ወዳጄ ያለመገጣጠም ነገር ሆኖብኝ እስከ ዛሬ ድረስ ድንቃድን መረጃዎችን ስነግርዎት የነበረው
በኮምፒውተር መስኮት በተለያዩ ድረገጾች አለምን እየዳሰስኩ ያገኘዋቸውን ነበር፡፡ የሀገራችንን ነገር ባልዘነጋውምና፤ ብዙ ድንቃድንቅ
ነገሮች እዚሁ አኛ ሀገር እንደ ጉድ እንደሚከናወኑ ባላጣው ያለመገጣጠም ሆኖብኝ ነው እንግዲህ፡፡ ምናልባት እርስዎም “ምነው ውጭ
ውጭውን ብቻ!... አገር ውስጥ አጀብ የሚያሰኝ ነገር ጠፍቶ ነው!? ብለው ታዝበውኝም ይሆናል፡፡
እነሆ ለዛሬ ታዲያ ወደ ውጭ ሳላማትር፤ እዚሁ አዲስ አበባችን ላይ፤ በሚያደርጋቸው ነገሮች
ብዙዎችን እያስደመመ የሚገኘውን ወጣት አምሳሉ ከበደ ላስተዋውቅዎት ወድጃለሁ፡፡ መቼም እርስዎ ወዳጄ የጥርስ ነገር ቢነሳብዎት፤
ጥርስ ምግብን ከመሰለቂያነቱ ባለፈ የደስታዎት መገለጫ፤ ፈገግ ሲሉበት ደግሞ ውበትዎ እንደሆነ ነው ሊናገሩ የሚችሉት፡፡ ምናልባት
ደግሞ የጥርስ ህመም ትዝታ ካለዎትም እሱን ያጫውቱኝ ይሆናል፡፡
የ30 አመቱ ወጣት አምሳሉ ከበደ ግን ጥርስን ከፈገግታና ምግብን ከማድቀቂያነት ባለፈ መኪናን ያክል ነገር ለመጎተት እየተጠቀመበት በርካቶችን አጀብ እያሰኘ ይገኛል፡፡ “እንደው የውጪውን አለም ስታስስ እኮ ‘በእጅ የያዙት…’ አይነት ነገር ሆኖ እኔን የመሳሰሉ የብዙዎችን ችሎታ እስከዛሬ አላስቃኘህንም”
ሲል የምሰራበት መስሪያ ቤት፤ አዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ(አዲስ ቴሌቪዥን፣ ኤፍኤም 96.3)፤ ጎራ ያለው ወጣት አምሳሉ፤
“ጥርሶቼን ተጠቅሜ መኪና እጎትታለገሁ” አለኝ፡፡
እኔኛ የስራ ባልደረቦቼም
“ለስራ ወዲያ ወዲህ የምንልባትን የመስሪያ ቤታችንን መኪና ‘በል እስቲ ችሎታህን አሳየን’” ስንል ከገመድ ጋር አብረን ሰጠነው፡፡
ገመዱን መኪናዋ ላይ ቋጥሮ፤ እስከዛሬ “ነዳጅ ፉት ካላልኩ ወዴትም አልሄድም” ስትል የኖረችዋን መኪና “የኔ ጥርስ እያለ ነዳጅ
ለምን ሲባል!” ብሎ በጥርሱ ገመዱን ነክሶ ወደፊት አየጎተተ አስኪዷታል፡፡
ይህም ብቻ አይደል ታዲያ
አንድ
ወጣት ወይም ጎልማሳ ሰው በሁለት እጆቹ ጨብጦ ይዞ ለመሄድ የሚያዳግተውን፤
ሁለት በውሃ የተሞሉ ባለ 25 ሊትር የዘይት ጀሪካኖች፤ አምሳሉ እንዲሁ እንደ ቀላል ነገር በጥርሶቹ ነክሶ ወደላይ አንስቷቸው ወዲያ
ወዲህ ራመድ ራመድ እያለ ካሜራችንን ደግነን በቦታው ለቆምነው ለኛ እና ሌሎችም በቦታው ለነበሩ ሰዎች ድንቅ ብቃቱን አሳይቶናል፡፡
ኑሮውን አዲስ አበባ ላይ ከመሰረት 5 አመታትን ያስቆጠረው አምሳሉ ተወልዶ ያደገው ሃዋሳ ከተማ ላይ ነው፡፡
ከአራት አመታት በፊት እንዲህ ከበድ ያሉ ነገሮችን በጥርስ የማንሳቱን ነገር መሞከር እንደጀመረ የሚናገረው አምሳሉ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ
ስፖርት ያዘወትር እንደነበርና ጠንካራ ጥርሶቹ ተፈጥሮ የቸረችው እንደሆኑ ነው የሚናገረው፡፡ “ጥርሶቼን ለማጠንከር ስል በተለየ
የማደርገው ነገር የለምም” ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ጥርሶቹ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ስኳር የበዛባቸውና በጣም ትኩስ የሆኑ ነገሮችን
ጨምሮ ጫትን የመሳሰሉ ጥርስን የሚጎዱ ነገሮችን እንደማይጠቀም ነው የነገረኝ፡፡
ከባድ እቃዎችን በጥርሱ ሲያነሳ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ጉዳት እንዳላጋጠመው የሚናገረውና አይሱዙ በመባል
ከሚታወቀው መካከለኛ መኪና በታች የሆኑ መኪናዎችን በጥርሱ፤ ከባድ መኪናዎችን ደግሞ በገመድ ወገቡ ላይ አስሮ የመጎተት ብቃት እንዳለው
የሚናገረው አምሳሉ፤ 50 ኪሎ የሚመዝን ማንኛውንም ነገር ደግሞ በጥርሱ ነክሶ ደረጃዎችን መውጣትና መውረድ ለሱ ቀላል እንደሆነም
ነግሮኛል፡፡
“ወደ ፊት ደግሞ ችሎታዬን በደንብ አዳብሬ በቅርቡ ስራ የጀመረውን ባቡር እና አውሮፕላንም በገመድ አስሬ በጥርሴ
የመጎተት ህልም አለኝ” የሚለው ወጣት አምሳሉ በተለያዩ ፊልሞች ላይ የሚታዩ አስቂኝ ድርጊቶችን አስመስሎ የመተወን ብቃትም አለኝ
ብሏል፡፡ “ይሁንና እነዚህን ችሎታዎቼን አንዳንድ ጊዜ ሰው በተሰበሰበባቸው ቦታዎች ላይ እያሳየሁ ትንሽ ገንዘብ እያገኘው ነው ህይወትን
የምመራው እንጂ ቋሚ የሆነ የገቢ ምንጭ የለኝም” ሲልም ነው የነገረኝ፡፡
ወዳጄ እንግዲህ ወጣት አምሳሉ በጥርሱ መኪና መጎተቱ አንድም ተፈጥሮ ለጥርሶቹ በለገሰቻቸው ጥንካሬ በሌላ በኩል
ደግሞ ስፖርታዊ እንቅስቃሴና ለዚሁ ተግባር የሚረዱትን ልምምዶች በማድረጉ ነው፡፡ እናም እርስዎ ወዳጄ እንዲህ ያለውን ድርጊት መሞከር
ለጉዳት ሊዳርግዎት ይችላልና እንዳይሞክሩት መልእክቴ ነው፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍኤም 96.3
We are really grateful for your blog post. You will find a lot of approaches after visiting your post. Great work.
ReplyDeleterental mobil cibinong bogor