Friday, September 25, 2015

አለቅጥ ውፍረት ከስፖርት ያልገደባት 108 ኪሎ የመትመዝን ወጣት፤ ቫለሪ ሳጉን

ወዳጄ መቼም የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የሰውነት ውፍረት አይጥና ድመት እንደነሆኑ፤ ስፖርት ባለበት ውፍረት ዝር ማለት እንደማይወድ አያጡትም፡፡ “ይሄ ነገር እንዲሁ ብሂል ነው፤ ውፍረትና ስፖርትን ሳይጣሉ አንድ ላይ ማስኬድ ግጥም አድርጎ ይቻላል” የምትለው አሜሪካዊት፤ ወፍራሟ ቫለሪ ሳጉን፤ ፈረንጆቹ ዮጋ ሲሉ የሚጠሩትንና ትውልዱ ከወደሩቅ ምስራቅ የሆነውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማዘውተር የተካነች ናት ይላል ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ያስነበበው ዘገባ፡፡
በብዙዎች ዘንድ ይሄ ዮጋ የተባለ፤ አካልንና መንፈስን ያጣመረ፤ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለሸንቃጦች ብቻ ነው የሚለውን የከዚህ ቀደም እሳቤ ፉርሽ ያደረገችው የሳንፍራንሲስኮዋ ድንቡሽቡሽ ቫለሪ ሳጉን ላለፉት ሶስት አመታት አይደለም አለቅጥ በወፈሩ ሰዎች ይቅርና በሸንቃጦች እራሱ የማይሞከሩ ከባባድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ያለምንም ችግር አቀላጥፋ ስትከውን በካሜራ አይን ውስጥ ገብታለች፡፡
‘ኢንስታግራም’ በተባለው የማህበራዊ ትስስር ድረገጽ ላይ 80 ሺ የሚጠጉ አድናቂዎችና ተከታዮችን ያፈራቸው፤ ለአይን ሞልታ የምትታየው፤ ቫልሪ በየጊዜው ዮጋ ስፖርትን እየሰራች የምትቀረጻቸውን ቪዲዮዎች ለአድናቂዎቿ ታጋራለች፡፡ “አድናቂዎቼና ተከታዮቼ ምናልባት ‘በአካል ቅርጽ ከማይመሳሰለን ሰው እንዴት ትምህርት እንወስዳለን’ የሚል እሳቤ እንዳያድርባቸው ማረጋገጥ ነው ፍላጎቴ” የምትለውና 108 ኪሎ የምትመዝነው ቫለሪ “ሁላችንም፤ ማለትም ወፍራምም ሆንን ቀጭን፤ ከአካላችን ጋር ቅሬታ ሊኖረን ይችላል… ግን ዋናው ነገር ወደ ራሳችን መመልከትና ያለንን ነገር መውደድ ነው!” ስትል ትመክራለች፡፡
የዛሬ አራት አመት ገደማ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለች ዮጋ ስፖርትን ማዘውተር የጀመረችው የ27 አመቷ ቫለሪ “ምንም እንኳ ስፖርቱን ብወደውም… የመጀመሪያው ቀን ከባድ እንደሚሆንብኝ ተረድቼው ነበር… አስተማሪዬ ግን ሁሌም ያበረታታኝ ነበር” ስትል ነው የተናገረችው፡፡ የኋላኋላ ስፖርቱን እየለመደችው ስትሄድ ግን ለወትሮው ያስጨንቃት የነበረው ውፍረቷን የመቀነስ ሀሳቧ እየተመናመነ እየተመናመነ ሄዶ በመጨረሻም ሊጠፋ ችሏል፡፡
“‘ወፍራሞች አንዳንድ ነገሮችን በአግባቡ መከወን አይችሉም! ቀጠንጠን ብሎ መገኘት ብቻ ነገሮችን እንደ ልብ መከወን ያስችላል!’ ብዬ በአእምሮዬ የጫንኩትን ሀሳብ ዮጋ ስፖርትን በደንብ ሳዳብር ከናካቴው እርግፍ አድርጌ ከጭንቅላቴ አውጥቼዋለው” የምትለው ቫለሪ፤ “ዮጋ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመጀመሬ በፊት ‘ወፍራም ነኝ! አልችልም!’” በሚል ፍራቻ ብቻ ብዙ እድሎች እንዳመለጧት ትናገራለች፡፡ ያኔ ጓደኞቿ ሲዘሉና ሲቦርቁ እሷ የዳር ተመልካች ሆና የኖረችው ቫለሪ፤ እድሜ ለዮጋ፤ ዛሬ ላይ ከልብ የምትወደውን የሰማይ ዝላይ ሳይቀር መከወን ችላለች፡፡
ሁሌም በስፖርቱ አዳዲስ ነገሮችን መሞከር የምትፈልገው ቫለሪ “ዮጋ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከማዘውተሬ በፊት እራሴን አላውቅም ነበር ማለት ይቻላል ምስጋና ለዮጋ ይሁንና ዛሬ ነገሮች ተቀይረዋል፤ ዮጋ የአእምሮና የቀና አስተሳሰብ ጉዳይ ነው” ስትልም ነው የምትናገረው፡፡ ልምዷን ለአለም ማጋራቷም ለበርካቶች መነቃቃትን እንደፈጠረና ወደፊት ደግሞ የስፖርቱ አሰልጣኝ በመሆን በርካቶች ልክ እንደሷ በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩ የማስተማር ፍላጎትም እንዳላት አክላለች፡፡
ወዳጄ እንግዲህ መቼም ከቫልሪ ብዙ ነገር መማር እንደሚቻል ምንም ጥርጥር የለው፡፡ እርግጥ ነው ውፍረት ለብዙ ተላላፊ ያልሆኑ የጤና ችግሮች የሚዳርግ ነውና አካላችንን የተስተካከለ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ወፍራምም ሆንን ቀጭን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ደግሞ ጤናማ ህይወትን መምራት ያስችለናልና ስፖርትን ብናዘወትር ተጠቃሚነታችን በብዙ መልኩ ነው፡፡ ሌላውና ትልቁ ከቫለሪ መማር የምንችለው ነገር እራሳችንን በተመለከተ ቀና አመለካከት ማዳበርን፤ ያለንን ነገር ከመጥላት ይልቅ በራስ መተማመንን አጎልብተን ባለን ነገር ላይ በመመርኮዝ የተሻለ ነገር መስራትና እራሳችን መለወጥ እንደምንችል ነው፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

8 comments: