Monday, August 31, 2015

የአለም ትልቁ ብረት-ድስት(ጎላ) 50 ኩንታል ሽሮ በአንድ ጊዜ ማንተክተክ ይችላል



ወዳጄ ጎላ ያውቃሉ አይደል!? ይሄ እንደ ሰርግ ላሉ ድግሶች ምግብ የሚዘጋጅበት ትልቅ ብረትድስት፡፡ እንደውም ብዙውን ጊዜ እድሮች አካባቢ አይጠፋም፡፡ እናልዎት ይሄ ትልቅ ብረት-ድስት እንደው እስከ አፉ ጢም ብሎ ወጥ ቢሰራበት ለምን ያክል ሰው የሚበቃ ምግብ ማብሰል ያስችላል ብለው ያስባሉ? በእርግጥ ምላሹን ለማወቅ የሚከብድ ቢሆንም ብቻ እርስዎ እያሰላሰሉት እኔ ቻይናውያን ስለሰሩት የአለም ትልቁ ጎላ ልንገርዎት፡፡
 በቻይናዋ ሁናን ግዛት ዶንግጂያንግ ሀይቅ አካባቢ በአሳ አጥማጆች ፌስቲቫል ላይ ለመሳተፍ የተሰባሰቡት ቻይናውያን የአለም ትልቁ ነው ያሉትን ብረት-ድስት ሰርተዋል፡፡ በአሳ ቅርጽ የሰሩት ይህ ጎላ ታዲያ በእርግጥ የአለም ክብረ ወሰን መዝጋቢ ድርጅት ከአለም አንደኛ ስለመሆኑ አረጋግጦ የምስከር ወረቀት ያልሰጠው ቢሆንም ለአስርሺ ሰዎች የሚሆን የአሳ ሾርባን ማብስል ችሏል፡፡ በፌስቲቫሉ ላይ የታደሙ 10 ሺ ቱሪስቶችም በትልቁ ጎላ ከተሰራው የአሳ ሾርባ ላይ የየድርሻቸውን ወስደው ፉት ብለው አጣጥመዋል፡፡
ወደጎን 11 ሜትር ርዝመት፣ 2 ሜትር ስፋትና ግማሽ ሜትር ቁመት ያለው ይህ ትልቅ ብረት-ድስት ምን ያክል መጠን ያለው ምግብ ማብሰል ይችላል መሰለዎት፡፡ መቼም አምስት ሺ ሲባል ቅድሚያ በፊትዎት ድቅን የሚለው አትሌቶቻችን የሚሮጡት የሩጫ ውድድር አሊያም ደግሞ ብር ሊሆን ይችላል ነገር ግን ይህ ቻይናውያኑ የሰሩት ጎላ በሙሉ አቅሙ 5 ሺ ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ምግብ መስሪያ ልዩ ልዩ ነገሮችን ሲጥ አድርጎ መያዝ እንደሚችል ነው ጎላውን የሰሩት ቻይናውያን የተናገሩት፡፡ ወዳጄ ያስቡት እንግዲህ ነገሩን እንዲያው በሽሮ እናስላው ብንል ብረት-ድስቱ በአንድ ጊዜ 50 ኩንታል ሽሮ ጎርሶ ማንተክተክ ይችላል እንደማለት ነው፡፡

ወዳጆቻችን ቻይናውያን ከአለም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ነው ያሉትን ብረት ድስት ሰርተው በብረት ድስቱ ያበሰሉትን የአሳ ሾርባ አስር ሺ ሰዎችን መግበውበታል፡፡ እናም እንግዲህ ለጎላ ቅርበት ያላችሁ እድሮችና በብረታብረት ዙሪያ ብዙ ብዙ ነገሮችን እየሰራችሁ ያላችሁ ሙያተኞች ቻይናውያኑን የሚያስከነዳ ጎላ በመስራት የአለም ክብረ ወሰንን የመጨበጧን ነገር አስቡባት ብያለሁ፡፡

ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment