Friday, September 4, 2015

እነ እማማ የጃፓንን ሙዚቃ እንዱስትሪ ተቆጣጠሩት



የጃፓን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከሰሞኑ ለየት ያለ ክስተት አስተናግዷል፡፡ “ምን ገጠመው?” አይሉም ወዳጄ… ካሉ እሰየሁ ኢንዱስትሪው በእነ እማማ ሙዚቃ መጥለቅለቁን አልሰሙም ከሆነ እያነበቡ ወደታች ይውረዱ፡፡ እነ እማማ የለቀቁት ዘፈን የጃፓንን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አጥለቅልቆታል ይላል ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ያስነበበው ዘገባ፡፡ “እነ እማማ ደግሞ እነማን ናቸው?” የሚል ጥያቄ መሰንዘርዎት አይቀርምና ምላሹን እነሆ፡፡
የጃፓንን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በአጭር ጊዜ መቆጣጠር የቻለው፤ ከ33 የሚደርሱ ዘፋኞችንና ተወዛዋዦችን ያቀፈው የሙዚቃ ቡድን ኬቢጂ84 የሚል መጠሪያ አለው፡፡ የሙዚቃ ቡድንኑ ለየት የሚያደርገው ደግሞ ሁሉም የቡድኑ አባላት እድሜያቸው ከ80 የዘለለ አረጋውያን መሆናቸው ነው፡፡ ከቡድኑ አባላቶች መካከል በእድሜ ትልቋ አያት እማማ ሃሩ ያማሺሮ እድሜያቸው 97 አመት ሲሆን በአጠቃላይ የቡድኑ አባላት አማካይ እድሜ ደግሞ 84 አመት ነው፡፡
እነ እማማ ተሰባስበው ያቋቋሙት ይህ የሙዚቃ ቡድን መቀመጫውን በኦኪናዋ ግዛት ገጠራማ አካባቢ ኮሃማ ውስጥ ነው ያደረገው፡፡ ‘ኑና ጨፍሩ ኮሃማ ደሴት’ ወይም በእንግሊዝኛው ‘ከም ኦን ኤንድ ዳንስ ኮሃማ አይላንድ’ ሲሉ ያቀነቀኑበት የመጀመሪያ ነጠላ ዜማቸው በጃፓን የሙዚቃ ደረጃ ሰንጠርዥ የፊት ተሰላፊ በመሆን ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈላቸው እድሜ ጠገብ አባላትን ያቀፈው ኬቢጂ84 የሙዚቃ ቡድን ባገኙት አድናቆት እጅጉን ተገርመዋል፡፡
“ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነ ሰው ‘አይዶል’ ናቸው ብሎ ሲጠራን ሰምቼ ‘አይዶል’ ማለት ረዥም እድሜን የኖረና ሊሞት አንድ ሀሙስ የቀረው አዛውንት ማለት ነው ብዬ ነበር የገመትኩት” ሲሉ የሚናገሩት የሙዚቃ ቡድኑ አባል የ92 አመት የእድሜ ባለጸጋዋ እማማ ዲቫ ቶሚ ሜናካ፤ “ኋላ ላይ ግን ቶኪዮ ከተማ ላይ ‘አይዶል’ ማለት አዝናኝ አጫዋች ማለት እንደሆነ ነገረውኝ እፎይ አልኩ.. እንዴ እኔ እኮ ያሰብኩት በቃ ወደ ሞት በራፍ እየሄድኩ እንዳለሁ አድርጌ ነበር” ሲሉ የዝነኝነት ገጠመኛቸውን ተናግረዋል፡፡ 

“ቶኪዮ ላይ ልክ በቃ አለ አይደል ዝነኞች እንደሆንን ነው የተሰማን” የሚሉት ሌላኛዋ የቡድኑ አባል የ86 አመት አዛውንቷ እማማ ሂዴኮ ኬዳሞሪ፤ “የመድረካችን ታዳሚዎች ላይ እንዳለ ፊታቸው ላይ ደስታ ይነበባል… ይህ ደግሞ ልባችን እስኪጠፋ ድረስ እንድንዘፍን ብርታትን ሰጥቶናል፡፡ የኮሃማ ተወላጆች መሆናችን እድለኞች ነን… የዘፈን ግጥሞቻችን ስለ ተፈጥሮ፣ ባህር ላይ ግልብጥ ብለው ስለሚመጡት አሳ ነባሪዎች… ስለሚገለባባጡ ዶልፎኖችና ሌሎችም ተፈጥሮን የሚዳስሱ አይነት ናቸው” ብለዋል፡፡
መድረክ ላይ ሲጫወቱ ያላቸው ብቃትና ሞራላቸው እጅግ አስገራሚ የሆነው እነ እማማ፤ የሙዚቃ ቡድናቸውን ማንም ከ80 አመት በታች የሆነ ሰው እንዲቀላቀለው አይፈቅዱም፡፡ ኬቢጂ84 የሚለው ስያሜያቸውንም የወሰዱት በጃፓን ዝነኛ ከሆነውና የወጣቶች ስብስብ ከሆነው ኤኬቢ48 የሙዚቃ ቡድን ቀድተው ነው፡፡ የኤኬቢ ቡድን አባላት መጠሪያ ላይ ያለው 48 የሚል ቁጥር የቡድኑን አባላት ቁጥር የሚወክል ሲሆን እነ እማማ ያቋቋሙት ቡድን ላይ ያለው 84 ደግሞ የቡድኑን አባላት አማካይ እድሜ የሚወክል ነው፡፡
“ልቤ አሁንም ወጣት ነው!” የሚሉት እማማ ዲቫ እራሳቸውን ለመጠበቅ የቤት ውስጥ ስራዎችን -እንደ ቤት ማጸዳዳትና ወለል መጠራርግ እንዲሁም ምግብ ማበሳሰል ስራዎችን- እንደሚያከናውኑና ለጤናቸው የሚስማማ ምግብ እየመረጡ መመገብ ላይ ግን እምብዛም እንደሆኑ ነው የሚናገሩት፡፡ የኬቢጂ የሙዚቃ ቡድን አባላት መደረክ ላይ ሲያቀነቅኑና ሲወዛወዙ ያላቸው ብቃት እንዳለ ሆኖ ነገር ግን እድሜ እድሜ ነውና አካላቸው አንዳንዴ መለገሙ አልቀረም፡፡ ለዚህም ሲባል ከመድረክ ጀርባ ምርኩዞቻቸው፣ የደም ግፊት መመርመሪያዎችና የልብ ህክምና መስጫ መሳሪያዎች ሁሌም በተጠንቀቅ ሆነው ይጠብቋቸዋል፡፡
የበርካታ ሙዚቃ አፍቃሪያን አይን ማረፊያ የሆኑት እነ እማማ፤ ምንም እንኳ ታዋቂ ቢሆኑምና ካሜራዎች እየተከታተሉ ካልቀረጽናችሁ እያሉ ቢያስቸግሯቸውም፤ ሻያቸውን ፉት እያሉ ተሰብስበው የማውጋታቸውን ነገር አንዲያቆሙ አላደረጋቸውም፡፡ “ሰብሰብ ብለን እንቀመጥና ‘ህይወትን እንዴት ነው?’ እየተባባልን እናወራለን፡፡ አልፎ አልፎ ብንጋጭም ታዲያ ልክ እንደ ልጅነታችን ወዲያዉኑ ተመልሰን እንስማማለን” የሚሉት እማማ ኬዳሙሪ “አንድ ልብ እንዳለን ቁጠሩት… ብዙ ሆነን እንደ አንድ፤ አንድ ሆነን እንደ ብዙ ነው እየኖርን ያለነው” ብለዋል፡፡
በኦኪናዋ ደሴቶች ላይ የሚኖሩ ሰዎች በአለማችን በእድሜ ጠገብነት የሚስተካከላቸው የለም፡፡ በአብዛኛው ጊዜ አትክልትቶችን መመገብ የሚያዘወትሩት የደሴቶቹ ነዋሪዎች በአካባቢቸው የሚበቅለውን ስኳር ድንች ስኳር የሚባል ነገር ሳይቀላቅሉበት አዘውትረው ይመገባሉ፡፡ የኬቢጂ84 ሙዚቃ አባላት እድሜ ጠገብነትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሲሆን የሙዚቃ ቡድኑን ያቋቋመው ደግሞ በኮሃማ 20 አመታትን የኖረው እውቁ ጃፓናዊ ሙዚቀኛ ኪኩዎ ጹቺዳ ነው፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment