Wednesday, September 2, 2015

ተጠርጣሪው ግለሰብ በፈጸመው ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የክስ ሂደቱን የተመለከቱት ዳኛም ለጥፋቱ መቀጫ ይሆነው ዘንድ በትዳር ይቀጣ ሲሉ ፈርደዋል፡፡



የልጅት ፍቅር አነሁልሎት “ያፈቀርኳትን ልጅ ዝንብ እንኳ ያለኔ ፍቃድ አያርፍባትም” ያለ የሚመስለው አቶ ጆስተን በንዲ ከለታት በአንዱ ቀን ልቡ እብጥ ብሎበት የፍቅረኛውን የቀድሞ ወዳጅ እንካ ቅመስ ሲል በቡጢ መንገጭላውን አናግቶ እንዳይሆኑ እንዳደረገው አቶ ጆስተንን ፍርድ ቤት እንዲቆም ያደረገው የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡ ለጠብ የተጋበዘበትና ሰው የደበደበበት ምክንያቱም “የወደድኳትን ልጅ ዘልፈሃታል” በሚል እሰጣገባ ምክንያት ተነሳስቶ እንደሆነም ያትታል፡፡

የክስ መዝገቡን ሲመለከቱ የነበሩት የስሚዝ አውራጃ ፍርድ ቤት ዳኛ ራንዳል ሮጀርስ ክሱን በደንብ አጢነው ለተከሳሹ ለአቶ ጆስተን በንዲ ቅጣት ይሆናሉ ያሏቸውን አማራጮች አስቀምጠው “በል እንግዲህ ምርጫው ያንተ ነው… የትኛው ቅጣት ይሻልሃል?” ሲሉ “አስራ አምስት ቀናትን ከፍርግርግ ብረት ጀርባ በዘብጥያ ውስጥ ሆነህ ብታሳልፍ ይሻልሃል ወይስ እንዲህ ለጸብና ሰው ለመደብደብ ወንጀል ያደረሰችህን ጉብል ኤልዛቤት ጄይንስን በቀጣይ ሰላሳ ቀናት ውስጥ አግብተህ፤ ከመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የተወሰደ አንድ ጥቅስ በቀን ለሀያ አምስት ጊዜ ያክል ደጋግመህ እየጻፍክ… እንዲሁም ደግሞ የምክር አገልግሎት እየተሰጠህ መኖርን ትመርጣለህ?” የሚሉ ምርጫዎችን አስቀምጠውለት “እህሳ ተከሳሽ ምን ትላለህ?” ሲሉ ጥያቄ ሰንዝረውለታል፡፡
“እንዲህ ነችና ቅጣት! ያውም የምወዳትን ልጅ እንዳገባ!? ይሄ ተገኝቶ ነው እንዴ!?” ብሎ በልቡ ጮቤ ሳይረግጥ የማይቀረው ተከሳሹ፤ በቴክስሳክ ግዛት ታይለር ውስጥ ነዋሪ የሆነው የ20 አመቱ ጆስተን “ሁለተኛው ቅጣት ይበጀኛል! የ19 አመቷን ኮረዳ ፍቅረኛዬን ኤልዛቤትን አግብቼ አለሜን እያየሁ ብኖር ይሻለኛል” ሲል ለፈጸመው የሰው ድብደባ ወንጀል ቅጣት እንዲሆነው ትዳርን መምረጡን ነው ሮይተርስ በድረገጹ ያስነበበው ዘገባ ያሰፈረው፡፡  
ምንም እንኳን እንዲህ በአስቸኳይ ሶስት ጉልቻ የመመስረት እቅድ ባይኖራቸውም ቅሉ በዳኛው ውሳኔ መሰረት መጋባት ግድ የሆነባቸው ጥንዶቹ ነገሩን ተገደው መፈጸማቸውን አልወደዱትም እንጂ መተሳሰሪያ የትዳራቸው ክር መቋጠሩ አስደስቷቸዋል፡፡ ሙሽሪት ኤልዛቤት “ያሰብነውን አይነት ሰርግ ደግሰን ልንሞሸር እንደማንችል ይሰማኛል፤ ሌላው ቀርቶ ነጭ ቀሚስ እንኳ የለኝም እኮ…” ብላለች፡፡ ጥንዶቹ እዛው ፍርድ ቤት ውስጥ ጋብቻቸውን አስመልክቶ የተነሷቸውን ፎቶዎችም እነሆ ጋብቻችን ሲሉ በማህበራዊ ድረገጾች አጋርተዋል፡፡
በዳኛው ውሳኔ ቅር የተሰኙት የሙሽሪት አባት “ይህ ተገቢ ፍርድ አይደለም… ዳኛው እንዲህ ሰውን አስገድደው እንዲያገባ ማድረግ አይችሉም! ይህ የዳኝነት ስህተት ሳይሆን አይቀርምና አጣራኋለሁ” ሲሉ ነው በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡
ወዳጄ እንግዲህ ነገሩን “ወይ ጉድ… እንዲህም ብሎ ፍርድ አለ እንዴ ጎበዝ!? እያሉ በአግራሞት ይለፉት፡፡” ወንጀለኛው ጆስተን ሰው ደብድቦ መቀጮ እንዲሆነው ትዳር ቢፈረድለትም አደራዎትን እርስዎም የትዳር አጋሬን አገኛለሁ በሚል ተስፋ ሰው ጫፍ ላይ እንዳይደርሱ፡፡ ያሰቡትን ትዳር ማግኘትዎት ቀርቶ የወንጀልዎት ክብደትና ቅለቱ ተጣርቶ ህግ በሚያዘው መሰረት በዘብጥያ ቀናትን አሊያም ወራትን እንዲየሳልፉ ቅጣት ይፈረድብዎታል እንጂ ትዳርን በወንጀል ፈጽሞ አያገኙትም፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment