Saturday, September 26, 2015

የካርቶን ጦርነት…

ወዳጄ መቼም አለማችን በየጥጋጥጉና በዱር በገደሉ የጦርነት አውድማ ከሆነች ስለመሰነባባቷ በየእለቱ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች የምንሰማቸውና የምናያቸው ጦርነት ተኮር መረጃዎች  ምስክር ናቸው፡፡ ግን እስከዛሬ ከሰሟቸው የተደረጉና እያተደረጉ ያሉ ጦርነቶች መካከል ስለ ካርቶን ጦርነት የሰሙት ነገር አለ እንዴ!? “ደግሞ የምን የካርቶን ጦርነት ነው!?.. ካርቶንን ስናውቀው እቃ መሸከፊያ ሆኖ ነው እንጂ መቼ ነው ደግሞ ጦርነት የሆነው!?” የሚል አግራሞት አዘል ጥያቄ እንደሚሰነዝሩ አያጠራጥርም፡፡
እርግጥ ነው ካርቶን እስከዛሬ በተለያዩ መጠኖችና ቅርጾች እየተዘጋጀ አቅሙ የፈቀደለትን እቃ የሚሸከም፤ ከወፍራም ወረቀት የተሰራ ስልቻ ሆኖ ነው የሚታወቀው፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ካርቶን የጦርነት አውድማ ማድመቂያ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል የሚለው ኦዲቲሴንትራል ድረገጽ አይዞዎት የካርቶን ጦርነት ሰው የሚያልቅበት ሳይሆን ተሰብስቦ እየተዝናና የሚደሰትበት ጦርነት ነው ሲል አስነብቧል፡፡
የካርቶን ጦርነት መነሻውን ከአውስትራሊያ ቢያደርግም ዛሬ ላይ በበርካታ የአለም ክፍሎች የሚከወን ልዩ መዝናኛ እየሆነ መጥቷል፡፡ የካርቶን ጦርነት መነሻ ሀሳብ በፈረንጆቹ አለም ያሉ ህጻናት በካርቶን የሚሰሩ ሽጉጦችን በመጠቀም የሚጫወቱተን፤ ልክ እዚህ እኛ ሀገር ‘ሸራብ-ሸራብ’ እያሉ ህጻናት ቆርኪ ቀጥቅጠውና ጭቃ ጠፍጥፈው በሰሯቸው ሽጉጦች እየተደባበቁ ‘ተኮስኩብህ’ ‘ገደልኩህ’ እየተባባሉ እንደሚጫወቱት ካለ የጨዋታ ሀሳብ መበነሳት ሲሆን ጨዋታው በዘመነ አቀራረብና ባደገ መልኩ ነው በጦርነቱ ላይ የሚተገበረው፡፡
የካርቶን ጦርነት ሀሳብ የተጠነሰሰው ታዲያ በአውስራሊያውያኑ ጓደኛማቾች ሆስ ሲጌል እና ሮስ ኮገር እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2002 ዓ.ም ነበር፡፡ አንድ ሁለት እያሉ ሲዝናኑ ሀሳቡን ያፈለቁት ጓደኛማቾቹ በግቢያቸው ውስጥ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ሆነው የካርቶን ጦርነት ማካሄድን ይጀምራሉ፡፡ በተለያ ጊዜያት በሚያደርጓቸው ጦርነቶች ላይ ታዲያ የካርቶን መሳሪያዎቹ አይነትና ጥራት እያደገ እያደገ ሄዶ ካርቶኖቹ የግቢያቸውን የመያዝ አቅም ሲፈታተኑት ጦርነቱን አደባባይ ይዘውት ለመውጣት ይወስኑና በአካባቢቸው ወዳለው መናፈሻ አምርተው እነሱ ቦክሲንግ ዴይ ሲሉ በሚጠሩት የፈረንጆች ታህሳስ 26 ቀን በመናፈሻው ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የካርቶን ጦርነትን ዘደረጉ፡፡ በወቅቱም ድርጊታቸው የበርካቶችን ቀልብ መሳብ በመቻሉ እነሆ ከዚያን ጊዜ አንስቶ የካርቶን ጦርነት በየአመቱ እየተካሄደ፤ በመላው አውስትራሊያና በተለያዩ የአለም ክፍሎች ከቦክሲንግ ዴይ ባለፈም በተለያዩ ክብረ በአሎች ላይ በበርካቶች ዘንድ እየተተገበረ ዛሬ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡
የካርቶን ጦርነት ተፋላሚዎች ጸበኞች ወይም ባላጋራዎች አይደሉም፤ ይልቁንም የሚዋደዱ ጋደኛሞች ቤተሰቦችና ሌሎችም ይሆናሉ፡፡ ጦርነቱ ተሳታፊዎች እራሳቸው በካርቶን የተለያዩ አይነት መሳሪያዎችን አስመስለው ሰርተው ወደ ጦርነት አውድማው ያመራሉ፤ ጦርነቱ እንደተጀመረም መጎዳዳት በሌለው መልኩ ውጊያ ይጀመራል፤ ከካርቶን የተሰሩት የጦር መሳሪያዎችም እንዳይሆኑ ሆነው ድምጥማጣቸው ይጠፋል፡፡ ወዳጄ ይሄ ነው እንግዲህ የካርቶን ጦርነት፡፡
እናልዎት ወዳጄ የካርቶን ጦርነት፤ በግርድፉ ወደኛ ሀገር ስንመልሰው ዘመናዊ ‘ሸራብ-ሸራብ’፤ እንዲያው ልጅነቴ ማርና ወተቴ አይነት ነገር ይመስላል፡፡ ተመልሶ የማይመጣውን ልጅነት ትልቅ ሆኖ መዘከር አይነት ነገር፡፡ ታዲያ ፈረንጆቹ ይሄን የልጅነት ጨዋታቸውን በዚህ መልኩ አሳድገውት ብዙዎች እንዲተገብሩትና እንዲዝናኑበት እያደረጉት ነው፡፡ ለመሆኑ ግን ወዳጄ በርካቶቻችን በልጅነት ሳለን የምናዘወትራቸውን ጨዋታዎች እናስታውሳቸዋለን? የዛሬ ህጻናትስ ጨዋታዎቹን ያውቋቸዋል ወይስ ከውጪው አለም በመጡ ጨዋታዎች ነው የተዋጡት? ይሄ ጥያቄዬ ነው በተለይም ለወላጆች፡፡ ከካርቶን ጦርነት ግን ባህልን አዘምኖ ማሳደግና ለአለም ማስተዋወቅን መማር እንደምንችል እገምታለሁ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍኤም 96.3 

No comments:

Post a Comment