተያየቱን የሠጠው፡፡
ወዳጄ እንግዲህ ቬንዝዌላውያኑ እንስቶች ከወደ ደረታቸው መአት ሆነው ለመታየት በመፈለጋቸው እራሳቸውን የቢላ ሲሳይ ማድረጋቸው ሳያንስ ጦሳቸው ለአሻንጉሊቶቹም ተርፎ አገር ሰላም ብለው የቆሙት አሻንጉሊቶች ፈርሰው እንዲሰሩ እያስገደዷቸው ነው፡፡ ውስጣዊ ውበት የሚባል ነገር የለም ውበት ሲባል ፊት ለፊት በአይናችን የምናየው ነው በተለይ ደግሞ ትላልቅ ጡቶች ወደር የማይገኝላቸው የውበት መገለጫዎች ናቸው የሚሉም ቬንዝዌላውያን አልጠፉም፡፡

እናልዎት እነሱ ይሄን ይበሉ እንጂ ነገ ከነገወዲያ እድሜ ሊያሟሽሸው ለውጫዊ ውበት ተጨንቆ ከእለት ጉርስ እየቀነሱ ተቆርጦ መቀጠል ትክክል አይመስለንም፡፡ ይህን ያክል ወጪ አውጥቶ ነገ የሚናድ አካላዊ ውበት ከመከመር አንድም ውስጣዊ ስብእናን ማሳመር ወይ ደግሞ ገንዘቡ ተርፎናል ካሉ ለበጎ አድራጎት ተግባር ቢያዉሉት ከምንም በላይ፤ ቆንጆ ሆኖ ከመታየትም በላቀ መልኩ የህሊናን እርካታ ያስገኛል ብዬ አምናለሁ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment