እናትነት፤ አንዲት እንስት ለ9 ወር በሆዷ ይዛ የቆየችውን
ጨቅላ በምጥ ስቃይ ወደ ምድር በምትቀላቅልበት ቅጽበት ይጀምራል፡፡ ታዲያ በእርግዝና ወራትም ይሁን በወሊድ ወቅት እናትም ጤና
ልጅም ጤና እንዲሆኑ ተገቢው የህክምና ክትትል እንዲሁም እውቀትና ክህሎቱ ባለው ሙያተኛ የማዋለድ ስራ መከናወኑ ግድ ነው፡፡
ይህ የወሊድ ነገር በአጥቢ አሳዎች ዘንድ እንዴት ባለ መልኩ
ይከናወን ባናውቅም መቼም ያው አሳ ሰው አይደለምና “ልወልድ ነው ብላ የአሶች ሆስፒታል ሄደች…” “እከሌ የተባለ አሳ አዋላጅ
ነርስ አሳ ነው” ሲባል ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ ነብሰጡሯ ዶሪና ሮዚን ግን “እኔን የሚያዋልዱኝ ሰዎች ሳይሆኑ አሳዎች ናቸው ብላለች” እንደ ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል
ድረገጽ ዘገባ፡፡
ዶሪና ሮዚን ነዋሪነቷን በአሜሪካ ሀዋይ ሆኖሉሉ ውስጥ
ያደረገች እንስት ናት፡፡ የዘጠኝ ወር ከ15 ቀን ገደማ ወይም የ38 ሳምንት ነብሰጡር የሆነችው ዶሪና፤ ከሰሞኑ ዩቲዩብ በተባለው
የማህበራዊ ትስስር ድረገጽ ላይ በተለቀቀ ቪዲዮ፤ የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ቀኔ ሲደርስ ያዋልዱኛል ካለቻቸው ዶልፊን በመባል
ከሚታወቁት የአሳ ዝርያዎች ጋር እየዋኘት ታይታለች፡፡
ዶልፊኖች ለሰው ልጆች በጣም ቀረቤታ ያላቸው፣ ለማዳና በሰው
ላይ ጉዳት የማያደርሱ አጥቢ የአሳ ዝርያዎች ሲሆኑ ያላቸውን ጭንቅላት በከፍተኛ ደረጃ በመጠቀምም በአለም ካሉ ፍጡራን፤ ሰውን
ጨምሮ፤ የሚስተካከላቸው እንደሌለ ይነገራል፡፡
ዶሪና ይህን ሃሳቧን ማሳወቋን ተከትሎ ‘ኬቲ ፓይፐርስ
ኤክትራኦርዲናሪ ብሪት’(British TV series Katie Piper's Extraordinary
Births)
በመባል የሚታወቀውና በእንግሊዝ ቴሌቪዥን ላይ የሚተላለፈው የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጆች አነጋግረዋታል፡፡ “አነስ ያሉ
የዶልፊን ወዳጅ የሆኑ ሰዎችን ነው እዚያ ያገኘሁት… ግን ደግሞ በጣም ደስተኞች ናቸው፤ ዶሪናም ዘና ብላ ነበር” ያለችው
የፕሮራሙ አዘጋጅ ኬቲ ፓይፐር “ነገሩ አይን የሚከፍት አይነት ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝም” ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡
![]() |
katie piper |
ምንም
እንኳ ዶሪና ልጄን የምገላገለው በዶልፊኖች አዋላጅነት ነው ብትልም ታዲያ ነገሩ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል የህክምናው
ጠበብቶች ከወዲሁ አስጠንቅቀዋል፡፡ “ለሰው ልጆች ካላቸው ቀረቤታ እና እንደልብ በየቦታው መገኘታቸው ዶልፊኖችን ተወዳጅና
እምነት የሚጣልባቸው ፍጡሮች አድርገን እንድናስባቸው አድርጎናል” ስትል ዲስከቨሪ መጽሄት ላይ የጻፈችው ክሪስቲን ዊልኮክስ “እዚች
ጋር ግን ትንሽ ቆም ብለን ማሰብ ሳይጠይቀን አይቀርም… ዶልፊኖች እንደማንኛውም እንስሳ የባህር እንስሳ የሆኑ አሳዎች
መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም! ደግሞም የተለያዩ ጉዳቶችን ሲያስከትሉ የታዘብንባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉም መረሳት የለበትም!”
ስትል ነው ጉዳዩን አስመልክታ ስጋቷን ያሰፈረችው፡፡
“እንበልና
ዶልፊኖቹ ድንገት ቢቆጡና ዶሪና ላይ አሊያም የሚወለደው ህጻን ላይ ጥቃት ለማድረስ ቢሞክሩ ምንድነው የሚደረገው…!? 200 ኪሎ
ገደማ ከሚመዝነውና በብርሀን ፍጥነት ከሚጓዘው አሳ እናትየውንም ሆነ ህጻንኑን እንዴት ነው መከላከል የሚቻለው…!? በዚያ ላይ
ደግሞ ከእናትና ልጁ በተሻለ ባህሩ ቤትነቱ ለዶልፊኑ እንደሆነም
መዘንጋት የለበትም!” ስትልም ነው ክሪስትን የጉዳዩን አደገኝነት የገለጸችው፡፡
እንግዲህ
ነብሰጡሯ ዶሪና ዶልፊኖች እንደሚያውልዷት ነው የተናገረችው ጸሀፊዋ ክርስቲን ደግሞ “ነገሩ አደጋ አለው!” እያለች ነው፡፡ ሁሉም
ነገር የዶሪን መውለጃ ቀን ደርሶ የሚታይ መሆኑ እንዳለ ሆኖ… “ኧረ የለም ይሄን ነገር እኛ አንችልም፤ እኛ እኮ አሳዎች ነን”
ወይም “ደግሞ ለማዋለድ… ኧረ ምንም ስጋት እንዳይገባችሁ በብቃት ነው የምንወጣው” የማለት እድሉን አግኝተው አንደበት
በኖራቸውና ዶልፊኖቹ መናገር ቢችሉ ግልግል ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ግን አንድም እናት ህይወት ለመስጠት ብላ መሞት የለባትምና ዶሪና
ሀሳቧን ብትቀይር መልካም ነው “አይ…” ካለች ደግሞ የምታዋልዷት ዶልፊኖች አደራችሁን ብያለሁ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ
ኤም 96.3
No comments:
Post a Comment