Sunday, August 30, 2015

“ይሳሙኝ ስኒ” ለገበያ ሊቀርብ ነው

“ያልታደለ ከንፈር ሳይሳም አረጀ” ይላል የኛ ሰው ሲተርት፡፡ “ኧረ ምን በወጣው ሳይሳም ያረጃል” ያሉ የሚመስሉት ኮሪያውያን “እንደ ልብዎት የሚስሙት ባለከንፈር የቡና ስኒ እያለልዎት… ምን ቁርጥ አድርጎት ነው ከንፈር ሳይሳም የሚያረጀው ብለዋል፡፡”
መቼም ቡና ለኛ ለኢትዮጵያውያን ያለው ትርጉም ለየት ያለ እንደሆነና ሌላው ቀርቶ የትውልድ ቦታው እራሱ እዚሁ እኛው ጋር ስለመሆኑ እርስዎ ወዳጄ ጠንቅቀው የሚያውቁት ጉዳይ እንደሆነ አልጠራጠርም፡፡ የቡና አፈላል ባህላችን እራሱ ልዩ ከሚያደርጉን መለያዎቻችን መካከል አንዱ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡

እናልዎት ወዳጄ ጠዋት… “ከእንቅልፍዎት እንደተነሱ ከሁሉ ነገር ቀድሞ ውልብ የሚልብዎት ቡና ከሆነና የ‘ሳይሳም አረጀ’ ተረት ነገር ሆድ ሆድዎትን እየበላዎት አስቸግሮዎት እንደሁ ጥሩ መላ ዘይጄልዎታለሁ” የሚለው ከሪያዊ ጠበብት “አዲሱ ፈጠራዬ ባለከንፈር የቡና መጠጫ ነው፤ ቡናዎትን ብቻ ሳይሆን ከንፈርም እንዲያጣጥሙ የሚያሰችልዎት ስኒ እነሆ ልልዎት ነው ብሏል፡፡”






ኮሪያዊው ጃንግ ውሲዎክ የሰራው አዲሱ የቡና መጠጫ ስኒ በሰው ከንፈር ቅርጽ የተሰሩ ከናፍርቶች ያሉት ሲሆን ስሙንም በግርድፉ ወደ አማርኛችን ስንመልሰው ‘ይሳሙኝ ስኒ’ ብሎ ሰይሞታል፡፡ በእርግጥ ስኒው አሁን ላይ ለገበያ የቀረበ ባይንሆንም ወደ ገበያው እንደተቀላቀለ ግን ትላልቅ ቡና መሸጫ ድርጅቶች እንደሚረባረቡበት ከወዲሁ ተገምቷል እንደ ዴይሊሜል ድረገጽ ዘገባ፡፡

አዲሱ ፈጠራውን አስመልክቶ ጃንግ ሲናገርም… “እንዲሁ ዝም ብሎ እንደ ሌሎች የቡና መጠጫዎች አይደለም… ይሳሙኝ ስኒ ልክ በሰው ፊት ቅርጽ የተሰራ ነው ከቡና መጠጫነቱ በተጨማሪ የሚያዝናናም ነው… ቡናውን የሚጠጣው ግለሰብ አይኑ በሚመለከተው ነገር ዘና እያለ መንፈሱን በማደስ ከወትሮ ለየት ያለ ቡናን ማጣጣም ይችላል” ሲል ነው ስለ ‘ይሳሙኝ ስኒ’ ፈጠራው ያስረዳው፡፡ “እርግጥ ነው ሁሌ ቡና መጠጣት ይቻል ይሆናል መሳምም ሆነ መሳም ግን እንደ ልብ ስለማይገኝ ‘ይሳሙኝ ስኒ’ ለዚህ ትልቅ መላ አለው ወይም አላት ሲልም ቀልድ ቢጤ አከል አድርጓል፡፡”

ወዳጄ ታዲያ የጃንግ የፈጠራ ውጤት ገበያውን ሲቀላቀል እሱ እንዳለው እንደ ልብ የማይገኘውን ከንፈር በየካፌውና በየጀበና ቡና መሸጫው ሁሉም በየፊናው እየኮመኮመው ‘ያልታደለ ከንፈር’ የሚለውን ተረት ከጨዋታ ውጪ ያደርገው ይሆን? ማን ያውቃል አንግዲህ ‘ይሳሙኝ ስኒ’ ለገበያ ሲቀርብ  አብረን የምንታዘበው ጉዳይ ይሆናል፡፡

ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment