Thursday, September 17, 2015

የ30 አመቱ ቻይናዊ ወጣት ሽማግሌ ሆነ



ወዳጄ አንድ ሰሞን መጥታ ብዙዎች ሲቀባበሏት የነበረች “ወመሽ” የምትባል ቃል ያውቃሉ እንዴ? እንደውም ገጥሞዎት ሰምተው ወይ እርስዎም እራስዎ ብለዋት ያውቁ እንደሁ ብዙ ጊዜ… “ኧረ ባክህ እሱ ቀላል ሰው እናዳይመስል እንዲህ ስታየው አንድ ፍሬ ልጅ ይመስላል እንጂ ወመሽ ነው እኮ…” “ማ እሷ!.. አታቂያትም ማለት ነው ሜካፕ ነው እንጂ እልም ወመሽ ናት እኮ..” አይነት ወሬዎች አንድ ሰሞን ላይ ይደመጡ ነበር፡፡ እናልዎት ይቺህ “ወመሽ” የምትል ቃል ምህጻረ ቃል እንደ ሆነችና ስትዘረዘረም “ወጣት መሰል ሽማግሌ” የሚል ፍቺ እንዳላት ቃሏን ከሚያዘወትሯት ሰዎች ዘንድ የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡


“ወመሽ” እንግዲህ ወጣት መሰል ሽማግሌ የሚል ፍቺ ካለው ለቻይናዊው ዩአን ቴይፒንግ ቃሉ መገልበጥ ሳይኖርበት አይቀርም፤ እናም “ወመሽ” የሚለው “ሽመወ” ተብሎ እንዲቀመጥ ሳያስደርግ አይቀርም የሚል የሚመስለው ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ቻይናዊው የ30 አመት ወጣት፤ ዩአን፤ የ80 አመት አዛውን ፊት ይዞ እየኖረ ይገኛል ሲል አስነብቧል፡፡
በቻይና ቾንግቂንግ መኖሪያውን ያደረገውና በአንድ የግንባታ ስራ በሚያከናውን ተቋም ውስጥ በማናጀርነት እየሰራ የሚገኘው ዩአን ባልተለመደ መልኩ የፊቱ ቆዳ ተሸብሽቦ የ80 አመት አዛውንት መልክ እንዲይዝ ያስገደደው በሽታ በቅጡ የታወቀ አይደለም፡፡ ለችግሩ መፍትሄ ፍለጋ ያልረገጠው የዶክተር ደጅ ባይኖርም “በሽታህ ይህ ነው… እንዲህ ብታደርግ ደግሞ መፍትሄ ይሆንሃል” የሚለው አንድም ሀኪም ማግኘት ግን አልቻለም፡፡ 
እስከ ሀያ አመቱ ድረስ ትክክለኛ መልኩን ይዞ የኖረው ዩአን ከዚያ በኋላ ነበር በሰውነቱ ላይ ለውጦችን ማየት የጀመረው፡፡ እግርና እጆቹ ላይ እባጮች መውጣት ሲጀምሩ ፊቱ ላይ ደግሞ ወፋፍራም መስመሮች መጋደም ጀመሩ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ነገሩ እንዲሁ ከውጥረት ብዛት የመጣ የመሰለው ዩአን ነገሩን ችላ ቢለውም የኋላ ኋላ ግን መስመሮቹ ግንባሩ ላይ እየጎሉ መሄድ ሲጀምሩ ነው የሆነ ችግር እንዳለ መጠርጠር የጀመረው፡፡ ከዚያ ጊዜ አንስቶም ላለፉት 9 አመታት የዶክተሮችንና የባህል ሀኪሞችን ደጅ ደጋግሞ ቢጠናም ጠብ የሚል መፍትሄ ማግኘት አልቻለም፡፡
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1985ዓ.ም. እንደተወለደ የሚናገረው ዩአን “በ21 አመቴ ገደማ ነበር ህመሙ የጀመረኝ… አሁን ዘጠኝ አመት ሞልቶታል፡፡ ሲጀምረኝ አጆቼና እግሮቼ ነበሩ ማባበጥ የጀመሩት ከዛም ፊቴ መጨማደድና መስመር ማበጀት ጀመረ… እናም አሁን ከአመት አመት እየባሰበት እየሄደ ነው፡፡ አመት በጨመረ ቁጥረም በቃ ይበልጡኑ እየተሰላቸሁ ነው” ሲል ነው ችግሩን አስመልክቶ የተናገረው፡፡ 
የዩአን ያለእድሜው ያረጀ ፊት ህይወቱን በብዙ መልኩ እያመሰቃቀለበትም ይገኛል፡፡ በመታወቂያው ላይ ያለው ፎቶውና አሁን የያዘው መልኩ ፈጽሞ አይገናኙም፤ እናም ህጋዊ የሆኑ ማስረጃዎቹ እንዳሉ ከመልኩ ጋር ተጣርሰውበታል፡፡ “ከባለቤቴ ጋር መንገድ ላይ አብረን ስንሄድ ሰዎች በግርምት ነው የሚመለከቱን፡፡ አንዳንዶች እንደውም ጠጋ ብለው ‘ወጣት ሆነሽ ከዚህ ሽማግሌ ጋር ምን ትሰሪያለች?’ የሚሉኝም አልጠፉም” የምትለው የዩአን ባለቤት ምንም እንኳ ባሏ ምንነቱ ባልተወቀና መድሀኒት ባልተገኘለት ህመም ተይዞ ያለ እድሜው የሸመገለ ቢመስልም ከልቧ እንደምትወደው ነው የተናገረችው፡፡
የዩአን በሽታ ገና ምንነቱ እየተጣራ ቢሆንም ታዲያ ሌሎችም በመሰል ህመም የተጠቁ ሰዎች በነዩአና መንደርና አጎራባች ቦታዎች ታይተዋል፡፡ የዩአን ታናሽ ወንድምም በ25 አመቱ መሰል ህመም እየታየበት ሲሆን ሌሎች ሁለት የመንድሩ ሰዎችና አንድ ሰው ከጎረቤት መንደር በተመሳሳይ ህመም መያዛቸው ተሰምቷል፡፡ ይህም ነገሩ በዘር የሚተላልፍ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነውም እየተባለ ነው፡፡ 
የሆነው ሆኖ ግን በሽታው ታወቆ መድሃኒት እስኪያገኝ ዩአን ገና በወጣትነቱ የሽማግሌ ፊት ይዞ ለመኖር መገደዱ ሀቅ ነው፡፡ “እባካችሁ መላ የምታውቁ እርዱኝ!!” ያለው ዩአን “የችግሬ ስር መሰረቱ ምን እንደሆነ የሚነግረኝና የምፈወስበትን መንገድ የሚያስተምረኝ… የሰው ያለህ!! እባካችሁ!!” ሲል ተማጽኗል፡፡ ወዳጃችን ዩአን ፈጣሪ ምህረቱን ያውርድልህ እያልነው እርስዎንና እኔን ደግሞ ይሰውረን ብያለሁ ወዳጄ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment