Monday, August 31, 2015

“የመንገድ ሀኪሙ” ህንዳዊ ጡረተኛ

በሙሉ ስማቸው አቶ ጋንጋድሃራ ቲላክ ካትናም ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ብዙዎች የሚያውቋቸው ግን “የመንገድ ሀኪም” በሚል ቅጥል ስማቸው ነው፡፡ በህንዷ ሀይደራባድ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት የ66 አመቱ ጎልማሳ አቶ ቲላክ ቀደም ባለቱት ጊዜያት በባቡር ኢንጂነርነት ነበር ህይወታቸውን ሲመሩ የኖሩት፡፡ እድሜያቸው መግፋቱን ተከትሎም ከስራቸው በጡረታ ይገለላሉ፡፡ አንድ አመት ያክል ካለስራ ሽርሽር እያሉ ቆይተው ታዲያ የአማካሪነት ስራ ሊጀምሩ በተሰናዱበት አንድ እለት ነበር “የመንገድ ሀኪምነት” ጥሪን ከህይወት ያስተናገዱት፡፡


“ወደ አዲሱ ስራዬ እያመራሁ ነበር መንገድ መሃል ተጠራቅሞ የነበረ አዳፋ ውሃ  በተማሪዎች ላይ አንቦራጭቄ ያለፍኩት፡፡ በተመሳሳይም መሰል ክስተቶች በተለያዩ ቦታዎች በተደጋጋሚ አጋጠሙኝ፡፡” ሲሉ ጉዳዩን የሚያስታውሱት ጋሽ ቲላክ “መንገዶች ቢስተካከሉ እኮ እንዲህ ያለ ነገር አይከሰትም” ሲሉም ለፖሊስ አባላት ደጋግመው ቢያመለክቱም መፍተሄ አላገኙም ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለም ነበር ሁሉን ነገር አስትቶ መንገዶችን በማከም ስራ ህይወትን እንዲመሩ ውሳኔ እንዲወስኑ ያደረጋቸውን ከፍተኛ የመኪና አደጋ የተመለከቱት፡፡
ከአራት ቀናት በፊት አደጋ ደርሶበት ባዩበት ቦታ ላይ አንድ መኪና ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ ላይ አደጋ አድርሶ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ተመለከቱ፡፡ “እነዚህ በመንገዶች ላይ ተቆፋፍረው የሚገኙ ጉድጓዶችን የሚደፍን ሰው ቢኖር እኮ የሰው ልጅ ህይወት እንዲህ በከንቱ አይቀጠፍም ነበር” ሲሉ አስበውም ከዚያን ጊዜ አንስቶ በአካባቢያቸው ብሎም በከተማዋ ያሉ የመንገድ ላይ ጉድጓችን በመድፈን ለመንገድ ህክምና የመስጠት ስራቸውን ሀ ብለው ጀመሩ፡፡ ተግባራቸውንም ሽራማዳን ሲሉ ሰየሙት ትርጓሜውም የጉልበት ድጋፍ፣ እገዛ ማድረግ የሚል ነው፡፡
“በመኪና አደጋ ህይወትን ያክል ነገር መነጠቀ ልብን የሚያሸብር ነገር ነው!” የሚሉት ጋሽ ቲላክ በመኪናቸው እየተዘዋወሩ በየመንገድ ጥጋጥግ ላይ ተደፍተው የሚገኙ የአስፓልት መስሪያ ቁሳቁሶችን እየሰበሰቡ መንገድ ላይ ጉድጓድ በገጠማቸው ቁጥር እየደፈኑ መኖር ጀመሩ፡፡ ለዚሁ መልካም ስራ ሲሉም ስራቸውን በፍቃዳቸው ለቅቀው በጡረታ የሚያገኟትን ገንዘብ የተበላሹ መንገዶችን ለማከም ማዋልን ተያይዘው አንድ አመት ዘለቁ፡፡ በእስካሁኑ ቆይታቸውም አንድ ሺ የሚደርሱ የመንገድ ጉድጓችን አክመው ደፍነዋል፡፡
የባለቤታቸው ነገር አልዋጥ ያላቸው፤ በጠራራ ጸሀይ አስፓልት ለአስፓልት መዞራቸው ጤናቸውን አደጋ ላይ ይጥለዋል ብለው የሰጉት የጋሽ ቲላክ ባለቤት ታዲያ ነገሩን በአሜሪካ ለሚኖር ልጃቸው አሳውቀው “እባክህ እስቲ እረፍ በለው!” ሲሉ ስሞታ ለልጃቸው ነግረዋል፡፡ ምንም እንኳ የእናቱን ጭንቀት ቢረዳም የአባቱን ተግባር ያደነቀው ልጃቸው ግን “ይህ ነገር ይቅርብህ!” ብሎ አባቱን ከማስቆም ይልቅ በሚችለው መጠን ከአባቱ ጎን ቆሞ ይህን መልካም ምግባር ወደፊት ለማራመድ ነበር የወሰነው፡፡

ዛሬ ላይ የጋሽ ቲላክን ‘ሽራማዳን’ የተገነዘቡ ሰዎች ጋሽ ቲላክ መንገድ ሲያክሙ ከጎናቸው ሆነው ያግዟቸው ጀምረዋል፡፡ አንዳንዶች እንዳውም የተበላሸ መንገድ ሲገጥማቸው ሀሎ ሲሉ ነገሩን የሚያሳውቁበት የስልክ መስመርም አሰናድተዋል፡፡

“የተበላሹ መንገዶችን እኛ እንጠግናቸዋለን” እያሉ የጋሽ ቲላክን ተግባር ሲያጣጥሉ የነበሩ የማዘጋጃ ቤት ሰዎችም የጋሽ ቲላክ “ወደ ኋላ አልልም” ባይነት አሸንፏቸው ዛሬ ላይ የመንገድ መጠገኛ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ከጎናቸው ሊቆሙ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ የቤት ወጪያቸውን ልጃቸው እየሸፈነላቸውም ከማዘጋጃ ቤትም ቁሳቁስ አቅርቦት እያገኙ  ስለሆነም ጋሽ ቲላክ በጡረታ ከሚያገኟት 25 ከመቶ የምትሆነዋን ኪሳቸው እንድትቀመጥ አድርገዋል፡፡ ከሰዎች የገንዘብ ድጋፍ ሳይሆን የጉልበት እገዛን ብቻ ሚፈልጉት የመንገድ ሀኪሙ ‘የማይቻል ነገር የለም!’ ብለው ያምናሉ፡፡ “የሰዎች አስተሳሰብ መቀየር አለበት አስተሳሰባችን ነው እየገደበን! ያለው ይሄ መቀየር አለበት” ብለዋል፡፡ “ይህን ለማድረግ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮችን እይታ ማግኘታቸው ትልቅ ጥቅም እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡”


ወዳጄ ከ66 አመቱ ጎልማሳ ጋሽ ቲላክ ‘ሽራማዳን’ ተግባር ብዙ ነገር መማር እንደምንችል ጥርጥር የለውም፡፡ የመኪና አደጋውም ሆነ የመንገዶች መቆፋፈር እዚህ እኛ ሀገርም በርክቶ የሚታይ ጉዳይ ነውና እኛም ‘የማይቻል ነገር የለም!’ የሚለውን እሳቤ ይዘን በመነሳት እያንዳንዳችን ለበጎ ምግባር እንሰለፍ መልእክቴ ነው፡፡ 
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment