ወዳጄ እሜቴ ማሪያ ኮልታኮቫን ይተዋወቋቸው፡፡ መኖሪያቸውን በሩሲያ ቤልጎሮድ ከተማ ያደረጉና ሰማይ ላይ
የደነሱ ሩሲያዊት የ93 አመት የእድሜ ባለጸጋ አዛውንት ናቸው፡፡ በእርግጥ “ሰማይ ላይ ደግሞ እንዴት ተብሎ ነው የሚደነሰው!?
ክንፍ አላቸው እንዴ አዛውንቷ!?” የሚል ጥያቄ መሰንዘርዎት አይቀርምና ነገሩ እንዴት እንደሆነ ደርዝ ደርዙን አስይዤ እንድንነግርዎት
ሜትሮ ድረገጽን አገላብጫለሁ ምላሹን እነሆ፡፡
እናልዎት ወዳጄ ምን መሰልዎት፤ ሩሲያዊቷ እመት ማሪያ ሰማይ ላይ መደነስ ያስቻሏቸው ተፈጥሮ የለገሰቻቸው
ክንፎች ኖረዋቸው አይደለም፡፡ ይልቁንም የእንጀራ ገመዳቸው ከሰማይ ጋር ተቋጥሮ በአውሮፕላን ወዲያ ወዲህ እያሉ የሚኖሩ ሰዎች
አንዳንድ ጊዜ ከሰማይ ወደ ምድር ቁልቁል እየተምዘገዘጉ የሚወርዱበትን ዣንጥላ ወይም በእንግሊዘኛው ስሙ ፓራሹት ተጠቅመው ነው
ሰማይ ላይ ሲደንሱ የዋሉት፡፡
“ምን እድሜዬ ቢገፋ ሰማይ ላይ ለመደነስ ገና አንዲት ፍሬ ልጅ ነኝ… ደግሞ ለፓራሹት ዝላይ ኧረዲያ እቴ!”
ያሉ የሚመስሉት የ93 አመት አዛውንቷ እማማ ማሪያ “ከሰማይ ወደ ምድር ተወርውሬ በዣንጥላ የምወርደው ያኔ እንደ ፈረንጆቹ
አቆጣጠር በ1945 ዓ.ም. በሁለተኛው የአለም ጦርነት ማገባደጃ አካባቢ አብረን ዘምተን ሳለ የሩሲያ ጦር ከጠላት ሀገር ጃፓን
ጦር ጋር ባደረገው ውጊያ የጠላትን ጦር ሲፋለምና ሲተጋተግ ህይወቱ ያለፈው ወንድሜን ለመዘከር” ነው ብለዋል፡፡
የቀዶሞዋ ሶቬት ህብረት ጦር ባልደረባና የአሁኗ ጡረተኛ እማማ ማሪያ በህይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በሰማይና
በምድር መሀል ዣንጥላ ላይ ተንጠልጥለው እየተንሳፈፉ ወዲያ ወዲህ ሲሉ የነበራቸውን ቆይታና ስሜት አስመልክተው ተጠይቀው ሲመልሱም…
“ያንተ ያለህ! እንዴት ያለ የማይታመን ነጻነት መሰላችሁ… በለው…በለው… ሰማይ ላይ ሽር ብትን እያልኩ ስደንስ ነበር እኮ.. ይሄ
ብቻ ደግሞ እንዳይመስላችሁ ደመናዎችን እንዲህ አፍንጫዬ ስር ቀርበውልኝ እየተመለከትኩም በነሱ ላይ ስራመድና ሳጣጥማቸው ነበር”
ብለዋል፡፡
“እድሜዬ ቢገፋም ቀላል ሰው እንዳልመስላችሁ.. ከፍተኛ የሆነ ጉልበትና ጥንካሬ አለኝ፤ ያኔ በጦርነቱ ጊዜ
ያካበትኩት ነው ታዲያ እ..” ያሉት ጡረተኛዋ እማማ ማሪያ “ይሄ
ጉልበቴና ጥንካሬዬ በህይወቴ የሚያጋጥሙኝን ነገሮች ሁሉ በብቃት እንድወጣቸው እያገዘኝ ነው” ሲሉም ነው ቆፍጠን ብለው የተናገሩት፡፡
“የሰማይ ላይ ዳንሴን በዚህ ብቻ የማበቃ አይመስለኝም… 94ኛ አመቴን ሳከብርም ሳልደግመው አልቀርም” ያሉት እማማ ወደ ጠፈር
የመጓዝ ህልም እንዳላቸውም ነው ለጠያቂዎቻቸው ሹክ ያሉት፡፡
ወዳጄ እማማን እንዴት ተመለከቷቸው ታዲያ! በአድናቆት እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ታዲያ ልክ እንደ እማማ
ማሪያ እድሜ ያልበገረው ወኔና የመስራት ብቃት ይዘው በየቤቱ ያሉ አረጋውያን እዚህ እኛ ጋርም አይጠፉምና ትኩረት እንስጣቸው መልእክቴ
ነው፡፡
ዳንኤል
ቢሠጥ
ለአዲስ
ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3
No comments:
Post a Comment