ወዳጄ “እንደው ይቺ የኛ የሰው
ልጆች ህይወት በእንስሳትኛ ብትቃኝ ምን ትመስላለች?” የሚል ሀሳብ ሽው ብሎብዎት ያውቅ ይሆን፡፡ ማለት ሰው መሆንዎት ቀርቶ
በግ፣ ፍየል፣ ዶሮ አሊያም ላም ወይ ደግሞ ነብር፤ አንበሳም ብቻ ሌላ “የዱርም ይሁን የቤት እንስሳ ሆኜ ብኖር ህይወት ምን
ትመስል ይሆን?” ብለው አስበው ያውቃሉ፡፡
“ኧረ ምኑን አመጣኸው ደግሞ!..
ምን ያለው የሞኝ ሀሳብ ነው ደግሞ ሰው መሆኔ ቀርቶ በሬ ሆኜ ልኑር የሚያስብል ሀሳብ” ብለው አግራሞት አዘል ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ
ቶማስ ትዌትስ ሊቀየምዎት ይችላልና ይተውት፡፡ “ደግሞ ቶማስ ትዌትስ ማነው?” የሚል ጥያቄ ካነሱ… “እንዴዴ… ቶማስን እስካሁን
አላወቅኩትም እንዳይሉና እሱ ካስደመመኝ በላይ እንዳያስገርሙኝ የሚልዎት ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ቶማስ ፍየሉን አሁኑኑ ይወቁት
በኋላ ደግሞ ምናልባት በአጋጣሚ አግኝተውት ለአመት በአል እንዳያስቡት ይልዎታል፡፡”
ቶማስ ትዌትስ እንግሊዛዊ ተመራማሪ
ነው፡፡ የሚመራመረው ደግሞ ‘የሰው ልጆች የልባቸውን ፍላጎት እንዴት በቀላል ማሳካት ይችላሉ?’.. ‘ምን አይነት የቴክኖሎጂ
ውጤቶችንስ ተጠቅመው የልባቸውን ማድረስ ይችላሉ?’ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ እናልዎት ወዳጄ ቶማስ ፍየል ሆኖ፤ በሰውኛ
ማውራትን ትቶ በ ኧ ኧ ኧ እያለ መኖር ምን እንደሚመስል የማወቅ ልዩ ፍላጎት ነበረው፡፡ ይህን ህልሙን እውን ለማድረግ ሲልም
የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን በመጠቀም እንደ ፍየል በአራት እግሩ እየሄደ፤ ሳር የሚፈጭለትን ሰው ሰራሽ ጨጓራ እላዩ
ላይ በመግጠምም እንደፍየል ሳር እየጋጠ በስዊዘርላንድ ተራራዎች ላይ ከፍየል መንጋ ጋር አብሮ ለሶስት ቀናት ያክል ፍየል ሆኖ
በመኖር የልቡን ፍላጎት አሳክቷል፡፡
“ትናንትን እያስታወሰ ከሚጸጸት፤
ነገን እያሰበ ከሚጨነቅ ሰው ከተሰኘ ፍጡርነት ተገላግዬ፤ የቤት ወይ የዱር እንስሳ ሆኜ አመት በአልን ማሳለፍ ነበር አላማዬ…”
ያለው ቶማስ የተረጋጋና ቀላል ነው ብሎ የሚያምነውንና ተቀጽላ የሆነ ስጋት የሌለበት ነው የሚለውን የእንስሳነት ህይወት ለምን መኖር እንደፈለገ ተናግሯል፡፡ ምንም እንኳ
ቶማስ ይህን ያስብ እንጂ ታዲያ የፍየልነት ህይወትን እንዳሰበው ቀላልና በግድ የለሽነት የሚኖሩት ሆኖ አላገኘውም፡፡ ምክንያቱም
የፍየሎቹን መንጋ ሊቀላቀል በሞከረበት ሰአት እንኳ ቶሎ ተቀባይነትን ከፍየሎቹ ዘንድ አላገኘም፡፡ ፍየል ነው ብለው አምነው
ከተቀበሉት በኋላም እንኳ ከፍየሎቹ እኩል እየወጣ እየወረደ አብሯቸው መጓዝ አልተሳካለትም ነበር፡፡
“የሆነ ሰአት ላይ እኔ ብቻዬን
የተራራው አናት ላይ ቆሜ ዞር ስል ለካስ ሌሎቹ ፍየሎች እታች ቅጠላጠል እየቀጣጠፉ ሲመገቡ ቀርተው እኔን ይመለከቱኛል፤
መጀመሪያ ላይ ምንም አልፈራሁም ነበር በኋላ ላይ ነው ሹልና ቀጥ ቀጥ ያሉ ቀንዶች እንዳሏቸው ያስተዋልኩት ሲል…” በፍየልነቱ
ወቅት የገጠመውን የሚናገረው ቶማስ “እርግጥ ነገሩን በሰውኛ አስቤው ሊሆን ቢችልም… አንድ ብዙውን ጊዜ አብሬው አሳልፍ የነበረ
ፍየል ጓደኛዬ ነገሩን አረጋግቶታል መሰለኝ” ብሏል፡፡ ቶማስ አሁን ላይ የፍየልነት ህይወቱን የሚያስቃኝ የፎቶግራፍ አውደርዕይ
ሊያዘጋጅ እየተሰናዳ ሲሆን ይህንኑ ህይወቱን የሚያስቃኝ መጽሀፍም እያዘጋጀ ነው፤ ‘ፍየሉ ሰው’ በሚል ርእስ፡፡
ወዳጄ የቶማስ ነገር “ወይ ጉ…ድ”
ሳይስብልዎት እንደማይቀር አልጠራጠርም፡፡ ግን እንደው ግርምትዎት እንዳለ ሆኖ እርስዎም የቶማስ ነገር ሽው ቢልብዎት የትኛውን
እንስሳ ሆነው ነው ህይወትን በእንስሳኛ ሊያጣጥሟት የሚፈልጉት? የሆነው ሆኖ የፈለጉትን እንስሳ መስለው ለመኖር ቢሞክሩ
ለመምሰል መሞከርዎት በራሱ እንስሳኛ ሳይሆን ሰውኛ እንደሆነ ግን ልብ ይሏል፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ
ኤም 96.3
No comments:
Post a Comment