Tuesday, September 29, 2015

እንዲህም አድርጎ መንገድ ማቋረጥ አለ

ወዳጄ እንደው በስከዛሬው ህይወትዎ የመኪና መንገድ ሲያቋርጡ መንገዱን ተግረው ለመጨረስ በጣም ትንሽ እርምጃ ተራመዱ ቢባል ስንት እርምጃ ይሆን የፈጀብዎት? አለ አይደል እንደው የእግርዎትን አጣጣል ሰፋ ሰፋ አድርገው እመር እመር እያሉ ተራመዱ ወይም ሮጡ እንበል፤ ወይ ደግሞ ከቻሉ ተለባብጠው አክሮባት እየሰሩም ይሁን ብቻ ግን አስፓልቱን ለመሻገር ስንት እርምጃ ወይም ግልብጫ ይፈጅብዎታል? ጥያቄ ይሁንዎትና እኔ ከመኪና መንገድ አንድ ጠርዝ ተግሮ በዚያኛው ጥግ ለመቆም አንዴ ብቻ እንጣጥ ያለውን እንግሊዛዊ ላስተዋውቅዎት፡፡

ሀገረ እንግሊዝ ለንደን ውስጥ ነው ይላል ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል ድረገጽ፡፡ ኮኖር ኮንትሪክስ የተባለ ተገለባባጭ ወይም አክሮባተኛ ወጣት ነው፡፡ እና እዛ ለንደን መሀል በሚገኝ ጎዳና ላይ ከጓደኞቹ ጋር የተከሰተው ኮኖር 5 ሜትር ገደማ ስፋት ያለውን የመኪና መንገድ ለማቋረጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የዘለለው፡፡ ተንደርድሮ ከአስፓልቱ አንደኛው ጫፍ ላይ ተስፈንጥሮ የተገለበው ኮኖር በሰማይ ተንሳፎ ማረፊያውን ያደረገው ከመንገዱ በዚያኛው ጥግ ካለ የእግረኞች መንገድ ላይ ነው፡፡
ወዳጄ በእርግጥ ኮኖሮ ያለውን ድንቅ ብቃት ተጠቅሞ በአንድ ግልብጫ ብቻ እንዲህ የመኪና መንገድ ማቋረጥ መቻሉ የሚደነቅ ቢሆንም በቅድሚያ ልምምድ አድርጎ እንዲሁም ደግሞ መኪና አለመኖሩን አረጋግጦና ጥንቃቄ አድርጎ ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

እናም እርስዎ ወዳጄ የኮኖር ልዩ ችሎታ አድንቆ ከማለፍ በዘለለ አንድም የትም ቦታ ቢሆን እንዲሁ ያለልምምድ ተነስተው ልገልበጥ እንዳይሉ ምክንያቱም ከመሰበር አንስቶ እስከሞት የሚዳርግ አደጋ ያስከትላልና ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ መኪና መንገድን አይደለም እንዲህ ተገልብጦ ማቋረጥ በአግባቡ እየተራመዱም ቢሆን ጥንቃቄ ካላደረጉ አደጋው የከፋ ነውና እራስዎትን ከመኪና አደጋ ጠብቀው ለራስዎት፣ ለሚወዷቸውና ለሚወዱዎት ሁሉ በጤናና በህይወት ቆይተው ብዙ ብዙ ማድረግ እንዲችሉ በተገቢው ቦታ ተጠንቅቀው መንገድ ያቋርጡ መልእክቴ ነው፡፡

ዳንኤል ቢሠጥ

መበየጃ ማሽንን እንደ ብሩሽ፣ ብረትን እንደ ሸራ ተጠቅሞ የሚስለው ወጣት

ወዳጄ ብየዳ ያውቃሉ አይደል፤ ብረት እየተቆረጠና እየተቀጠለ የተለያዩ ነገሮች የሚሰሩበትን ሙያ! መቼም እስከዛሬ በር ሊያሰሩም ይሁን የአልጋ ብረት ሊያስበይዱ ወይ ደግሞ የሚዘውሯት መኪናም ካለችዎት እሷን ለማስጠገን ወይም በሌላ አጋጣሚ ከብየዳ ጋር ተገናኝተው እንደሚሆን እርግጥ ነው፡፡ ምናልባት የብየዳ ሙያተኛ ከሆኑ ደግሞ ያው ብየዳ ከእለት ተእለት እንቅስቃሴዎት ጋር የተገናኘ ነው ማለት ነው፡፡ እናልዎት ታዲያ የብየዳ ነገር ሲነሳ የሚታወቀው፤ ብረት የተፈለገውን ቅርጽ እንዲይዝ ተደርጎ በእሳት ሲጠበስ ነው እንጂ በብየዳ ‘ስእል’ ይሳላል ‘ቅርጻ ቅርጽ’ ይሰራል ቢባል ለማመን እንደሚያዳግት አልጠራጠርም፡፡
እናማ ወዳጄ “አንድ የብየዳ ባለሙያ ስእል ይስላል” ቢባሉ “ታዲያ ምን ችግር አለው… ሁለት ሙያ አለው ማለት ነዋ! መቼም የሚስለው በትርፍ ጊዜው ነው” ብለው ሊመልሱ ይችላሉ “ኧረ የለም እንደሱ አይደለም እዚያው እየበየደ ነው ስእል የሚስለው… ማለት መበየጃውን እንደ ብሩሽ ብረቱን እንደ ሸራ ተጠቅሞ ነው ብረት ላይ በተለያዩ ቀለማት የተዋቡ የጥበብ ስራዎችን የሚሰራው” ቢባሉ ደግሞ “ይሄማ በጭራሽ ሊሆን አይችልም!” ብለው መከራከርዎት አይቀርም ምክንያቱም አንድም ብረት ወረቀት እንዳልሆነና መበየጃ ማሽን እሳት እንጂ ቀለም እንደማይተፋ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በሌላ በኩል ደግሞ ሪቻርድ ላውትን አያውቁትምና ነው፡፡

ሪቻርድ ላውት መኖሪውን በአሜሪካ ቺካጎ ውስጥ ያደረገ የ23 አመት ወጣት ነው፡፡ ጥበብ “ሪቻርድውው…” ብላ ጮክ ብላ የጠራችው ሪቻርድ የብየዳ ማሽንና ብረትን ብቻ ተጠቅሞ ለየት ያሉ፤ በተለያዩ ቀለማት የተዋቡ ስእሎችንና ቅርጻ ቅርጾችን አስጊጦ በመስራት የተካነ ሙያተኛ ነው፡፡ በእርግጥ በስራው ኢንጂነር ቢሆንም ሪቻርድ “የለም እኔ የብየዳ ጥበበኛ ነኝ” ሲል ነው የሚናገረው፡፡ ከስራው የሚተርፈውን ጊዜ ብረት ላይ በመጠበብ የሚያሳልፈው ሪቻርድ ከብረት ውስጥ ጥበብን ፈልፍሎ ማውጣት እጅጉን እንደሚያስደስተውም ይናገራል፡፡

ሪቻርድ መበየጃ ማሽንን እንደ ብሩሽ፤ ማሽኑ የሚተፋውን እሳት እንደ ቀለም፤ ብረትን ደግሞ እንደ ሸራ ተጠቅሞ ከሚሰራቸው የጥበብ ስራዎች መካከከል የተለያዩ እንስሳት አምሳያዎችና በእለት ተእለት የህይወት ኡደት ውስጥ የምንገለገልባቸው ቁሳቁሶች የሚጠቀሱ ሲሆን በተለያዩ ፊልሞች ላይ ያሉ ታዋቂ ገጸባህርያትንም በብየዳ ጥበብ ብረት ላይ ስሏቸዋል፡፡ እንደ ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ዘገባ፡፡


ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍኤም 96.3

Sunday, September 27, 2015

ኢትዮጵያዊው ወጣት በጥርሱ መኪና ጎተተ፤ ውሃ የተሞሉ ባለ 25 ሊትር 2 የዘይት ጀሪካኖችንም አንድ ላይ በጥርሱ አንሰቶ ወዲያ ወዲህ ተራምዳል፡፡

ወዳጄ ያለመገጣጠም ነገር ሆኖብኝ እስከ ዛሬ ድረስ ድንቃድን መረጃዎችን ስነግርዎት የነበረው በኮምፒውተር መስኮት በተለያዩ ድረገጾች አለምን እየዳሰስኩ ያገኘዋቸውን ነበር፡፡ የሀገራችንን ነገር ባልዘነጋውምና፤ ብዙ ድንቃድንቅ ነገሮች እዚሁ አኛ ሀገር እንደ ጉድ እንደሚከናወኑ ባላጣው ያለመገጣጠም ሆኖብኝ ነው እንግዲህ፡፡ ምናልባት እርስዎም “ምነው ውጭ ውጭውን ብቻ!... አገር ውስጥ አጀብ የሚያሰኝ ነገር ጠፍቶ ነው!? ብለው ታዝበውኝም ይሆናል፡፡
እነሆ ለዛሬ ታዲያ ወደ ውጭ ሳላማትር፤ እዚሁ አዲስ አበባችን ላይ፤ በሚያደርጋቸው ነገሮች ብዙዎችን እያስደመመ የሚገኘውን ወጣት አምሳሉ ከበደ ላስተዋውቅዎት ወድጃለሁ፡፡ መቼም እርስዎ ወዳጄ የጥርስ ነገር ቢነሳብዎት፤ ጥርስ ምግብን ከመሰለቂያነቱ ባለፈ የደስታዎት መገለጫ፤ ፈገግ ሲሉበት ደግሞ ውበትዎ እንደሆነ ነው ሊናገሩ የሚችሉት፡፡ ምናልባት ደግሞ የጥርስ ህመም ትዝታ ካለዎትም እሱን ያጫውቱኝ ይሆናል፡፡
30 አመቱ ወጣት አምሳሉ ከበደ ግን ጥርስን ከፈገግታና ምግብን ከማድቀቂያነት ባለፈ መኪናን ያክል ነገር ለመጎተት እየተጠቀመበት በርካቶችን አጀብ እያሰኘ ይገኛል፡፡እንደው የውጪውን አለም ስታስስ እኮበእጅ የያዙት…’ አይነት ነገር ሆኖ እኔን የመሳሰሉ የብዙዎችን ችሎታ እስከዛሬ አላስቃኘህንም” ሲል የምሰራበት መስሪያ ቤት፤ አዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ(አዲስ ቴሌቪዥን፣ ኤፍኤም 96.3)፤ ጎራ ያለው ወጣት አምሳሉ፤ “ጥርሶቼን ተጠቅሜ መኪና እጎትታለገሁ” አለኝ፡፡
እኔኛ የስራ ባልደረቦቼም “ለስራ ወዲያ ወዲህ የምንልባትን የመስሪያ ቤታችንን መኪና ‘በል እስቲ ችሎታህን አሳየን’” ስንል ከገመድ ጋር አብረን ሰጠነው፡፡ ገመዱን መኪናዋ ላይ ቋጥሮ፤ እስከዛሬ “ነዳጅ ፉት ካላልኩ ወዴትም አልሄድም” ስትል የኖረችዋን መኪና “የኔ ጥርስ እያለ ነዳጅ ለምን ሲባል!” ብሎ በጥርሱ ገመዱን ነክሶ ወደፊት አየጎተተ አስኪዷታል፡፡
ይህም ብቻ አይደል ታዲያ አንድ ወጣት ወይም ጎልማሳ ሰው በሁለት እጆቹ ጨብጦ ይዞ ለመሄድ የሚያዳግተውን፤ ሁለት በውሃ የተሞሉ ባለ 25 ሊትር የዘይት ጀሪካኖች፤ አምሳሉ እንዲሁ እንደ ቀላል ነገር በጥርሶቹ ነክሶ ወደላይ አንስቷቸው ወዲያ ወዲህ ራመድ ራመድ እያለ ካሜራችንን ደግነን በቦታው ለቆምነው ለኛ እና ሌሎችም በቦታው ለነበሩ ሰዎች ድንቅ ብቃቱን አሳይቶናል፡፡
ኑሮውን አዲስ አበባ ላይ ከመሰረት 5 አመታትን ያስቆጠረው አምሳሉ ተወልዶ ያደገው ሃዋሳ ከተማ ላይ ነው፡፡ ከአራት አመታት በፊት እንዲህ ከበድ ያሉ ነገሮችን በጥርስ የማንሳቱን ነገር መሞከር እንደጀመረ የሚናገረው አምሳሉ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ ስፖርት ያዘወትር እንደነበርና ጠንካራ ጥርሶቹ ተፈጥሮ የቸረችው እንደሆኑ ነው የሚናገረው፡፡ “ጥርሶቼን ለማጠንከር ስል በተለየ የማደርገው ነገር የለምም” ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ጥርሶቹ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ስኳር የበዛባቸውና በጣም ትኩስ የሆኑ ነገሮችን ጨምሮ ጫትን የመሳሰሉ ጥርስን የሚጎዱ ነገሮችን እንደማይጠቀም ነው የነገረኝ፡፡
ከባድ እቃዎችን በጥርሱ ሲያነሳ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ጉዳት እንዳላጋጠመው የሚናገረውና አይሱዙ በመባል ከሚታወቀው መካከለኛ መኪና በታች የሆኑ መኪናዎችን በጥርሱ፤ ከባድ መኪናዎችን ደግሞ በገመድ ወገቡ ላይ አስሮ የመጎተት ብቃት እንዳለው የሚናገረው አምሳሉ፤ 50 ኪሎ የሚመዝን ማንኛውንም ነገር ደግሞ በጥርሱ ነክሶ ደረጃዎችን መውጣትና መውረድ ለሱ ቀላል እንደሆነም ነግሮኛል፡፡
“ወደ ፊት ደግሞ ችሎታዬን በደንብ አዳብሬ በቅርቡ ስራ የጀመረውን ባቡር እና አውሮፕላንም በገመድ አስሬ በጥርሴ የመጎተት ህልም አለኝ” የሚለው ወጣት አምሳሉ በተለያዩ ፊልሞች ላይ የሚታዩ አስቂኝ ድርጊቶችን አስመስሎ የመተወን ብቃትም አለኝ ብሏል፡፡ “ይሁንና እነዚህን ችሎታዎቼን አንዳንድ ጊዜ ሰው በተሰበሰበባቸው ቦታዎች ላይ እያሳየሁ ትንሽ ገንዘብ እያገኘው ነው ህይወትን የምመራው እንጂ ቋሚ የሆነ የገቢ ምንጭ የለኝም” ሲልም ነው የነገረኝ፡፡

ወዳጄ እንግዲህ ወጣት አምሳሉ በጥርሱ መኪና መጎተቱ አንድም ተፈጥሮ ለጥርሶቹ በለገሰቻቸው ጥንካሬ በሌላ በኩል ደግሞ ስፖርታዊ እንቅስቃሴና ለዚሁ ተግባር የሚረዱትን ልምምዶች በማድረጉ ነው፡፡ እናም እርስዎ ወዳጄ እንዲህ ያለውን ድርጊት መሞከር ለጉዳት ሊዳርግዎት ይችላልና እንዳይሞክሩት መልእክቴ ነው፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍኤም 96.3

Saturday, September 26, 2015

የካርቶን ጦርነት…

ወዳጄ መቼም አለማችን በየጥጋጥጉና በዱር በገደሉ የጦርነት አውድማ ከሆነች ስለመሰነባባቷ በየእለቱ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች የምንሰማቸውና የምናያቸው ጦርነት ተኮር መረጃዎች  ምስክር ናቸው፡፡ ግን እስከዛሬ ከሰሟቸው የተደረጉና እያተደረጉ ያሉ ጦርነቶች መካከል ስለ ካርቶን ጦርነት የሰሙት ነገር አለ እንዴ!? “ደግሞ የምን የካርቶን ጦርነት ነው!?.. ካርቶንን ስናውቀው እቃ መሸከፊያ ሆኖ ነው እንጂ መቼ ነው ደግሞ ጦርነት የሆነው!?” የሚል አግራሞት አዘል ጥያቄ እንደሚሰነዝሩ አያጠራጥርም፡፡
እርግጥ ነው ካርቶን እስከዛሬ በተለያዩ መጠኖችና ቅርጾች እየተዘጋጀ አቅሙ የፈቀደለትን እቃ የሚሸከም፤ ከወፍራም ወረቀት የተሰራ ስልቻ ሆኖ ነው የሚታወቀው፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ካርቶን የጦርነት አውድማ ማድመቂያ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል የሚለው ኦዲቲሴንትራል ድረገጽ አይዞዎት የካርቶን ጦርነት ሰው የሚያልቅበት ሳይሆን ተሰብስቦ እየተዝናና የሚደሰትበት ጦርነት ነው ሲል አስነብቧል፡፡
የካርቶን ጦርነት መነሻውን ከአውስትራሊያ ቢያደርግም ዛሬ ላይ በበርካታ የአለም ክፍሎች የሚከወን ልዩ መዝናኛ እየሆነ መጥቷል፡፡ የካርቶን ጦርነት መነሻ ሀሳብ በፈረንጆቹ አለም ያሉ ህጻናት በካርቶን የሚሰሩ ሽጉጦችን በመጠቀም የሚጫወቱተን፤ ልክ እዚህ እኛ ሀገር ‘ሸራብ-ሸራብ’ እያሉ ህጻናት ቆርኪ ቀጥቅጠውና ጭቃ ጠፍጥፈው በሰሯቸው ሽጉጦች እየተደባበቁ ‘ተኮስኩብህ’ ‘ገደልኩህ’ እየተባባሉ እንደሚጫወቱት ካለ የጨዋታ ሀሳብ መበነሳት ሲሆን ጨዋታው በዘመነ አቀራረብና ባደገ መልኩ ነው በጦርነቱ ላይ የሚተገበረው፡፡
የካርቶን ጦርነት ሀሳብ የተጠነሰሰው ታዲያ በአውስራሊያውያኑ ጓደኛማቾች ሆስ ሲጌል እና ሮስ ኮገር እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2002 ዓ.ም ነበር፡፡ አንድ ሁለት እያሉ ሲዝናኑ ሀሳቡን ያፈለቁት ጓደኛማቾቹ በግቢያቸው ውስጥ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ሆነው የካርቶን ጦርነት ማካሄድን ይጀምራሉ፡፡ በተለያ ጊዜያት በሚያደርጓቸው ጦርነቶች ላይ ታዲያ የካርቶን መሳሪያዎቹ አይነትና ጥራት እያደገ እያደገ ሄዶ ካርቶኖቹ የግቢያቸውን የመያዝ አቅም ሲፈታተኑት ጦርነቱን አደባባይ ይዘውት ለመውጣት ይወስኑና በአካባቢቸው ወዳለው መናፈሻ አምርተው እነሱ ቦክሲንግ ዴይ ሲሉ በሚጠሩት የፈረንጆች ታህሳስ 26 ቀን በመናፈሻው ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የካርቶን ጦርነትን ዘደረጉ፡፡ በወቅቱም ድርጊታቸው የበርካቶችን ቀልብ መሳብ በመቻሉ እነሆ ከዚያን ጊዜ አንስቶ የካርቶን ጦርነት በየአመቱ እየተካሄደ፤ በመላው አውስትራሊያና በተለያዩ የአለም ክፍሎች ከቦክሲንግ ዴይ ባለፈም በተለያዩ ክብረ በአሎች ላይ በበርካቶች ዘንድ እየተተገበረ ዛሬ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡
የካርቶን ጦርነት ተፋላሚዎች ጸበኞች ወይም ባላጋራዎች አይደሉም፤ ይልቁንም የሚዋደዱ ጋደኛሞች ቤተሰቦችና ሌሎችም ይሆናሉ፡፡ ጦርነቱ ተሳታፊዎች እራሳቸው በካርቶን የተለያዩ አይነት መሳሪያዎችን አስመስለው ሰርተው ወደ ጦርነት አውድማው ያመራሉ፤ ጦርነቱ እንደተጀመረም መጎዳዳት በሌለው መልኩ ውጊያ ይጀመራል፤ ከካርቶን የተሰሩት የጦር መሳሪያዎችም እንዳይሆኑ ሆነው ድምጥማጣቸው ይጠፋል፡፡ ወዳጄ ይሄ ነው እንግዲህ የካርቶን ጦርነት፡፡
እናልዎት ወዳጄ የካርቶን ጦርነት፤ በግርድፉ ወደኛ ሀገር ስንመልሰው ዘመናዊ ‘ሸራብ-ሸራብ’፤ እንዲያው ልጅነቴ ማርና ወተቴ አይነት ነገር ይመስላል፡፡ ተመልሶ የማይመጣውን ልጅነት ትልቅ ሆኖ መዘከር አይነት ነገር፡፡ ታዲያ ፈረንጆቹ ይሄን የልጅነት ጨዋታቸውን በዚህ መልኩ አሳድገውት ብዙዎች እንዲተገብሩትና እንዲዝናኑበት እያደረጉት ነው፡፡ ለመሆኑ ግን ወዳጄ በርካቶቻችን በልጅነት ሳለን የምናዘወትራቸውን ጨዋታዎች እናስታውሳቸዋለን? የዛሬ ህጻናትስ ጨዋታዎቹን ያውቋቸዋል ወይስ ከውጪው አለም በመጡ ጨዋታዎች ነው የተዋጡት? ይሄ ጥያቄዬ ነው በተለይም ለወላጆች፡፡ ከካርቶን ጦርነት ግን ባህልን አዘምኖ ማሳደግና ለአለም ማስተዋወቅን መማር እንደምንችል እገምታለሁ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍኤም 96.3 

Friday, September 25, 2015

አለቅጥ ውፍረት ከስፖርት ያልገደባት 108 ኪሎ የመትመዝን ወጣት፤ ቫለሪ ሳጉን

ወዳጄ መቼም የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የሰውነት ውፍረት አይጥና ድመት እንደነሆኑ፤ ስፖርት ባለበት ውፍረት ዝር ማለት እንደማይወድ አያጡትም፡፡ “ይሄ ነገር እንዲሁ ብሂል ነው፤ ውፍረትና ስፖርትን ሳይጣሉ አንድ ላይ ማስኬድ ግጥም አድርጎ ይቻላል” የምትለው አሜሪካዊት፤ ወፍራሟ ቫለሪ ሳጉን፤ ፈረንጆቹ ዮጋ ሲሉ የሚጠሩትንና ትውልዱ ከወደሩቅ ምስራቅ የሆነውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማዘውተር የተካነች ናት ይላል ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ያስነበበው ዘገባ፡፡
በብዙዎች ዘንድ ይሄ ዮጋ የተባለ፤ አካልንና መንፈስን ያጣመረ፤ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለሸንቃጦች ብቻ ነው የሚለውን የከዚህ ቀደም እሳቤ ፉርሽ ያደረገችው የሳንፍራንሲስኮዋ ድንቡሽቡሽ ቫለሪ ሳጉን ላለፉት ሶስት አመታት አይደለም አለቅጥ በወፈሩ ሰዎች ይቅርና በሸንቃጦች እራሱ የማይሞከሩ ከባባድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ያለምንም ችግር አቀላጥፋ ስትከውን በካሜራ አይን ውስጥ ገብታለች፡፡
‘ኢንስታግራም’ በተባለው የማህበራዊ ትስስር ድረገጽ ላይ 80 ሺ የሚጠጉ አድናቂዎችና ተከታዮችን ያፈራቸው፤ ለአይን ሞልታ የምትታየው፤ ቫልሪ በየጊዜው ዮጋ ስፖርትን እየሰራች የምትቀረጻቸውን ቪዲዮዎች ለአድናቂዎቿ ታጋራለች፡፡ “አድናቂዎቼና ተከታዮቼ ምናልባት ‘በአካል ቅርጽ ከማይመሳሰለን ሰው እንዴት ትምህርት እንወስዳለን’ የሚል እሳቤ እንዳያድርባቸው ማረጋገጥ ነው ፍላጎቴ” የምትለውና 108 ኪሎ የምትመዝነው ቫለሪ “ሁላችንም፤ ማለትም ወፍራምም ሆንን ቀጭን፤ ከአካላችን ጋር ቅሬታ ሊኖረን ይችላል… ግን ዋናው ነገር ወደ ራሳችን መመልከትና ያለንን ነገር መውደድ ነው!” ስትል ትመክራለች፡፡
የዛሬ አራት አመት ገደማ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለች ዮጋ ስፖርትን ማዘውተር የጀመረችው የ27 አመቷ ቫለሪ “ምንም እንኳ ስፖርቱን ብወደውም… የመጀመሪያው ቀን ከባድ እንደሚሆንብኝ ተረድቼው ነበር… አስተማሪዬ ግን ሁሌም ያበረታታኝ ነበር” ስትል ነው የተናገረችው፡፡ የኋላኋላ ስፖርቱን እየለመደችው ስትሄድ ግን ለወትሮው ያስጨንቃት የነበረው ውፍረቷን የመቀነስ ሀሳቧ እየተመናመነ እየተመናመነ ሄዶ በመጨረሻም ሊጠፋ ችሏል፡፡
“‘ወፍራሞች አንዳንድ ነገሮችን በአግባቡ መከወን አይችሉም! ቀጠንጠን ብሎ መገኘት ብቻ ነገሮችን እንደ ልብ መከወን ያስችላል!’ ብዬ በአእምሮዬ የጫንኩትን ሀሳብ ዮጋ ስፖርትን በደንብ ሳዳብር ከናካቴው እርግፍ አድርጌ ከጭንቅላቴ አውጥቼዋለው” የምትለው ቫለሪ፤ “ዮጋ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመጀመሬ በፊት ‘ወፍራም ነኝ! አልችልም!’” በሚል ፍራቻ ብቻ ብዙ እድሎች እንዳመለጧት ትናገራለች፡፡ ያኔ ጓደኞቿ ሲዘሉና ሲቦርቁ እሷ የዳር ተመልካች ሆና የኖረችው ቫለሪ፤ እድሜ ለዮጋ፤ ዛሬ ላይ ከልብ የምትወደውን የሰማይ ዝላይ ሳይቀር መከወን ችላለች፡፡
ሁሌም በስፖርቱ አዳዲስ ነገሮችን መሞከር የምትፈልገው ቫለሪ “ዮጋ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከማዘውተሬ በፊት እራሴን አላውቅም ነበር ማለት ይቻላል ምስጋና ለዮጋ ይሁንና ዛሬ ነገሮች ተቀይረዋል፤ ዮጋ የአእምሮና የቀና አስተሳሰብ ጉዳይ ነው” ስትልም ነው የምትናገረው፡፡ ልምዷን ለአለም ማጋራቷም ለበርካቶች መነቃቃትን እንደፈጠረና ወደፊት ደግሞ የስፖርቱ አሰልጣኝ በመሆን በርካቶች ልክ እንደሷ በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩ የማስተማር ፍላጎትም እንዳላት አክላለች፡፡
ወዳጄ እንግዲህ መቼም ከቫልሪ ብዙ ነገር መማር እንደሚቻል ምንም ጥርጥር የለው፡፡ እርግጥ ነው ውፍረት ለብዙ ተላላፊ ያልሆኑ የጤና ችግሮች የሚዳርግ ነውና አካላችንን የተስተካከለ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ወፍራምም ሆንን ቀጭን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ደግሞ ጤናማ ህይወትን መምራት ያስችለናልና ስፖርትን ብናዘወትር ተጠቃሚነታችን በብዙ መልኩ ነው፡፡ ሌላውና ትልቁ ከቫለሪ መማር የምንችለው ነገር እራሳችንን በተመለከተ ቀና አመለካከት ማዳበርን፤ ያለንን ነገር ከመጥላት ይልቅ በራስ መተማመንን አጎልብተን ባለን ነገር ላይ በመመርኮዝ የተሻለ ነገር መስራትና እራሳችን መለወጥ እንደምንችል ነው፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3