ወዳጄ ዌልሳዊ ዜግነት ያለውን ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ን ይተዋወቁት፡፡ ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ አውሮፕላን
አብራሪ ፓይለት ሆኖ አይደለም ካፕቴን መባሉ፡፡ መጠሪያ ስሙም ቦሎቄ አይደለም ነገር ግን ለቦሎቄ ካለው ፍቅር የተነሳ “ይህን ስፍስፍ
የምለለትን የጥራጥሬ ዘር መጠሪያ ስሜ አድርጌው ብጠራበትም ያንስበታል” ብሎ ነው ለራሱ ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ የሚል ስያሜ የሰጠው፡፡
ዌልሳዊው ባሪ ኪርክ ህይወቱን በሙሉ የቦሎቄ ነገር የማይሆንለት፤ ቦሎቄ የሚለው ስም ሲነሳ ቀድሞ አቤት የሚል፤ በጥቅሉ የቦለቄ ፍቅር ያነሆለለው ግለሰብ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ እናም ይህን ፍቅሩን ለመግለጽ ሲል ነው መጠሪያ ስሙን አስቀምጦ ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ የሚል ቅጥል ስም ለራሱ ያወጣው፡፡ ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ ለቦሎቄ ያለውን ፍቅር በዚህ ብቻም አይደለም የገለጸው እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1986ዓ.ም. በመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ቦሎቄ ሞልቶ እራሱን በመዘፍዘፍ 100 ሰአታትን ገንዳው ውስጥ እንዳለ አሳልፎ የአለምን ክብረ ወሰን መያዝ ችሎ ነበር፡፡
እናም ራሰ በራው ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ ባሳለፍነው አመት 60ኛ አመት የልደት ቀኑን ሲያከብር
60 የቦሎቄ ፍሬዎችን በንቅሳት መልክ መላጣው ላይ እንዲሰፍሩ አድርጓል፡፡ “ቦሎቄን አናቴ ላይ መነቀሴ ዘመናትን ላስቆጠረው የቦሎቄ
ፍቅሬ መግለጫ አንድ እርምጃ ጭማሪ ነው” የሚለው ካፕቴን “በዚያ ላይ ደግሞ የትም ቦታ ስሄድ ንቅሳቴን እየተመለከቱ ሰዎች ቦሎቄ
መውደዴን ብቻ ሳይሆን በቦሎቄ እንደተሞላሁም ማየት ይችላሉ” ማለቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ አስነብቧል፡፡
‘ካፕቴን ቦሎቄ’ እንዲህ ማድረጉ ግን እውቅናን ለማትረፍ ብቻ አይደለም፡፡
ከ30 አመት በፊት የራሱ የብቻው ፈጠራ በሆነው ድርጊት የአለምን ክብረ ወሰን ለመስበር ሲነሳ ጎን ለጎን ለበጎ አድራጎት የሚውል
ገንዘብ የማሰባሰብ አላማንም ሰንቆ ነበር የተነሳው፡፡ በወቅቱ ስኬታማ መሆንኑ ተከትሎም ከዛን ጊዜ ጀምሮ ስራውን በፍቃዱ በመልቀቅ
ለሰናይ ምግባር የሚውል ገንዘብ የማሰባስብ ስራ በመስራት ነው ህይወቱን ሲመራ የኖረው፡፡
እናም ስልሳኛ አመቱን ለማክበር በተሰናዳበት ወቅት ታዲያ አንድ
ሀሳብ መጣለት አናቱ ላይ የሚነቀሳቸውን 60 የቦሎቄ ፍሬዎች ለአንዷ ቦሎቄ 2 ሺ ብር የሚጠጋ ዋጋ ቆርጦላት የተለያዩ ተቋማትና
ግለሰቦች ሰፖንሰር እንዲያደርጉት በምትኩም የስማቸውን መጀመሪያ ፊደሎች በቦሎቄዎቹ ላይ እንደሚያሰፍር ጠቅሶ ገንዘብ ማሰባሰብ ይጀምራል፡፡
ማሰባሰብ የቻለውን 115 ሺ ብር ገደማ በወሊድ ወቅት በሚከሰት የአንጎል መጎዳት የሚፈጠር ጡንቻዎችን ማዘዝ ያለመቻል ህመም ሴሬብራል
ፓልሲ ለተጠቃችው የ3 አመት ህጻን መታከሚያ ይውል ዘንድ ለግሷል፡፡
የህጻኗ አያቶች ጋሼ አለንና እትዬ ሮበርትስም ጥቂት ቦሎቄዎችን
ስፖንሰር አድርገው ስማቸውን በ’ካፓቴን ቦሎቄ’ አናት ላይ ያሰፈሩ ሲሆን “ካፕቴን እኛ ጋር መጥቶ ይህን የእብደት የመሰለ ሀሳቡን
ነገረንና እኛም ተስማማንበት” ያሉት እትዬ ሮበርትስ “አሁን ላይ ካፕቴን ቦሎቄን ልክ እንደ ቤተሰባችን ነው፤ የምንቆጥረው በጣም
ገራሚ ሰው ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ወዳጄ ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ እንግዲህ ለቦሎቄ ያለው ፍቅር እንዳለ ሆኖ
ይህን ፍቅሩን ለበጎ ምግባርም እያዋለው ይገኛል፡፡ እንግዲህ ይህ የጤና መጓደል ነገር እዚህ እኛም ሀገር አለና በመሰል መልኩ ታክሞ
ለመዳን አቅም ያነሳቸውን ወገኖች ለመርዳት መኪናውን ለሽያጭ ካቀረበው አርቲስት ሰለሞን ቦጋለም ከ‘ካፕቴን ቦሎቄም’ መልካምነትን
ተምረን የተቸገሩን ለመርዳት አቅም በፈቀደ መጠን የቻልነውን እናደርግ ዘንድ መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3
No comments:
Post a Comment