የእናት ውለታዋን… (ብዙነሽ በቀለ)
.
.
ይህ ዘፈን በቻይንኛ ተተርጉሞ ተዘፍኖ ቢሆን ኖሮ
በእርግጠኛነት አቶ ሼን በቀን ውስጥ ለቁጥር የሚያታክት ጊዜ እያንጎራጎረው እንደሚውል ጥርጥር የለኝም፡፡ ሼን ዢንጂን የ48
አመት ጎልማሳ የሆነ ቻይናዊ ገበሬ ነው፡፡ ለእናቱ ልዩ ፍቅር ያለው፡፡
.
.
መኖሪያውን በቾንግ ኪንግ ከተማ ቶንግዢን መንደር ውስጥ ያደረገው
ሼን ገና የ7 አመት ታዳጊ ሳለ ነበር በደረሰበት የኤሌክትሪክ አደጋ ሁለት እጆቹን ለማጣት የተገደደው፡፡ ካሳለፍነው ወር
አንስቶ በህመም ምክንያት ፓራላይዝ ሆነው ከአልጋ ለመዋል የተገደዱት እናቱን የመንከባከብ ሀላፊነት ሙሉ በሙሉ እሱ ላይ
የወደቀው ሼን እምዬ እናቴ እኔ ልጅሽ እያለሁልሽ ወድቀሽ አትወድቂም አይዞሽ ብሎ እናቱን እያስታመማቸው ይገኛል፡፡
.
ምንም እንኳ ሁለት እጆች ባይኖሩትም ሼን የ91 አመት አዛውንቷ
እናቱን ከማስታመም ወደ ኋላ አላስባሉትም፡፡ እግሩን በመጠቀም የቤት ውስጥ ስራዎችን አቀላጥፎ እከወነ ምግብ አበሳስሎ በአፉ
ማንኪያ ነክሶ ይዞ ለእናቱ ምግብ እያጎረሰ፤ መጥገባቸውን ጭንቅላታቸውን ነቅንቀው እስኪገልጹለት ድረስ እየመገባቸው ህይወትን
መምራቱን ተያይዞታል፡፡
.
.
መንፈሰ ጠንካራው ሼን በርካታ የመንደሩ ሰዎች ለምን ወደ
ከተማ ወጣ ብለህ እየለመንክ አትኖርም ሲሉ ቢመክሩትም “እርግጥ ጥሩ እጆች የሉኝም… ነገር ግን ምርጥ እግሮች እስካሉኝ ድረስ ምንም
ብዙ ሊሆን ቢችልም በልመና የሚገኝን ገንዘብ ፈጽሞ አላስበውም… ሰርቼ እየኖርኩ እናቴን እጦራታለሁ” የሚል ምላሽ እየሰጠ ነው
ሲሸኛቸው የኖረው፡፡
.
“እጆች ባይኖሩኝም ምርጥ እግሮች አሉኝ” የሚል የህይወት
መርህ ያለውና አካል ጉዳተኝነቱ ከምንም ያልገደበው፤ ቆፍጣናው ገበሬ ሼን የቤት ውስጥ ስራዎችን ብቻ ሳይሆን የእርሻ ስራንም
ቢሆን አቀላጥፎ ማከናወን ይችላል፡፡ ጠንክሮ በመስራቱም 24 በጎች፣ ሁለት ከብቶች አራት ዶሮዎችን በጥሪትነት ማፍራት የቻለ
ሲሆን እህልም ቢሆን ከእርሻው ላይ ይሰበስባል፡፡
.
.
ማንኪያ በአፉ ነክሶ ከማእድ ላይ እየጨለፈ እናቱን በመመገብ
እያስታመመ፤ በቀን ለሶስት ጊዜ የሚወስዱትን መድሃኒትም ሳያቆራርጥ እየሰጣቸው ያለው ሼን የበርካታ መገናኛ ብዙሃን አውታሮችን
ቀልብ መሳብ የቻለ ሲሆን ይህ ድንቅ ተግባሩም በርካቶች በግርምት ጣታቸውን አፋቸው ላይ ጭነው እንዲደነቁና በተለያዩ ማህበራዊ
ድረገጾች ስለሱ እንዲወያዩ አድርጓቸዋል፡፡
.
ሁለት እጆች ባይኖሩትም በሌሎች እርዳታና ምጽዋት ላይ
ተንጠልጥሎ እየለመነ ከመኖር ይልቅ እየሰራ ህይወትን ለማሸነፍ ከወሰነው ሼን የምንማረው ልበ ሙሉነትና መንፈሰ ጠንካራነት
እንዳለ ሆኖ ሼን ለእናቱ ያለው ፍቅር ብዙ ነገር ሳያስተምረን የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ወዳጃችን ሼን ሀሳብህ ይሙላልህ!!!
ጀግና ነህ!!! ብሎ ነገሩን በአግራሞትና በአድናቆት ከመመልከት ባለፈ የሼንን አርአያነት እርስዎ ወዳጄ በልብዎት ያሳድሩት
መልእክቴ ነው፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3
No comments:
Post a Comment