ወዳጄ መቼም ዛሬ ዛሬ የእድሜ ጣሪያ ነገር እያደር እያጠረ እያጠረ ሄዶ ቁጭ ብለን እስከምንነካው ድረስ ለአናታችን ከቀረበ ሰናባብቷል፡፡ መቶን መሻገር በራሱ እንደ አጀብ የሚታይበት ዘመን ላይም ከደረስን ቆይተናል፡፡ ታዲያ የእድሜ ነገር ከተነሳ ‘ወጣት የነብር ጣት’ እንደሚባለው በወጣትነት ቅልጥፍናው ሩጫው ውጣ ውረዱ ሁሉ በቀላሉ የሚከወን ይሆንና፤ ቀን በቀን ሲተካ እድሜም እየገፋ ሲሄድና ሀምሳን ሲሻገር ጎንበስ ማለትም በራሱ “ኧኧረረ…” እያስባለ “አሄሄ እርጅና አይንኑ አፍጥጦ ከተፍ አለኮ እናንተዬ” እያባባለ… ከዚያም ደግሞ የእድሜ ጸጋውን የተቸረው ሰባና ሰማኒያዎቹን ሲጠጋ የድሮው ቅልጥፍና ከነድራሹ ጠፍቶ እግርን እንኳን በአግባቡ አንስቶ መራመድ አዳጋች ሲሆን ማየት የተለመደ ነው፡፡ እድሜ መቶን ከዘለለማ እንዲያው ወዲያ ወዲህ ማለቱ ቀርቶ “በተቀመጥኩበት እንዳለሁ ወይም ደግሞ ተኝቼ የነገዋን ጸሀይ ባይ ትልቅ ጸጋ ነው! ይህንስ ማን አየበት! ተመስገን ፈጣሪዬ! ተመስገን!” ሲባል በተለያዩ አጋጣሚዎች ተመልክተን ወይም ሰምተን ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡
“በዚህ ጉዳይ እኔ አልስማማም፤ እድሜ ቢገፋም እንደ ልብ መሮጥ
ይቻላል” ያሉ የሚመስሉት ጃፓናዊው አባባ ሂዴኪቺ ሚያዛኪ የ105 አመት አዛውንት ሲሆኑ የምድራችን ፈጣኑ ሰው መሆናቸውንም አስመስክረዋል፡፡
በእሳቸው እድሜ ካሉት ጋር ተነጻጽረው ነው ታዲያ፡፡ አባባ ሂዴኪቺ ከሰሞኑ በሀገራቸው ጃፓን ኪዮቶ ላይ የአረጋውያንን ቀን ለመዘከር በተዘጋጀ የሩጫ ውድድር በእሳቸው እድሜ ክልል ካሉ ሌሎች አረጋውያን ጋር የመቶ ሜትር ሩጫ ውድድር
አድርገው ነው የአለም ፈጣኑ አዛውንት እሳቸው መሆናቸውን ያስመሰከሩት፡፡
ውድድሩ እንደተጀመረ ልክ እንደ አቦሸማኔ ፈትለክ ያሉት አባባ ሂዴኪቺ
100 ሜትሩን ውድድር ለማጠናቀቅ 42.22 ሰከንዶች ብቻ ነው የፈጀባቸው፡፡ እንግዲህ አባባ ሂዴኪቺ በመቶ ሜትር ውድድር ከአለም
ወደር የማይገኝለት ነው ከሚባለው የአለም ፈጣኑ ሰው ጃማይካዊው ዩሴይን ቦልት ጋር ቢወዳደሩ ቦልት ውድድሩን ካጠናቀቀበት ሰአት
32.64 ሰከንዶችን ብቻ ዘግይተው የውድድሩን መጨረሻ መስመር ያልፋሉ እንደማለት ነው፡፡
ወዳጃችን እንግዲህ ከ29 አመት ወጣቱ ቦልት 76 አመታትን አልፈው
105ኛ አመታቸውን ባከበሩ ማግስት እድሜያቸው ከ80 አመት በላይ ከሆኑ ሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር 100 ሜትር ሩጫ ውድድር አድርገው
በ42.22 ሰከንዶች በማጠናቀቅ የአለምን ክብረ ወሰን መጨበጥ የቻሉት አባባ ሂዴኪቺ ርቀቱን በ76 አመት የሚበልጡት ቦልት ካጠናቀቀበት
ሰአት 32.64 ሰከንዶችን ብቻ ነው የዘገዩት፡፡ ምናልባት ቦልት እድሜና ጤናውን ሰጥቶት የእሳቸው እድሜ ላይ ቢደርስ ርቀቱን እሳቸው
በገቡበት ሰአት ይገባ ይሆን የሚለውን ጊዜ የሚፈታው ቢሆንም ለአሁኑ ግን በ105 አመት እድሜ የምድራችን ፈጣኑ ሰው ጡረተኛው የቀድሞ
የጦር ሰራዊት አባል አባባ ሂዴኪቺ ሚያዛኪ ሆነው በአለም ክብረ ወሰን መዝገብ ላይ ስማቸው ሰፍሯል፡፡
ምንም እንኳ የአለምን ክብረ ወሰን መስበር ቢችሉም ታዲያ “በልምምዴ
ወቅት እኮ ርቀቱን በ36 ሰከንዶች ብቻ ነበር ያጠናቀቅኩት፤ ሀሳቤም በዚያ ሰአት እጨርሰዋለሁ ብዬ ነበር! ወይኔ ሰውዬው!” ሲሉ
በውጤታቸው የተቆጩት አባባ ሂዴኬቺ የስኬታቸው ምስጢር ምን እንደሆነ ተጠይቀው፤ “በየቀኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አደርጋለሁ፤ ለጤናዬ
የሚስማሙኝን ምግቦች የምመገብ ሲሆን በምመገብበት ወቅት ደግሞ ምግቦቹን በደንብ አድቅቄ ነው የምውጠው” ሲሉ ነው ምላሽ የሰጡት፡፡
‘ወርቃማው ቦልት’ የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው አባባ ሂዴኪቺ “እንደው ጊዜውና ቦታው ፈቅዶ ብንገናኝ ዩሴይን ቦልትን 100 ሜትር
ሩጫ ውድድር እገጥመዋለሁ” ብለዋል፡፡
No comments:
Post a Comment