Tuesday, September 15, 2015

1.5 ቢሊየን ብር የተሸጠው በአልማዝ ያሸበረቀ ኬክ

ወዳጄ 1.5 ቢሊየን አለዎት እንበል… ወይ ደግሞ ለአውዳመት በቆረጡት ሎተሪ እድል ቀንቶዎት 1.5 ቢሊየን ብር እቤትዎ ሰተት ብሎ ገባልዎት እንበል… “እንደው ይሄን ሁሉ ብር ምን ያደርጉበታል?” ቢባሉ ምላሽዎት ምን ይሆናል? ምናልባት ቅደም ተከተላቸው ቢለያይም “ያለብኝን እዳ እንዳለ ከፍዬ ከጨረስኩ በኋላ ቤት ወይም ቦታ ቢጤ ገዝቼ… እ መኪናም አይቀርም… ከዛ ደግሞ ትምህርቴን እቀጥላለሁ… ያሰብኩትን ቢዝነስም እጀምርበታለሁ… ደግሞም ለቤተሰቦቼ…” የሚሉ ምኞቶችዎት በምላሽነት እንደሚግተለተሉ አያጠራጥርም፡፡ 
ግና ታዲያ እርስዎ ወዳጄ ይሄን ሁሉ ነገር አደርገበታለሁ ያሉት 1.5 ቢሊየን ያክል መአት ብር “አንድ ኬክ ብቻ ነው መግዛት የሚስችልዎት!” ቢባሉ ኡ… ብለው እንደመጮህ የሚቃጣዎት ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም ደግሞ “ይህ ፈጽሞ የማይሆንና የሌለ ነገር ነው!!” ብለው ሊያስቡም ሊከራከሩም ይችሉ ይሆናል፡፡
እርግጥ ነው አንድ እኔ ነኝ ያለ ኬክ በሺዎች የሚቆጠር ብር ቢቆረጥለት በራሱ የሚያስደነግጥም የሚስገርምም ሊሆን ይችላል፡፡ ይበሉ እርምዎትን ያውጡ ቤት፣ መኪናና ሌላም ሌላም የሚያስደርገው 1.5 ቢሊየን ብር የአንድ ኬክ ዋጋ ሆኖ ቀርቧል ሲል ያስነበበው ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ፤ መኖሪያቸውን በዱባይ ያደረጉትና ማንነታቸው ያልተገለጸ የአረብ ባለጸጋ ቤተሰቦች የልጃቸውን ልደትና የቀለበት ስነስርአት በአንድ ላይ ለማክበር 75 ሚሊየን ዶላር ዋጋ የተቆረጠለት ኬክ አስጋግረዋል ሲል አስነብቧል፡፡ ወዳጄ 75 ሚሊየኑን እንዲሁ በ20 ይምቱትና እንግዲህ ሂሳቡን በብር ይደርሱበታል፡፡
“እንዲህ ከጣራ አልፎ ሰማየ ሰማያት የነካ ዋጋ የተቆረጠለት ኬኩ ከምን ቢሰራ ነው?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርምና ምላሹን እነሆ፡፡ በእርግጥ እስከዛሬ ኬክ ሲሳራ የሚታወቀው ዱቄት፣ ቅቤ፣ እንቁላል፣ ወተትና ስኳርን የመሳሰሉ ነገሮች ተዋህደው እንዲጋገሩ በማድረግ ነበር፡፡ “ይሄ የኬክ አሰራር ነገር ሰልችቶናል እስቲ ለየት ያለ ኬክ ያላችሁ ጋጋሪዎች እባካችሁ” ያሉት ዱባያውያኑ ቤተሰቦች በአልማዝ ፈርጦች ያሸበረቀ ኬክ አስጋግረው ነው እንግዲህ 1.5 ቢሊየን ብር ሆጭ አድርገው የከፈሉት፡፡
ይሄንን በአልማዝ የተንቆጠቆጠ ኬክ ለመጋገር ከባለሃብቶቹ ጋር የተስማማችው እንግሊዛዊት ‘የልብስ ቀዶ ጥገና ባለሙያ’ ወይም ዲዛይነር ዴቢ ዊንግሀም ናት፡፡ ዴቢ ከዚህ ቀደም በአለም ውድ ናቸው የተባሉ በአልማዝ ፈርጦች ያጌጡ ቀሚሶችን ሰርታ ለአለም ያሳየች እውቅ የልብስ ቀዶጥገና ባለሙያ ናት፡፡ እናም ይህን ጥበቧን ጨርቅ ላይ ብቻ ሳይሆን ሊጥ ላይም ትጠበብበት ዘንድ የቀረበላትን ጥያቄ 2 ሜትር ገደማ የሚረዝም ኬክ ጋግራ 17  በሚደርሱ የከበሩ ድንጋዮች ወይም አልማዞች አስጊጣው ብቃቷን አሳይታለች፡፡
ወዳጄ የተጋገረው ኬክ ከዚህ ቀደም እንደሚያውቋቸው ኬኮች በክብ፤ በአራት ማእዘን ወይ ደግሞ ተደራራቢ አሊያም ሌላ ቅርጽ ይዞ ሳይሆን ዲዛይነሯ ዴቢ ሙሽሪት በእለቱ ለብሳ እንድትደምቅባቸው ጨርቅ ላይ የተጠበበችባቸውን ቀሚሶች አምሳያ የለበሱ የኬክ አሻንጉሊቶች መድረክ ላይ ሲንጎማለሉ የሚያሳይና በሌሎች አጃቢ አሻንጉሊቶች ያሸበረቀ ነው፡፡ 
ዋናውና ትልቁ ነገር… የኬኩ ዋጋ መናር ምስጢር የሆነው ግን ይህ አይደለም ይልቁንም በኬኩ ላይ የሰፈሩት 5.2 ካራት ሮዝ አልማዝ፣ 6.4 ካራት ቢጫ አልማዝ፣ እያንዳንዳቸው 5 ካራት የሆኑ 15 ነጭ አልማዞችን ጨምሮ ሌሎች 4 ሺ የሚደርሱ የከበሩ ድንጋዮችና ትናንሽ አልማዞች ናቸው እንጂ፡፡ 

ዴቢ ይሄንን ኬክ ሰርታ ለማጠናቀቅ 1 ሺ 1 መቶ ሰአታትን ወይም 45 ቀናትን ፈጅቶባታል፡፡ ነገሩን አስመልከታ ተጠይቃም “ምንም እንኳ እንዲህ አለቅጥ ያሸበረቀ ቢሆንም… ኬኩ ያን ያክል ሳቢ አይደለም! እኔ በግሌ ከዚህ የተሻሉ… ኪስና ካዝናንም በዚህን ያክል ደረጃ የማያራቁቱ ኬኮችን አይቻለሁ… ብቻ ግን ቤተሰቦቹ ደስተኞች ነበሩ ዋናው ጉዳይ ደግሞ ያ ነው” ስትል ምላን ሰጥታለች፡፡
“ኬኩን ስኬታማ በሆነ መልኩ ሰርቼ በመጨረሴ በጣም ተደስቻለው… ግን ስራው በጣም ጊዜ የሚፈጅ ነበር! እያንዳንዷ ነገር በጥንቃቄ መሰራት ነበረባት… ብቻ በስተመጨረሻ ቤተሰቡም ሆነ የስነስርአቱ ታዳሚዎች በጣም ደስተኞች ነበሩ” ያለችው ዴቢ “የስነስርአቱ ታዳሚዎች ከኬካቸው ጋር የቀረቡላቸውን አልማዞች ይውሰዱ አይውሰዱ ማወቅ እፈልግ ነበር” ስትልም አክላለች፡፡
ወዳጄ አጀብ ዘንድሮ… አጀብ አጀብ ከማለት ሌላ ምን ይባላል፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment