Monday, August 31, 2015

“ጫካ ለምኔ” ያለችው አንበሳዋ ኤልሳ ብርድ ልብስ ለብሳ አልጋ ላይ መተኛትን መርጣለች

“የእንስሳቶች ንጉስ፤ በሚያስገመግም ድምጹ አራዊትን የሚያሸብር፤ በፈርጣማ ክንዱ ደቁሶ ከአፈር የሚደባልቅ፤ በዱር በጫካ የሚኖር… ይህ እንስሳ ማነው?” ቢባሉ እርስዎ ወዳጄ ካለምንም ማቅማማት “እንዴ… አንበሳ ነዋ!” ብለው በፍጥነት እንደሚመልሱ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ “እርግጥ ነው መልስዎት ላይ ምንም ስህተት ባይኖርበት ለኔ ግን አልተመቸኝም” የምትልዎት ኤልሳ፤ የሞቀ የደመቀ ቤትና ምቹ አልጋ እያለ እንዴት ሲባል በዱር በገደሉ ይታደራል ብላ ብድር ልብስ እየለበሰች አልጋ ላይ መተኛትን መርጣለች፡፡


ኤልሳ አንበሳ ነች፡፡ “በየጫካው እያደኑ መኖር የሚያዋጣ አልመሰለኝም… ልክ እንደነ ውርዬ እቤት ውስጥ ከትሞ ጓዳና ሳሎን እየተመላለሱ መኖር ነው ብልህነት” ያለች የምትመስለው ኤልሳ መኖሪያዋን በደቡብ አፍሪካ ከአሳዳጊዋ ሚኪ ቫን ቶንደር ጋር በሚኪ ቤት ውስጥ አድርጋለች፡፡

አይደለም ቀርበው ሊዳብሷቸውና አብረው ሊተኙ ቀርቶ እዚህ ስድስት ኪሎ አንበሳ ግቢ ከፍርግርግ ብረት ጀርባ ሆነው ይጎበኙ ከነበሩት አንበሶች ጋር ቀረብ ብሎ ፎቶ መነሳት በብዙዎች ላይ ምን ያክል መሳቀቅና ፍራቻ ይፈጥር እንደነበር እራሳችን ገጥሞን አሊያም ፎቶ ለመነሳት የቆሙ ሰዎች በአንበሶቹ ድምጽ ደንግጠው ለመሮጥ ሲዳዳቸው አይተን ታዝበን ይሆናል፡፡ አንበሳን እንደ ቤት እንስሳ አላምዳ እየኖረች ያለችው ሚኪ ግን አንበሳ መፍራት ሲያልፍም አይነካካኝ ብላለች ይላል ሜትሮ ድረገጽ ያስነበበው ዘገባ፡፡

በህጻንነቷ ከእናቷ የተለያየቸውን ኤልሳ በማደጎነት ተቀብላ እንደ እናት ተንከባክባ ያሳደገቻት ሚኪ ለኤልሳ ልዩ ፍቅር አላት፡፡ ስለኤልሳ ተጠይቃም “አብረን ነው የምንተኛው፤ ብርድ ልብስ ለብሰን ተቃቅፈን ነው የምናድረው… ከአንበሳ ጋር መተኛት በጣም ገራሚ ነው” ስትል ነው ምላሽ የሰጠችው፡፡ ኤልሳን ልክ እንደ ልጇ አድርጋ የምትንከባከባት ሚኪ በአንድ ወቅት ኤልሳ ክፉኛ ታማባት ህይወቷን ለማዳን የቀዶ ጥገና ህክምና ማድረግ ነበረባትና ለህክምናዋ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ ሚኪ አንበሳ የሚያስመስላትን ልብስ ለብሳ በየቀኑ በመንገድ ዳር ቆማ ገንዘብ ታሰባስብ ነበር፡፡ ይህ ተግባሯም በአካባቢዋ ሰዎች ዘንድ ታዋቂነትን አትርፎላት ነበር፡፡

ወዳጄ የኤልሳና የሚኪን የእናትና ልጅ ፍቅር እንዴት አዩት ታዲያ፡፡ እርግጥ ነገሩን ማድነቅዎትና መገረምዎት እንዳለ ሆኖ፤ “አሄሄ… ምን ቢያለምዱት አንድ ቀን አንበሳ አንበሳነቱ ትዝ ሳይለው አይቀርምና ሚኪም የኤልሳን አንበሳነት መዘንጋት አይኖርባትም” ሳይሉ እንደማይቀሩ እገምታለሁ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment