Wednesday, September 16, 2015

ሩሲያዊቷ ስፖርተኛ ከቀላል ባቡር ጋር ገመድ ጉተታ ገጥማ ባቡሩን አሸነፈችው!

ወዳጄ መቼም ገመድ ጉተታ የሚባለውንና አሸናፊው ወደ ኋላ ተሸናፊው ደግሞ ወደፊት የሚወድቅበትን ስፖርት እንደሚያውቁት አያጠያይቅም፡፡ ምናልባትም ደግሞ በሆነ አጋጣሚ ገመድ ጉተታ ላይ ተሳትፈውም ያውቁ ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው ገመድ ጉተታ ስፖርት በሁለቱም ጥግ ሰዎች ተደርድረው ገመድ በመጓተት ይበልጥ ጠንካራ የሆነው ቡድን ተጋጣሚውን ጎትቶ መስመር በማሳለፍ የሚሸንፍበት ስፖርት እንደሆነም ያውቃሉ፡፡ ግን እንደው “እከሌ ከባቡር ጋር ገመድ ጉተታ ገጠመ!” ሲባል ሰምተው ያዉቁ ይሆን፡፡ “ኧረ በጭራሽ… እንዴት ሆኖ?” የሚል ምላሽ ከሰጡ ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል ድረገጽ “ይቆዩ ኦክሳና ኮሼሌቫን ላስተዋውቅዎት” ይልዎታል፡፡
ሩሲያዊቷ ኦክሳና የክብደት ማንሳት ስፖርተኛ ናት፡፡ በከተማዋ ያለውን ቀላል ባቡር ለምን ገመድ ጉተታ አልገጥመውም ብላ የተነሳች፡፡ እናም 20 ሺ ኪሎ ግራም ክብደት ያለውን በኤሌክትሪክ ሀይል የሚንቀሳቀስ የከተማ ቀላል ባቡር በገመድ ጠፍራ ካሰረች በኋላ “ያዝ እንግዲህ ባቡሩ” ብላ በመጎተት 5 ሜትር ያክል ወደፊት አንደርድራው  የሀገሯን ክብረ ወሰን ለመጨበጥ ችላለች፡፡ ባቡሩ ላይ የታሰረውን ገመድ በትከሻዋ አንግታ ወደፊት የጎተተችው ኦክሳና ምንም እንኳ ገመድ ጉተታውን በድል ብትወጣውም ፍላጎቷ ግን ባቡርን መግጠም አልነበረም፡፡ ይልቁንም ከባቡሩ ክብደት ከ2 ሺ ኪሎ ግራም በላይ የሚበልጥ አውሮፕላን መጎተት ነበር ህልሟ፡፡
“ምን እባካችሁ እኔ እንኳን አውሮፕላን መጎተት ነበር የፈለግኩት… ግን ሳይሳካ ቀርቶ ያው እንዳያችሁት ባቡር ጎትቻለሁ… ደግሞ ያን ያክል ከባድ አልነበረም ምናልባት አንድ ብቻ መሆኑ በቀላሉ እንዲረታ ሳያደርገው አልቀረም… በቀጣይ ሶስትም አራትም የሚሆኑ ባቡሮችን ደርድሬ ነው ገመድ ጉተታ የምገጥማቸው” ያለችው ኦክሳና በሚቀጥለው አመት አውሮፕላን ጎትታ የአለምን ክብረ ወሰን ለመያዝ እቅድ እንዳላትም ተናግራለች፡፡ “መጀመሪያ ውስጥህ ስሜቱ ሊኖርህ ይገባል… ይሄንን ነገር እፈልገዋለሁ ወይስ አልፈልገውም ብለህ እራስህን መጠየቅ ይኖርብሃል… ቀድሞዉኑ የማትፈልገው ነገር ከሆነ ብትሞክረውም ስኬታማ አትሆንም” ስትልም ነው ኦክሳና የገመድ ጉተታ ስኬቷን ምስጢር ያካፈለችው፡፡

መቼም የከተማችን ቀላል ባቡር ከሰሞኑ መደበኛ አገልግሎቱን ሊጀምር እንደሆነ መስማትዎትን አንጠራጠርም፡፡ ያው ቀላል ባቡሩ ደግሞ በኤሌክትሪክ ሀይል እንደሚንቀሳቀስ ማወቅዎትንም እንደዛው፡፡ እናልዎት ወዳጃችን ምናልባት እርሰዎም አንድ ቀን እራስዎትን በደንብ በስፖርት አጠንክረው ባቡሩን ገመድ ጉተታ እገጥመዋለሁ የሚል ሀሳብ ካለዎት እርስዎ ሀሳብዎት እስኪማላና ለውድድሩ ዝግጁ እስኪሆኑ ድረስ ባቡሩም በጤና ደህና ሆኖ እንዲቆይዎት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉለት ልክ እንደራስዎ ንብረት ይጠብቁት በቡሩ በሚያልፍባቸው መንገዶች ላይም በተፈቀዶ ቦታዎች ተጠንቅቀው በማቋረጥ እራስዎትንም ከአደጋ ጥጠብቁ መልእክቴ ነው፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment