Friday, August 28, 2015

ቻይናዊቷ አዛውንት ቀንድ አበቀሉ



በእርግጥ ከዚህ ቀደም እድሜው ገፍቶ ቀንድ ያበቀለ ሰው ኖሮ ይሁን ወይ ደግሞ ሌላ ምክንያት ኖሮት ብቻ መነሻው ከምን እንደሆ በእርግጠኛነት ይህ ነው ማለት ቢያስቸግርም በጨዋታ መሀል የእድሜያችንን መግፋት ለመናገር ስንፈልግ… “እንግዲህ መቼስ ከዚህ በኋላ ቀንድ አላበቅል…” የምንላት ብሂል አለችን እኛ ኢትዮጵያውያን፡፡ ቻይናውያን ደግሞ ብሂል ሳይሆን በእርግጥም ቀንድ ያበቀለ ሰው አላቸው፡፡





እመት ሊያንግ ዢውሼን መኖሪያቸውን በቻይናዋ ሲሹዋን ያደረጉ የ87 አመት የእድሜ ባለጸጋ አዛውንት ናቸው፡፡ ባልተለመደ መልኩ አናታቸው ላይ ቀንድ ያበቀሉት እማማ ለቻይናውያን ዶክተሮች እንቆቅልሽ ነው የሆኑባቸው፡፡ ዶክተሮች ቀንድ መሆኑን ያረጋገጡት ባእድ አካል መሃል አናታቸው ላይ የበቀለው የ87 አመት አዛውንቷ እመት ሊያንግ ቀንድ ማብቀል የጀመሩት የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ነበር እናም ዛሬ ላይ ቀንዱ 12 ሳንቴሜትር ገደማ የሚረዝም ሆኖ የተገኘ ሲሆን አሁንም ማደጉን አላቆመም፡፡

ከስምንት አመታት በፊት ቀንዱ በበቀለበት የጭንቅላታቸው ክፍል አካባቢ ጥቁር ነገር ነበረ፡፡ በኋላም ቀንዱ መብቀል ሊጀምር ሰሞን ቦታው ላይ ያሳክካቸው የነበረው አዛውንቷ በአካባቢያቸው ባሉ የባህል ህክምና ባለሙያዎች መድሃኒት ቢጤ ተሰጥተዋቸውም ነበር፡፡ መድሃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት ሲያስከትልባቸው ግን ትተውት ነገሩን ችላ ብለውት ነበር የቆዩት፡፡ ከሁለት አመት በፊት ታዲያ ያ ጥቁር የአናታቸው ክፍል ተከፍቶ ቀንዱ መብቀል ሲጀምር ትንሿን ጣት የሚያክልና ቁመቱም ሶስት ሳንቲሜትር ገደማ ነበር፡፡

እማዬ ወደ ሆስፒታል መሄድ አትወድም ሆስፒታል ከሄደች ተመልሳ የምትመጣ አይመስላትም የሚለው የእመት ሊያንግ ልጅ አቶ ዋንግ ዣሆጁን ወደ ሆስፒታል ብንሄድም ዶክተሮቹ የቀንዱን እድገት መመርመር አልቻሉም ነበር ብሏል፡፡ በዚህ አመት መጀመሪያ አካባቢ ዋንግ እናቱን ጸጉራቸውን አያጠበ ሳለ ድንገት መጀመሪያ ላይ በቅሎ የነበረውን ቀንድ መትቶት ነቅሎት የነበረ ቢሆንም በተነቀለው ቀንድ ቦታ እንደ አዲስ መብቀል የጀመረው ቀንድ ከመጀመሪያው ይበልጥ በፍጥነት እያደገ በስድስት ወር ውስጥ ብቻ 12 ሳንቲሜትር ያክል ረዝሟል፡፡ 

የተፈጠረባቸውን ባእድ አካል አስመልክተው የተጠየቁት እማማ ሊያንግ “ህመም አለው… አንዳንዴ አንዲያም እንቅልፍ ይነሳኛል”… ሲሉ ነው ምላሽ የሰጡት፡፡ ነገሩን የመረመሩት ዶክተሮች እመት ሊያንግ የበቀለባቸው ቀንድ ከጭንቅላታቸው ቆዳ ላይ የተነሳ መሆኑን ያረጋገጡ ሲሆን የታማሚዋ የጤና ሁኔታ ታይቶም በቀዶ ጥገና ሊወገድላቸው እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡ ነገር ግን ቀንዱ በከፈተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ መሆኑ ምናልባተም ወደ ካንሰርነት እንዳይለወጥባቸው የሚል ስጋትም አላቸው ዶክተሮቹ፡፡ 

እርግጥ እንዲህ አይነት ክስተቶች ከስንት አንዴ የሚከሰቱ ቢሆንም እማማ ሊያንግ ብቸኛዋ ቀንድ ያበቀሉ ሰው አይደሉም፡፡ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መልኩ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2010ዓ.ም. ቻይናዊቷ 101 አመት የአድሜ ባለጸጋ አዛውንቷ ዣንግ ሩዊፋንግ ግንባራቸው ላይ ቀንድ አብቅለው ነበር፡፡


ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3


No comments:

Post a Comment