Friday, August 28, 2015

60 አመት ሙሉ እየተበላ ዛሬም ድረስ ያላለቀውን ኬክ በንባብ ይቅመሱት

“አንድ ኬክ በልተው ለመጨረስ ምን ያህል ጊዜ ይፈጅብዎታል?” የሚል የዋህ ጥያቄ ቢሰነዘርልዎት እርስዎ ወዳጄ “ምን ያክል ይፈጃል… ያው እንደ ቦታው፣ እንደ ሁኔታውና እንደ ኬኩ መጠን ሊለያይ ይችላል… ማለት ቦታው ሰው የተሰበሰበበት ነው ወይ? ከጓደኞቼ ጋር ነኝ ወይስ ከፍቅረኛዬ ጋር? የሚሉ ጥያቄዎች ነገሩን ይወሰኑታል እንጂ እንዲሁ ለውድድር ነው ቢባል… ይቺ በየካፌው አለቅጥ አንሳ የምትሸጠዋን ጉንጭ የማትሞላ ኬክ ያለ ይሉኝታ ሁለቴ አልጎርሳትም ብለህ ነው!?” የሚል ምላሽ ሊሰጡበት እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡

እርግጥ ነው እንዳሉት የኬኩ መጠን ከሁኔታና ቦታ ጋር ተዳምሮ ኬኩን በልተው የሚጨርሱበትን ቆይታ ሊያረዝመውም ሊያሳጥረውም ይችላል፡፡ ግን “አንድ ኬክ 60 አመት በሙሉ ሳያልቅ ይበላል…” ቢባሉ… “ኬኩ አገር የሚያክል መሆን አለበት! እናስይዝ!” ብለው እንደሚወራረዱ አልጠራጠርም፡፡ ምናልባት የተወራረዱት ከነ እትዬ አን እና ከጋሼ ኬን ጋር ከሆነ ግን በውርርዱ እንደሚሸነፉ ይወቁት፡፡ ምክንያቱም እትዬ አን እና ጋሼ ኬን አገር የሚያክል ኬክ አስጋግረው ሳይሆን ከዛሬ 60 አመት በፊት በትዳር ሲጣመሩ በሰርጋቸው እለት የተጋገረውን ኬክ ነው እስከ ዛሬ ድረስ እየበሉት ያሉት፡፡

የያኔው ጉብል ኬን ፍሬድርክስና ኮረዳዋ አን ፍሬድሪክስ በአንድ ጎጆ ስር በትዳር አብረው ለመኖር ወስነው ድል ባለ ሰርግ የተጋቡት ከዛሬ ስልሳ አመት በፊት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ነሃሴ 19 ቀን 1955 ዓ.ም. ነበር፡፡

የልጅ ልጃቸውን ሰርግ ለማድመቅ ሽር ጉድ ሲሉ የነበሩት የአን አያት ታዲያ ባለ ሶስት ደረጃ ኬክ ጋግረው ለሰርገኞቹ “እነሆ! ትዳራችሁ ይስመር!” ሲሉ ነበር ኬኩን በስጦታ መልክ ያበረከቱላቸው፡፡ እናም ይህን ኬክ ነው እንግዲህ እነ አን እስከ ዛሬ ድረስ እያጣጣሙት ያሉት፡፡ በየአመቱ የተጋቡበትን ቀን በሚያከብሩበት እለት ነው በክብር ካስቀመጡትና ወደፊትም ከሚያስቀምጡት ከዚህ እድሜ ጠገብ ኬክ ላይ እየቆነጠሩ በትዝታ 60 አመታትን ወደኋላ እየተመለሱ የሰርጋቸውን እለት አስበው የሚውሉት፡፡

“በየአመቱ ጠቅልለን ካስቀመጥነበት ቦታ አውጥተን እንፈታዋለን፡፡ ደርቆ ስለምናገኘውም ራስ እንዲል ብራንዲ ፈሰስ እናደርግበታለን… ከዘማ ተወው ቆረስ አድርገን ትዝታን ማጣጣም ነው!!!” የሚሉት እትዬ አን “ይህን ነገር ሰዎች ሲሰሙ በጣም ተገርመው ነው የሚመለከቱን… ልጆቻችንማ እንዴት ስልሳ አመት የሞላውን ነገር ትመገባላችሁ እያሉ ለጤናችን በመስጋት ይጨነቃሉ፡፡ ነገር ግን አንድም ቀን ኬኩ ለህመም ዳርጎን አያውቅም” ሲሉ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሲራከስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪ ሳሉ የተወዳጁት ጋሼ ኬን እና እትዬ አን ከተጋቡ በኋላ መኖሪያቸውን በአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ነው ያደረጉት፡፡ 85ኛ አመታቸውን የደፈኑት ጋሽ ኬን ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ በሙዚቃ መምህርነት ሲያገለግሉ የኖሩ ሲሆን የ81 አመት የእድሜ ባለጸጋ ባለቤታቸው እትዬ አን ደግሞ 27 አመታትን በነርስነት አገልግለዋል፡፡ በትዳር በቆዩባቸው ስልሳ አመታትም ሶሰት ልጆችን አፍርተዋል በርካታ የልጅ ልጆችም አሏቸው፡፡ ስልሳ አመት ያስቆጠረውን ኬክ ባልና ሚሰቱ ቆርሰው ሲመገቡ ታዲያ “እንብላ” የሚል ጥያቄ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው ሲሰነዝሩ “አይ ይቅርብን… ጨርሳችሁታል እኮ” በሚል ማስተባበያ እድሜ ጠገቡን ኬክ ከመቅመስ እንደተቆጠቡ ነው ዛሬ ላይ የደረሱት፡፡

“በተአምር አይቀምሱትም” ሲሉ ልጆቻቸውና የልጅልጆቻቸው ለኬኩ ያላቸውን ፍራቻ ጋሽ ኬን ሲናገሩ “ሁሌም እንዲቀምሱት ብንጠይቃቸውም እሺ አይሉንም” ሲሉ እትዬ አን የጋሽ ኬንን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ “እንጃ ምናልባት ከዚህ ኬክ ጋር አብረን ሳንቀበር የምንቀር አይመስለኝም” የሚል ሀሳብ አክለውበት፡፡

ወዳጄ እናልዎት አንድ ኬክ 60 አመት ጣእሙን እንደያዘ ዛሬም ድረስ  ተበልቶ አላለቀም እነ እትዬ አንና ጋሽ ኬን ቤት፡፡ ምንም እንኳ የነአን ምላስ ኬኩን ይሁን ትዝታቸውን እያጣጣመ እንደሚገኝ ኬኩን ቀምሶ የተናገረ ሰው ባይኖርም ማለት ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ሰርግ ያሰባችሁ ጥንዶች የኬካችሁን ነገር አስቡበት በኔ በኩል ትዳራችሁ ሰምሮ ኬኩም ልክ እንደነ አንና ኬን ሁሉ 60 አመት ይበላ ስል መርቄያለሁ፡፡

ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment