ወዳጄ የቻይና
ገበሬ እያንጎራጎረ ሞፈር ጨብጦ፤ ጅራፍ እያወናጨፈ ማረስ ብቻ ሳይሆን ‘ህም’ ‘ፍፍ..’ የሚሉ ድምጾችን እያወጣ እጅና እግሮቹን… አንዳንዴም
ዱላ ቢጤ በማወናጨፍም የተካነ ነው፡፡ እንዲያው በተለምዶ እዚህ እኛ ሀገር ለቻናውያን ለየት ያለ ግምት አለን፡፡ በዚህ ማርሻል
አርት በሚባለው የስፖርት አይነት፤ እኛ እንዲሁ በዘልማድ ‘ካራቴ’ እያልን በምንጠራው ስፖርት የተካኑ እንደሆነ ነው ብዙዎቻችን
የምናስበው፡፡
“እውነትም ይህ
እሳቤያችሁ ትክክል ሳይሆን አይቀርም” ያለ የሚመስለው ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ በቻይና ጋንዢ ዶንግ መንደር ውስጥ ያለ
እያንዳንዱ ገበሬ በዚህ እነሱ ኩንግ ፉ ሲሉ በሚጠሩት ማርሻር አርት ስፖርት የተካነ ነው የሚል መረጃ አስነብቧል፡፡
ኩንግ ፉ ለቻይናውያን እንዳለ ማለት በሚያስደፍር መልኩ ባህላዊ ስፖርታቸው ነው፡፡
ይህ ስፖርት እዚህ እኛ ሀገርም ስልጠናውን በወሰዱ ሙያተኞች በየሰፈሩ ቻይናውያን ስያሜዎችን ይዞ ‘እከሌ ውሹ ኩንግፉ’ ‘እገሊት
ታይገር’ ‘ማንትስ ድራጎን’ የሚሉ መጠሪያ ባላቸው ተቋማት ስልጠናው መሰጠት ከጀመረ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡
እናልዎት ወዳጄ
በማእከላዊ ቻይና በቲያንዡ ተራሮች ተከብባ የምትገኘው ጋንዢ ዶንግ መንደር ውስጥ ያሉ ገበሬዎች ሁሉም የማርሻል አርስ ስፖርት
ጠበብ ናቸው፡፡ የእርሻ ስራቸውን አከናውነው በምትተርፋቸው ጊዜ ይህን ስፖርት የማዘውተር ልማድ አላቸው፡፡
እያንዳንዱ ገበሬም
የግሉ የሆነ የዚሁ የኩንግ ፉ ስፖርት ፈጠራ ባለቤት ሲሆን አንዳንዴ ልምምዳቸውን ልክ እዚህ እኛ ጋር ትግል እንደምንለው በጋራ
በጋራ እየሆኑ በመግጠምም ያከናውኗሉ፡፡ ለባህላቸው ልዩ ትኩረት የሚሰጡት የዚህ መንደር ገበሬዎች ‘እምቢ ለባህላችን’ ብለው
ከውጪው አለም ለሚመጡ ባህሎች በራቸውን ከዘጉ ቆይተዋል፡፡
ይህ የስፖርት ባህል በመንደሩ ገበሬዎች ዘንድ እንዴት መዘውተር
እንደጀመረ እርግጠኛ መረጃ ባይኖርም የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ግምቶቻቸውን ያስቀምጣሉ፤ “ድሮ ድሮ የአካባቢው ነዋሪዎችና ከብቶቻቸው
በተደጋጋሚ በአውሬዎች ጥቃት ይደርስባቸው ነበር.. ይህን ለመከላከል ሲባልም ከእያንዳንዱ ቤተሰብ ፈርጠም ፈርጠም ያሉ ወጣቶች ይመረጡና
መንደራቸውን ከአደጋ መከላከል የሚያስችል መላ እንዲፈጥሩ ይላካሉ..
እነዚህ ወጣቶች ታዲያ የድራጎን፣ የእባብ፣ የነብርና የአቦሸማኔን ስልት በማስመሰል እንቅስቃሴዎችን አጥንተው በመፍጠር ለቤተሰቦቻቸው
አስተማሩ፤ ቤተሰቦቻቸውም ይህን ክህሎት በተለያየ መንገድ በማጥናት ኩንግ ፉ ስፖርት የተለያየ ዘርፍ እንዲኖረው አስቻሉ” የሚለው
አንደኛው ግምት ነው፡፡
ሁለተኛው ግምት ደግሞ “የመንደሩ ሰዎች በሰፈሩበት አካባቢ
ካሉ አጎራባች መንደሮች በየጊዜው ዝርፍያ ሲፈጸምባቸው ጊዜ “አልበዛም እንዴ አሁንስ… ኤጭ!” ሲሉ ሰዎችን መርጠው ራሳቸውን ከአደጋ
የሚከላከሉበትን መንገድ እንዲያሰለጥኗቸው አደረጉ.. ልምዳቸውንም ለቤተሰቦቻቸው እያካፈሉ እዚህ ደርሰዋል” የሚል ነው፡፡
የሆነው ሆኖ እውነተኛው ታሪክ ከጊዜ ርዝመት ጋር ተያይዞ
ቢጠፋም የመንደሩ ነዋሪ ግን ባህሉን እንደጠበቀ ይዞ እዚህ ደርሷል፡፡ በመንደሩ ባሉ 123 ቤተሰቦች እንዳለ ኩንግፉ ስፖርት ይዘወተራል፡፡
ዛሬ ዛሬ ወጣቶች ለተሸለ ህይወት ወደ ከተማ መኮብለል ቢጀምሩም በመንደሩ ያሉ ሴቶች ሳይቀሩ የኩንግ ፉ ስፖርት ባህላቸውን ሁሌም
እየተገበሩት መኖር ቀጥለዋል፡፡
ወዳጄ እንግዲህ የኩንግ ፉ ስፖርት ወጣቶችን በስነ ምግባር
በማነጽ ትልቅ ሚና የሚጫወት ከመሆኑም ባለፈ ለጤና ጠቃሚ፤ ብሎም ራስን ከአደጋ ለመጠበቅ የሚስችል ስፖርት
ነውና እርስዎም ሆኑ ልጆችዎት ስፖርቱን ተቀላቅለው ‘ህም’ ‘ሆይ’ ‘ፍፍፍ..’ ቢሉ ያተርፋሉ፡፡ ሌላውና ትልቁ ነገር ግን ከጋንዢ
ዶንግ መንደር ገበሬዎች መማር ያለብን ባህላችንን ጠብቀን በማቆየት ያልተበረዘ ያልተከለሰ ሀገራዊ ባህልን ለትውልድ ማስተላልፍን
ነው፡፡
ዳንኤል
ቢሠጥ
ለአዲስ
ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3
No comments:
Post a Comment