Wednesday, September 23, 2015

‘ናሩቶ’ ዝንጀሮው “የፍትህ ያለህ!.. መብቴን አትንፈጉኝ!” ሲል ፍርድ ቤት ቆመ

በዳንኤል ቢሠጥ

‘ናሩቶ’ ማካኩ በመባል ከሚታወቁት የአህጉረ እሲያ ዝንጀሮዎች የሚመደብ ዝንጀሮ ነው፡፡ መኖሪያውን በሀገረ ኢንዶኔዢያ ያደረገ ዝንጀሮ፡፡ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2011ዓ.ም.  ታዲያ ‘ናሩቶ’ የእለት ተእለት ህይወቱን በሚመራበት ጫካ ሳለ፤ ዴቪድ ጄ ስላተር የተባለ ፎቶ ግራፍ አንሺ ካሜራወን ይዞ በጫካው ይገኛል፡፡ ዴቪድ ካሜራውን አስቀምጦ ዘወር ሲልለት ታዲያ… ምናልባትም ቢጠየቅ- “እኔ ፎቶ ግራፍ የማንሳት ፍቅር ገና የሶስት ወር ጨቅላ ሳለሁ ነበር አእምሮዬ ውስጥ ይመላለስ የነበረው” የሚል ምላሽ ሳይሰጥ የማይቀረው ‘ናሩቶ’ የዴቪድን ካሜራ ላፍ አድርጎ እራሱን ፎቶ ደጋግሞ ያነሳል፡፡ እንግዲህ በዘመንኛው አጠራር ‘ናሩቶ’ እራሱን ‘ሰልፊ’ አነሳ እንደማለት ነው፡፡
እንግዲህ ጉዳዩ የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው፡፡ ፎቶ አንሺው ዴቪድ ካሜራውን ከ‘ናሩቶ’  ተቀብሎ ሲፈትሸው ‘ናሩቶ’ ያነሳቸውን ምስሎች ይመለከታል፡፡ ከፎቶዎቹ መካከልም ‘ናሩቶ’ ልክ እንደ ድሮ ፎቶ “ትንሽ ፈገግ… ትንሽ ፈገግ” የተባለ ይመስል ፈገግ ብሎ ያነሳውን ፎቶ ይይዝና በተለያዩ ድረገጾች ላይ ‘ናሩቶ’ እራሱን ያነሳው ፎቶ በማለት ለጥፎት ገንዘብ ማግኛ ያደርገዋል፡፡  
ባሳለፍነው አመት ግን “የዚህ ፎቶ ባለቤት አንተ ሳትሆን ናሩቶ እራሱ ነውና አንተ ገንዘብ ልትሰበስብበት አትችልም፤ ፎቶው የህዝብ ነው፤ ማንም ሰው እንደፈለገ ሊጠቀምበት ይችላል” ሲል ዊኪሚዲያ የተባለ ድረገጽ ያለ ዴቪድ ፍቃድ የ‘ናሩቶ’ን ፎቶዎች ያሰራጫል፡፡ ይሄኔም ዴቪድ “የቅጂ መብቱ የኔ ነው፤ ያለኔ ፈቃድ የ‘ናሩቶ’ ፎቶዎች የህዝብ ናቸው ተብለው መለቀቅ የለባቸውም፤ ‘ናሩቶ’ እራሱን ፎቶ ቢያነሳም ካሜራውን ያሰናዳሁት እኔ ነበርኩ፤ በዚያ ላይ ደግሞ የቅጂ መብትም ከአገረ እንግሊዝ ተችሮኛል” ብሎ ክስ መስርቶ ፎቶዎቹ ከድረገጹ ላይ እንዲነሱ ጥረት ቢያደርግም ድረገጹ ግን “አንተ ባላነሳኸው ፎቶ አያገባህም!” የሚል ምላሽ ሰጥቶ እምቢ ብሎታል፡፡ እስከዛሬም ክርክሩና እሰጣገባው እንደቀጠለ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ ባለበት ሁኔታ ነው እንግዲህ ከሰሞኑ ‘ናሩቶ’ ህጋዊ የፎቶው ባለቤት ነው ሲሉ መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉ የእንሳሳት መብት ተሟጋቾች ፍርድ ቤት ቀርበው አዲስ ክስ የመሰረቱት፡፡ ‘ሰዎች ተገቢ ለሆነ የእንስሳት እንክብካቤ’ ወይም በምህጻረ ቃሉ ‘ፒኢቲኤ’ የሚል ስያሜ ያላቸው የእንስሳት መብት ተሟጋቾቹ በአሜሪካ ሳን ፍራንሲስኮ በሚገኝ የፌደራል ፍርድ ቤት ነው ፍትህ ለ‘ናሩቶ’ ሲሉ በዴቪድ እና በድርጅቱ ላይ ክስ የመሰረቱት፤ እንደ ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል ድረገጽ ዘገባ፡፡
“እኛ እያልን ያለነው የአገረ አሜሪካ የቅጂ መብት የእንስሳቶችን የባለቤትነት መብት የሚገድብ አይደለም፤ ስለዚህም ፎቶውን ያነሳው ዴቪድ ሳይሆን ‘ናሩቶ’ እራሱ ነውና የቅጂ መብቱም ለራሱ ለ‘ናሩቶ’ ነው የሚገባው” ሲሉ ለመሟገት ፍርድ ቤት የቆሙት የእንስሳት መብት ተሟጋቾቹ ፎቶው የሚስገኘው ገቢ ‘ናሩቶ’ እራሱና ሌሎች የማካኩ ዝንጀሮ ዝርያዎች እንዲጠቀሙበት ነው ፍላጎታችን ብለዋል፡፡

ወዳጄ የደላው ዝንጀሮ እንግዲህ እሱ ጫካ ተቀምጦ ሰውን እያካሰሰ ነው፡፡ ግን እንዳው ጉዳዩን ሰምቶ “ምን ትላለህ?” ተብሎ ቢጠየቅና ምላሽ በሰውኛ አንደበት መስጠት ቢችል፤ “ወይ ስራ ማጣት… ሰው እንዴት እንዴት ማሰብ ጀምሯል ጃል… በእርግጥ እኛን ለመርዳት ማሰባቸው የሚደገፍ ቢሆንም እንደኔ ያለ አንድ ዝንጀሮ ምንም ሳያውቀው ሲነካካ በአጋጣሚ ላነሳው ፎቶ… ይገባኛል! አይገባህም! እያሉ ስንት ፍትህ ያጡ ሰዎች ሊዳኙበት የሚችሉትን የፍርድ ቤት ሰአት መሻማታቸው እንዲያው በኛም ሳይቀር ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ነው” ብሎ የሚመልስ ይመስለኛል፡፡  

No comments:

Post a Comment