Wednesday, September 23, 2015

ጥይት የማይበሳው መስታወት በባዙቃ(ላውንቸር) ቢመታ ይሰበራል ወይስ አይሰበርም? ራሻውያን በተግባር የተደገፈ ምላሽ አላቸው

ወዳጄ ሀገረ ራሺያ ከወደ ሞስኮ አካባቢ ነው ይላል ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል ድረገጽ፡፡ የጦር መሳሪያ ነገር የማይሆንላቸው፤ መሳሪያ ለተባለ ነገር ልዩ ፍቅር ያላቸው፤ ሰዎች ተሰባስበው “እንደው እናንተዬ ይሄ ላውንቸር ወይም ባዙቃ የሚባለው፤ በሮኬት የሚወነጨፍ፤ ጸረ ታንክ መሳሪያ ጥይት የማይበሳውን፤ 40 ሴንቲ ሜትር ውፍረት ያለውን፤ መስታዎት ይበሳው ይሆን? ወይስ መስታወቱ ይቋቋመዋል?” የሚል ጥያቄ አንስተው ያወራሉ፡፡ እናም “ለምን ሞክረን አናረጋግጠው!” ሲሉ ወፍራሙን መስታወትና ሩሲያ ሰራሽ አርፒጂ-7 ጸረ ታንክ ላውንቸራቸውን ሸክፈው የሙከራ ስራችንን እናደርግበታለን ወዳሉት ቦታ ያመራሉ፡፡
እናልዎት ወዳጄ ሙከራቸውን በቪዲዮ ምስል ቀድተው ለአለም ለማካፈል በተለያዩ ቦታዎች ካሜራዎችን አዘገጃጅተው የደቀኑት ሩሲያውያን ታዲያ ለግማሽ ሜትር ትንሽ የቀረውን ወፍራም መስታወት ካስቀመጡ በኋላ ከኋላው አንድ የፈረደበት፤ በሰው አምሳል የተሰራ፤ አሻንጉሊት አስቀምጠው ባዙቃ በመተኮስ ለተካነ ሙያተኛ “አልመህ ያንን መስታወት በዚህ ላውንቸር ድባቅ ምታወና እስቲ ምን እንደሚፈጠር አብረን እናያለን” ሲሉ “ያዝ እንግዲህ!” ይሉታል፡፡
የተተኮሰው ባዙቃ ታዲያ “እኔ ነኝ ያለ ጥይት እኔን አያልፈኝም” ብሎ ተኮፍሶ የቆመውን ወፍራም መስታወት ልቡን ብሎ እንዳልነበር አድርጎ በረቃቅሶታል፡፡ ጥይት የማይበሳውን መስታወት ተገን አድሮ ለባዙቃ ደረቱን ሰጥቶ የቆመው፤ ወዳጅ ዘመዶቹ በየልብስ ቤቱ ተሸቀርቅረው በየቀኑ ልብስ እየቀያየሩ የሚኖሩት፤ ያልታደለው አሻንጉሊት ታዲያ ነገሩ ያህያ ባል ከጅብ አያስጥል ሆኖበት መስታወቱን ለመፈተን የተተኮሰው ላውንቸር እጆቹን ነቃቅሎ ወዲያና ወዲህ አስፈንጥሮበት ከአፈር ቀላቅሎታል፡፡
“እስቲ መስታወቱን ሁለት እናድርገውና እንደገና ሞክረን ውጤቱን እንየው” ያሉት መሳሪያ አፍቃሪ ሩሲያውያኑ ታዲያ እንደገና ሁለት ጥይት የማይበሳቸው መስታወቶችን አራርቀው ሰድረው፤ ከላውንቸር ጥይት ጋር እንዲላተሙ ፈርደውባቸው፤ ለሁለተኛው ሙከራቸው “በል እንግዲህ ተኩስ” ሲሉ ለባዙቃ ተኩስ ሙያተኛው ትእዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ ምንም እንኳ የኛ የሀበሾት ተረት “ለአንድ ብርቱ ሁለት መድሀኒቱ” ቢልም ታዲያ ይህ ተረት በነመስታወት ዘንድ የሚሰራ አልሆነም፡፡
“ሁለት ሆነንማ አያቀተንም! አንዳችንን ቢጎዳን አንዳችን አፈር እናስልሰዋለን!” ብለው ለሁለት አንድ ብርቱውን ባዙቃ የገጠሙት መስታወቶች በባዙቃው ብርቱ ጡጫ ሆዳቸው ተቦድሶ እያንዳንዳቸው በአካላቸው ላይ ቀዳዳ ለማበጀት ተገደዋል፡፡ እነሱም ብቻ አይደሉ ታዲያ መስታወቶቹን መከታ አድርጎ ከላውንቸር ጋር ሊፋለም ከጀርባቸው የቆመው አሻንጉሊትም ድጋሜ እንዳይሆኑ ሆኖ ተበረቃቅሷል፡፡
ወዳጄ እንግዲህ ሩሲያውያኑ ይህን መሞከራቸው “ጥይት የማይበሳው ነው!” የሚባለው መስታወት “የባዙቃ ጥይትን ይቋቋማል ወይ?” የሚለውን ለማወቅና ለማሳየት ፈልገው ይሆናል፡፡ ሙከራቸውን ያደረጉትም ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገውና ከሙያተኞች ጋር አብረው መሆኑ ምንም ጥርጥር የለው፡፡

እናም እኛ ሙከራውን በጉዳዩ ላይ እወቀት ያስጨበጠን አድርገን እንውሰደው፤ ከስራችን ጋር የተያያዘ ካልሆነ በስተቀር፤ ማለትም ፖሊስ ወታደር ወይም ሌላ ከጦር መሳሪያዎች ጋር የሚያገናኝ ስራ የማንሰራ ከሆነ፤ እራሳቸንን ከጦር መሳሪያ እናርቅ፤ እንዲሁም ደግሞ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሙከራዎችን ልናደርግ ካቀድን ተገቢውን ጥንቃቄ እናድርግ በዘርፉ ላይ እወቀትና ክህሎት ያላቸውን ሰዎችም እናማክር መልእክቴ ነው፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍኤም 96.3

No comments:

Post a Comment