ወዳጄ መቼም ማንም ሰው ቢሆን ችግር ገጥሞት፤ የውስጥ ስሜቱ ገንፍሎ፤ በውሀ መልክ በአይን በኩል እንባ ሆኖ ሲወርድ
አጠገቡ ሆኖ “አይዞህ!” ብሎ የሚያጽናናው ሰው ይፈልጋል፡፡ በተለይም ደግሞ ይህ ነገር በሴቶች ዘንድ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን
በርካታ እንስቶች በተለያዩ ምክንያቶችና አጋጣሚዎች እንባቸውን እንዲቀድም የሚያደርግ ነገር ሲገጥማቸው “አይዞሽ!” የሚላቸው ሰው
ከጎናቸው ሲሆን ቶሎ ሲጽናኑ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ እዚህ እኛ ሀገርና በሌሎች የውጪው አለም ሀገራትም የሚታይ ጉዳይ
ነው፡፡ ከጃፓን በስተቀር፡፡
“እንዴት ማለት? ጃፓናውያን የምታለቅስ ሴት አያባብሉም ማለት ነው!?” የሚል ጥያቄ ማንሳትዎት አይቀርምና ከኦዲቲ
ሴንትራል ድረገጽ ያገኘውትን ምላሽ እነሆ፡፡ እርግጥ የዛሬን አያድርገውና ጃፓናውያኑ የምታለቅስን ሴት ብቻ ሳይሆን እንደው
ልታለቅስ ያሰበችዋን እራሱ ሳያባብሉ የማያልፉ ሰዎች ሆነው ኖረው ይሆናል፡፡ ዛሬ ላይ ግን ይህ ነገር ተረት ሳይሆን
አልቀረም፡፡ ምክንያት ቢሉ እንባ ማበስ አዲሱ የጃፓናውያን ሸበላ ወንዶች የገቢ ምንጭ፤ ወይም በዘመኑ ቋንቋ ቢዝነስ
ሆኖላቸዋልና ነው፡፡
እናም አንዲት ጃፓናዊት እንስት የስራዋ ነገር፤ ከህይወቷ ጋር ተዳምሮ፤ እረፍት ቢነሳትና “እንደው ተነስተሸ ስቅስቅ
ብለሽ አልቀሰሽ ይውጣልሽ” የሚል ስሜት ተጠናውቷት እንባዋ ዱብ ዱብ ማለት ቢጀመር ካልከፈለች በስተቀር የሚባብል የማግኘቷ
ነገር አጠራጣሪ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እንባ ማበስ ለጃፓናውያን ወጣት ወንዶች የስራ አማራጭ ሆኖ የቀረበ የገቢ ምንጭ ነውና
ነው፡፡
እንባ ማበስ፤ በጃፓንኛው ‘ልኬሜሶ’ ወደ አማርኛችን ስናመጣው ‘መልከ መልካም ሸበላ’ የሆኑ ጃፓናውያን ወንዶች
በስራዋ ውጥርጥር ያለችና እዛም እዚህም እያለች የሩጫ ህይወትን የምትመራ ሴት፤ በከፋትና እንባ በቀደማት ቀን “አይዞሽ! እኔ
አለሁልሽ!” እያሉ በጃፓን ገንዘብ 7 ሺ 900 የን፤ በኛ ሲሰላ 1300 ብር ክፍያ የሚሰሩት የማባበል ስራ ሆኖ ነው ጃፓን
ላይ የተወለደው፡፡
አልቅሽ.. አልቅሽ.. ያላት ጃፓናዊት ሴት ስልኳን አንስታ ብቻ፤ ለዚህ ስራ ከተዘጋጁ 7 መልከ መልካም ወንዶች
አንዱን መርጣ፤ መጥቶ ያባብለኝ ብላ ለድርጅቱ ታሳውቃለች፡፡ የተመረጠው ጉብልም የምትሰራበት ቦታ ድረስ ይመጣና እሷ ስታለቅስ
እሱ እንባ የማበሱን ስራ ይሰራል ማለት ነው፡፡ ህጋዊ እውቅና ያለው ‘የእንባ ሀኪሙ’ ጉብል በቦታው ከመድረሱ በፊት ለቅሶ
ጀምራ ከጠበቀችው ደግሞ በቀጥታ እንደመጣ እንባዋን እየጠራረገ አይዞሽ እሺ!... አይዞሽ!!.. አይነት ቃላትን በመጠቀም
የማባበሉን ስራ ይያያዘዋል፡፡ አልቅሽ.. አልቅሽ.. ብሏት እንባ ለደረቀባት እንስትም ሸበላው ችግሯን በእንባ እንድታስተነፍሰው
የሚያደግ ፊልም ከፍቶ እንድትንሰቀሰቅ የማድረግ ሀላፊነት አለበት፡፡ ከዛም እንባ ማበሱን ይቀጥላል፡፡
እንባ አባሽ ፈላጊ እንስቶች ታዲያ ያሻቸውን አይነት ባህሪ ያለው ወንድ እንዲመርጡም አማራጮች ተመቻችቶላቸዋል፡፡
ታናሽ ወንድም፣ ምሁር፣ ቦዘኔ፣ ጎልማሳ እና ሌሎችም አማራጮች በዝርዝር ነው የቀረቡላቸው፡፡ “እዚ ቶኪዮ ውት ያሉ ጃፓናውያን
ሴቶች በስራ ቦታቸው ላይ በከፍተኛ ውጥረት ነው የሚኖሩት” የሚለው የዚህ ስራ ሀሳብ አመንጪ አቶ ሂሮኪ ቴራይ፤ “እናም ይሄ
ውጥረት ብዙ ጊዜ የሚጠናቀቀው እንባ በመራጨት ነው፤ እኛ ደግሞ ለዚህ መፍትሄ ይዘን መጥተናል፡፡ ድርጅታችን ያሉት ሰባት እንባ
አባሽ ሸበላዎች ስልክ ብቻ ነው የሚጠብቁት፡፡ ሀሎ እንደተባሉ በቦታው ከተፍ ብለው በጥሩ ቃላት እያባበሉ እንባ የማበስ
ስራቸውን ያከናውናሉ” ሲል ነው የስራ ፈጠራውን አስመልክቶ የተናገረው፡፡
የስራ ፈጠራ ሀሳቡ በብዙዎች ዘንድ ‘በጣም ሀሪፍ ሀሳብ ነው!!’ የሚል ምላሽ እያስተናገደ ሲሆን የስራውን መጀመር
የሚገልጸው ድረገጽ ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ በርካቶች የ‘አባብሉኝ!’ ጥያቄያቸውን እያቀረቡ እንደሆነ የሚናገረው ሂሮኪ ቴራይ፤
ሰዎች ነገሩን ቀልድ ነው ብለው እንዳያስቡና ስራ መሆኑን እንዲያውቁም ነው ያሳሰበው፡፡ ‘ልኬሜሶ’ እንባ እንባ ላላቸው ሴት ሰራተኞች
ታስቦ የተፈጠረ ቢሆንም ታዲያ ካገኘው ተቀባይነት አንጻር በተለያዩ ቦታዎች፤ በብዙ ዘርፍ ሊስፋፋ እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ወዳጄ ይህን ስራ እንዴት አዩት ታዲያ እ…? እንባ ማበሱን!? “እንዲህም ብሎ ስራ… ወይ ዘንድሮ!” የሚል አግራሞት
አንደሚፈጥርብዎት አንጠራጠርም፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ለስራ ፈጣሪዎቹ የገቢ ምንጭ መሆን ችሏል፡፡ እናም ወዳጄ እንባ ማበስ ባይሆንም
እርስዎም እንዲህ ለብዙዎች ችግር መፍትሄ የሆነ ስራ ቢፈጥሩ በሁለት መንገድ ስኬታማ ይሆናሉ፤ አንድም የሰው ችግር አቃልለው…
አንድም የራስዎትን ገቢ ማግኛ ፈጥረው፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍኤም 96.3
No comments:
Post a Comment