Friday, August 28, 2015

“እድሜ ሌላ መዘነጥ ሌላ…” ጋሽ ገንተር ክራቤንሆፍት

“እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ
እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ…” (ሀይሌ ሩትስ)
 
ድምጻዊው እንዲህ ብሎ ማንጎራጎሩ አያ እርጅና ሲመጣ እንዲሁ ብቻውን ሳይሆን ብዙ ግሳንግሶቹን አስከትሎ፤ በልጅነትና በወጣትነት እንደልብ ሲከወኑ ከነበሩ ድርጊቶች ሊያቆራርጥ መሆኑን ተረድቶት… “እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ…” ማለቱም የአፍላነት አለም፣ የወጣትነት ጊዜ የብዙ ብዙ ነገሮች ማስተናገጃ በመሆኑ ምክንያት ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

እድሜ ገፍቶ ገፍቶ ወደ ማምሻው ሲጠጋ አስቀርቶ ከሚያልፋቸው ብዙ ነገሮች መካከል ዘመን አፈራሽ በሆኑ ልብሶች ተሸቀርቅሮ በየጎዳናው መንፈላሰስ አንዱ እንደሆነ… መቼም የያኔ ወጣቶች የዛሬ አዛውንቶች ምስክርነታቸውን… “እንዴታ!... መጣ የተባለ ፋሽን አይቀረንም ነበር እኮ… እምር ድምቅ ብለን ለመታየት ማን ብሎን!.. ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍራችን አጊጠን በየመንገዱ እንነጎማለል ነበር… የዛሬን አያድርገውና!! እያሉ በትዝታ ወደ ኋላ ተጉዘው የድሮውን እያስታወሱ እንደሚመሰክሩ በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል፡፡

“እድሜ የቁጥር ጉዳይ ነው… ዛሬም ቢሆን እሽቀረቀራለሁ… እርጅና ከነግሳንግሳህ ዘወር በል” ያሉ የሚመስሉት አዛውንቱ ጀርመናዊ አቶ ገንተር ክራቤንሆፍት ሽክ በልክ እያሉ የፋሽኑን አለም ቀልብ ስበውታል፡፡ “ፋሽንን ለወጣት ብቻ ያለው ማነው?.. እኛም እኮ አንድ ሰሞን ወጣት ነበርን… ትተን አልፈንው ነው እንጂ”… በሚል ወኔም ጋሽ ገንተር በተለያዩ አልባሳት አሸብርቀው እየተንጎማለሉ ነው የሚገኙት፡፡

የእድሜያቸው ጉዳይ በተለያዩ ድረገጾች ተለያይቶ 104ም 77 ነው እየተባለ በመገለጽ ላይ የሚገኘው ጋሽ ገንተር ቀለልና ጸዳ ያሉ ልብሶቻቸው ከከለር አመራረጣቸው ጋር ተዳምረው የፋሽኑን አለም ሰው “ኧረ በለውውው…” እያስባሉ የሚገኙ ሲሆን ጅንስ ሱሪ ጃኬትና ኮፍያ እንዲሁም ቦቲ በመባል የሚታወቁትን ከረባቶች አንገታቸው ላይ ሸብ አድርገው ቡትስ ጫማዎችን ነው የሚጫሙት፡፡ ጋሽ ገንተር የዘመኑ ልጆች በመሰል መለኩ ለማጌጥ ጥረው ያልተሳካላቸውን እሳቸው ተዋጥሎቸዋል፡፡

“አለባበሴ ምንም ልዩ ነገር የለውም… ሁሌም እንዲሁ ነው” የሚሉት ጋሼ “ወደ ስራ ስሄድ፣ ስፖርት ስሰራ ብቻ ማንኛውንም ነገር ሳደርግ እራሴን ደስተኛ ሆኜ  ማግኘት ነው የምፈልገው… ለዛም ነው ሁሌ እንዲህ ሽቅርቅር ብዬ የምለብሰው፤ ከውጭ ምትመለከቱት የውስጤ ነጸብራቅ ነው” ሲሉ አለባበሳቸው የውሳጣቸው ደስተኝነት አካል መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ እንዲህ አምረውና ደምቀው መታየታቸው ታዲያ ለአዛውቱ ጋሼ ገንተር ከፋሽኑ አለም ሰዎች ዘንድ የሞዴሊንግ ስራ አስገኝቶላቸዋል፡፡ ሌላ ደስታ ይሏል ደግሞ ይሄ ነው፡፡

ወዳጄ ምናልባት እርስዎም ወጣትነትን ሻገር ያሉ ከሆነና “እንዲህ ነበር እንጂ!.. እንደ ጋሽ ገንተር…” የሚል ምኞት ነገር ነሸጥ ካደረግዎት ምንም ሳያቅማሙ “ምነው በስተርጅና አንቱ… ወደ ፈጣሪ በመቅረቢያ እድሜዎት እንደገና እንደ አንድ ፍሬ ልጅ ፋሽን ፋሽን ይላሉ?” ለሚሉ አስተያቶች ጆሮዎትን ሳይሰጡ አምረውና ደምቀው እርጅናን ያጊጡበት ብያለሁ፡፡ ዋናውና ትልቁ ነገር ግን ጋሽ ገንተር እንዳሉት ውጫዊው ውበት የውስጣችን ነጸብራቅ ነውና በቻሉት መጠን እራስዎትን ደስተኛ ያድርጉት፡፡

ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

No comments:

Post a Comment