Thursday, September 3, 2015

40 ኪሎ ግራም የሚመዝን፤ 30 ሹራቦችን መስራት የሚያስችል ጸጉር እላዩ ላይ ተሸክሞ ሲዞር የነበረው ጸጉራሙ በግ ‘ክሪስ’

ወዳጄ… አውስታራሊያ ካንቤራ ውስጥ ነው፡፡ “በሰዎች ቁጥጥር ስር መኖር አልፈልግም” ያለው ‘ክሪስ’ “የቤት እንስሳነት ነገር ይቅርብኝ” ብሎ የጫካ ኑሮን ከተቀላቀለ ሰነባብቷል፡፡ ባሳለፍነው እሮብ በአልፎ ሂያጅ መንገደኞች አይን ውስጥ ገብቶ የተገኘው ‘ክሪስ’ በጉ “ምናልባትም በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመቀስ ጋር ተዋውቋል” የሚለው አሶሼትድ ፕሬስ ‘ክሪስ በጉ’ “30 ሹራቦችን ቅልብጭ አድርጎ መስራት የሚያስችል 40 ኪሎግራም ጸጉር ተሸክሞ ነበር ህይወትን በጫካ መምራቱን የተያያዘው” ሲል አስነብቧል፡፡
‘አውስትራሊያን ሜሪኖ’ በመባል ከሚታወቁትና በጸጉራቸው ትልቅነት ከሚለዩት የበግ ዝርያዎች የሚመደበው ክሪስ እንዳይወልድ የተደረገ ወይም በተለምዶ እንደምንለው ‘የተቀጠቀጠ’ ነው፡፡ የክብደቱ እኩል የሆነ ጸጉር እላዩ ላይ ተከምሮበት የነበረው ክሪስ ጸጉሩ ከተገፈፈለት በኋላ 44 ኪሎግራም ብቻ የሚመዝን፤ ሸንቃጣ በግ ወጥቶታል፡፡ ከነጸጉሩ እንግዲህ 84 ኪሎ ይመዝን እንደነበር ልብ ይሏል፡፡
የክሪስን ጸጉር የሸለተው፤ በበግ ሸላችነቱ ወደር እንደማይገኝለት በተለያዩ ውድድሮች ላይ ብቃቱን በማሳየቱ የሚታወቀው፤ ኢያን ኤልኪንስ “‘ክሪስ’ ከዚህ በፊት መቀስ አይቶ የሚያውቅ አይመስለኝም፤ ምናልባት እድሜው አምስት ወይ ስድስት አመት እንደሚሆንም እገምታለሁ” ብሏል፡፡ 40 ኪሎ ጸጉር ከላዩ ላይ የወረደለት ክሪስ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ የተናገረው ሸላቹ ኢያን “የአለምን ክብረወሰን ያለምንም ጥርጥር ሰብረንዋል” ሲልም ነው ለኤቢሲ የዜና ምንጭ አስተያየቱን የሰጠው፡፡
“ከላዩ ላይ የተሸለተለት 40 ኪሎ ግራም ጸጉር ክሪስን የአለምን ክብረ ወሰን መጨበጥ የሚያስቸለው ስለሚሆን ለክብረ ወሰን መዝጋቢ ድረጅት አሳውቀን እንዲመዘገብ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው” ያሉት በጉን ከጫካ ያነሳው የካንቤራ ሪስፔካ ተቋም ሀላፊ እትዬ ታሚ ቬን ዳንጅ “አሁን ላይ ክሪስ በጣም ደህና ነው… በቃ ልክ እንደ አዲስ እንደተፈጠረ ቁጠረው… ስናመጣው እኮ ሰው በጣም ይሸሽ ነበር! እየተንቀጠቀጠና ቆሞ መሄድ እራሱ ከብዶት ነበር… አሁን ግን ሰውን ቀረብ ቀረብ ማለት እየለመደ ነው፡፡ በአጠቃላይ ስናመጣው ከነበረበት ሆኔታ አሁን ያለበት ሁኔታ በጣም የተሸለ ነው” ብለዋል፡፡
“ሌላው ቀርቶ ጸጉሩ አለቅጥ እላዩ ላይ መከመሩ እኛ አግኝተን ባናነሳለት ህይወቱን ሊያሳጣው ይችል ነበር” ሲሉም ክሪስን አስመልክተው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ክሪስ አስፈላጊው ህክምና ከተደረገለት በኋላ አዲስ መኖሪያ እንደሚሰጠውም ነው እትዬ ታሚ የተናገሩት፡፡ የጸጉሩ ነገር ግን እንዲያው ሙዚየም ውስጥ ለመቀመጥ ካልሆነ በስተቀር እድሜው የገፋ በመሆኑ ለሽያጭ የሚቀርብ እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2004 ዓ.ም. 27 ኪሎ የሚመዝን ጸጉር ከላዩ ላይ አስሸልቶ የአለምን ክብረ ወሰን መያዝ የቻለው በዋሻ ውስጥ ተደብቆ ስድስት አመታትን የኖረው ሽሬክ የተባለ በግ ነበር፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment