Monday, August 31, 2015

“የመንገድ ሀኪሙ” ህንዳዊ ጡረተኛ

በሙሉ ስማቸው አቶ ጋንጋድሃራ ቲላክ ካትናም ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ብዙዎች የሚያውቋቸው ግን “የመንገድ ሀኪም” በሚል ቅጥል ስማቸው ነው፡፡ በህንዷ ሀይደራባድ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት የ66 አመቱ ጎልማሳ አቶ ቲላክ ቀደም ባለቱት ጊዜያት በባቡር ኢንጂነርነት ነበር ህይወታቸውን ሲመሩ የኖሩት፡፡ እድሜያቸው መግፋቱን ተከትሎም ከስራቸው በጡረታ ይገለላሉ፡፡ አንድ አመት ያክል ካለስራ ሽርሽር እያሉ ቆይተው ታዲያ የአማካሪነት ስራ ሊጀምሩ በተሰናዱበት አንድ እለት ነበር “የመንገድ ሀኪምነት” ጥሪን ከህይወት ያስተናገዱት፡፡


“ወደ አዲሱ ስራዬ እያመራሁ ነበር መንገድ መሃል ተጠራቅሞ የነበረ አዳፋ ውሃ  በተማሪዎች ላይ አንቦራጭቄ ያለፍኩት፡፡ በተመሳሳይም መሰል ክስተቶች በተለያዩ ቦታዎች በተደጋጋሚ አጋጠሙኝ፡፡” ሲሉ ጉዳዩን የሚያስታውሱት ጋሽ ቲላክ “መንገዶች ቢስተካከሉ እኮ እንዲህ ያለ ነገር አይከሰትም” ሲሉም ለፖሊስ አባላት ደጋግመው ቢያመለክቱም መፍተሄ አላገኙም ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለም ነበር ሁሉን ነገር አስትቶ መንገዶችን በማከም ስራ ህይወትን እንዲመሩ ውሳኔ እንዲወስኑ ያደረጋቸውን ከፍተኛ የመኪና አደጋ የተመለከቱት፡፡
ከአራት ቀናት በፊት አደጋ ደርሶበት ባዩበት ቦታ ላይ አንድ መኪና ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ ላይ አደጋ አድርሶ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ተመለከቱ፡፡ “እነዚህ በመንገዶች ላይ ተቆፋፍረው የሚገኙ ጉድጓዶችን የሚደፍን ሰው ቢኖር እኮ የሰው ልጅ ህይወት እንዲህ በከንቱ አይቀጠፍም ነበር” ሲሉ አስበውም ከዚያን ጊዜ አንስቶ በአካባቢያቸው ብሎም በከተማዋ ያሉ የመንገድ ላይ ጉድጓችን በመድፈን ለመንገድ ህክምና የመስጠት ስራቸውን ሀ ብለው ጀመሩ፡፡ ተግባራቸውንም ሽራማዳን ሲሉ ሰየሙት ትርጓሜውም የጉልበት ድጋፍ፣ እገዛ ማድረግ የሚል ነው፡፡
“በመኪና አደጋ ህይወትን ያክል ነገር መነጠቀ ልብን የሚያሸብር ነገር ነው!” የሚሉት ጋሽ ቲላክ በመኪናቸው እየተዘዋወሩ በየመንገድ ጥጋጥግ ላይ ተደፍተው የሚገኙ የአስፓልት መስሪያ ቁሳቁሶችን እየሰበሰቡ መንገድ ላይ ጉድጓድ በገጠማቸው ቁጥር እየደፈኑ መኖር ጀመሩ፡፡ ለዚሁ መልካም ስራ ሲሉም ስራቸውን በፍቃዳቸው ለቅቀው በጡረታ የሚያገኟትን ገንዘብ የተበላሹ መንገዶችን ለማከም ማዋልን ተያይዘው አንድ አመት ዘለቁ፡፡ በእስካሁኑ ቆይታቸውም አንድ ሺ የሚደርሱ የመንገድ ጉድጓችን አክመው ደፍነዋል፡፡
የባለቤታቸው ነገር አልዋጥ ያላቸው፤ በጠራራ ጸሀይ አስፓልት ለአስፓልት መዞራቸው ጤናቸውን አደጋ ላይ ይጥለዋል ብለው የሰጉት የጋሽ ቲላክ ባለቤት ታዲያ ነገሩን በአሜሪካ ለሚኖር ልጃቸው አሳውቀው “እባክህ እስቲ እረፍ በለው!” ሲሉ ስሞታ ለልጃቸው ነግረዋል፡፡ ምንም እንኳ የእናቱን ጭንቀት ቢረዳም የአባቱን ተግባር ያደነቀው ልጃቸው ግን “ይህ ነገር ይቅርብህ!” ብሎ አባቱን ከማስቆም ይልቅ በሚችለው መጠን ከአባቱ ጎን ቆሞ ይህን መልካም ምግባር ወደፊት ለማራመድ ነበር የወሰነው፡፡

ዛሬ ላይ የጋሽ ቲላክን ‘ሽራማዳን’ የተገነዘቡ ሰዎች ጋሽ ቲላክ መንገድ ሲያክሙ ከጎናቸው ሆነው ያግዟቸው ጀምረዋል፡፡ አንዳንዶች እንዳውም የተበላሸ መንገድ ሲገጥማቸው ሀሎ ሲሉ ነገሩን የሚያሳውቁበት የስልክ መስመርም አሰናድተዋል፡፡

“የተበላሹ መንገዶችን እኛ እንጠግናቸዋለን” እያሉ የጋሽ ቲላክን ተግባር ሲያጣጥሉ የነበሩ የማዘጋጃ ቤት ሰዎችም የጋሽ ቲላክ “ወደ ኋላ አልልም” ባይነት አሸንፏቸው ዛሬ ላይ የመንገድ መጠገኛ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ከጎናቸው ሊቆሙ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ የቤት ወጪያቸውን ልጃቸው እየሸፈነላቸውም ከማዘጋጃ ቤትም ቁሳቁስ አቅርቦት እያገኙ  ስለሆነም ጋሽ ቲላክ በጡረታ ከሚያገኟት 25 ከመቶ የምትሆነዋን ኪሳቸው እንድትቀመጥ አድርገዋል፡፡ ከሰዎች የገንዘብ ድጋፍ ሳይሆን የጉልበት እገዛን ብቻ ሚፈልጉት የመንገድ ሀኪሙ ‘የማይቻል ነገር የለም!’ ብለው ያምናሉ፡፡ “የሰዎች አስተሳሰብ መቀየር አለበት አስተሳሰባችን ነው እየገደበን! ያለው ይሄ መቀየር አለበት” ብለዋል፡፡ “ይህን ለማድረግ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮችን እይታ ማግኘታቸው ትልቅ ጥቅም እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡”


ወዳጄ ከ66 አመቱ ጎልማሳ ጋሽ ቲላክ ‘ሽራማዳን’ ተግባር ብዙ ነገር መማር እንደምንችል ጥርጥር የለውም፡፡ የመኪና አደጋውም ሆነ የመንገዶች መቆፋፈር እዚህ እኛ ሀገርም በርክቶ የሚታይ ጉዳይ ነውና እኛም ‘የማይቻል ነገር የለም!’ የሚለውን እሳቤ ይዘን በመነሳት እያንዳንዳችን ለበጎ ምግባር እንሰለፍ መልእክቴ ነው፡፡ 
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

የአለም ትልቁ ብረት-ድስት(ጎላ) 50 ኩንታል ሽሮ በአንድ ጊዜ ማንተክተክ ይችላል



ወዳጄ ጎላ ያውቃሉ አይደል!? ይሄ እንደ ሰርግ ላሉ ድግሶች ምግብ የሚዘጋጅበት ትልቅ ብረትድስት፡፡ እንደውም ብዙውን ጊዜ እድሮች አካባቢ አይጠፋም፡፡ እናልዎት ይሄ ትልቅ ብረት-ድስት እንደው እስከ አፉ ጢም ብሎ ወጥ ቢሰራበት ለምን ያክል ሰው የሚበቃ ምግብ ማብሰል ያስችላል ብለው ያስባሉ? በእርግጥ ምላሹን ለማወቅ የሚከብድ ቢሆንም ብቻ እርስዎ እያሰላሰሉት እኔ ቻይናውያን ስለሰሩት የአለም ትልቁ ጎላ ልንገርዎት፡፡
 በቻይናዋ ሁናን ግዛት ዶንግጂያንግ ሀይቅ አካባቢ በአሳ አጥማጆች ፌስቲቫል ላይ ለመሳተፍ የተሰባሰቡት ቻይናውያን የአለም ትልቁ ነው ያሉትን ብረት-ድስት ሰርተዋል፡፡ በአሳ ቅርጽ የሰሩት ይህ ጎላ ታዲያ በእርግጥ የአለም ክብረ ወሰን መዝጋቢ ድርጅት ከአለም አንደኛ ስለመሆኑ አረጋግጦ የምስከር ወረቀት ያልሰጠው ቢሆንም ለአስርሺ ሰዎች የሚሆን የአሳ ሾርባን ማብስል ችሏል፡፡ በፌስቲቫሉ ላይ የታደሙ 10 ሺ ቱሪስቶችም በትልቁ ጎላ ከተሰራው የአሳ ሾርባ ላይ የየድርሻቸውን ወስደው ፉት ብለው አጣጥመዋል፡፡
ወደጎን 11 ሜትር ርዝመት፣ 2 ሜትር ስፋትና ግማሽ ሜትር ቁመት ያለው ይህ ትልቅ ብረት-ድስት ምን ያክል መጠን ያለው ምግብ ማብሰል ይችላል መሰለዎት፡፡ መቼም አምስት ሺ ሲባል ቅድሚያ በፊትዎት ድቅን የሚለው አትሌቶቻችን የሚሮጡት የሩጫ ውድድር አሊያም ደግሞ ብር ሊሆን ይችላል ነገር ግን ይህ ቻይናውያኑ የሰሩት ጎላ በሙሉ አቅሙ 5 ሺ ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ምግብ መስሪያ ልዩ ልዩ ነገሮችን ሲጥ አድርጎ መያዝ እንደሚችል ነው ጎላውን የሰሩት ቻይናውያን የተናገሩት፡፡ ወዳጄ ያስቡት እንግዲህ ነገሩን እንዲያው በሽሮ እናስላው ብንል ብረት-ድስቱ በአንድ ጊዜ 50 ኩንታል ሽሮ ጎርሶ ማንተክተክ ይችላል እንደማለት ነው፡፡

ወዳጆቻችን ቻይናውያን ከአለም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ነው ያሉትን ብረት ድስት ሰርተው በብረት ድስቱ ያበሰሉትን የአሳ ሾርባ አስር ሺ ሰዎችን መግበውበታል፡፡ እናም እንግዲህ ለጎላ ቅርበት ያላችሁ እድሮችና በብረታብረት ዙሪያ ብዙ ብዙ ነገሮችን እየሰራችሁ ያላችሁ ሙያተኞች ቻይናውያኑን የሚያስከነዳ ጎላ በመስራት የአለም ክብረ ወሰንን የመጨበጧን ነገር አስቡባት ብያለሁ፡፡

ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

‘ካፕቴን ቦሎቄ’፡፡ አውሮፕላን አብራሪ ግን አይደለም!

ወዳጄ ዌልሳዊ ዜግነት ያለውን ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ን ይተዋወቁት፡፡ ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ አውሮፕላን አብራሪ ፓይለት ሆኖ አይደለም ካፕቴን መባሉ፡፡ መጠሪያ ስሙም ቦሎቄ አይደለም ነገር ግን ለቦሎቄ ካለው ፍቅር የተነሳ “ይህን ስፍስፍ የምለለትን የጥራጥሬ ዘር መጠሪያ ስሜ አድርጌው ብጠራበትም ያንስበታል” ብሎ ነው ለራሱ ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ የሚል ስያሜ የሰጠው፡፡


ዌልሳዊው ባሪ ኪርክ ህይወቱን በሙሉ የቦሎቄ ነገር የማይሆንለት፤ ቦሎቄ የሚለው ስም ሲነሳ ቀድሞ አቤት የሚል፤ በጥቅሉ የቦለቄ ፍቅር ያነሆለለው ግለሰብ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ እናም ይህን ፍቅሩን ለመግለጽ ሲል ነው መጠሪያ ስሙን አስቀምጦ ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ የሚል ቅጥል ስም ለራሱ ያወጣው፡፡ ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ ለቦሎቄ ያለውን ፍቅር በዚህ ብቻም አይደለም የገለጸው እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1986ዓ.ም. በመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ቦሎቄ ሞልቶ እራሱን በመዘፍዘፍ 100 ሰአታትን ገንዳው ውስጥ እንዳለ አሳልፎ የአለምን ክብረ ወሰን መያዝ ችሎ ነበር፡፡

እናም ራሰ በራው ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ ባሳለፍነው አመት 60ኛ አመት የልደት ቀኑን ሲያከብር 60 የቦሎቄ ፍሬዎችን በንቅሳት መልክ መላጣው ላይ እንዲሰፍሩ አድርጓል፡፡ “ቦሎቄን አናቴ ላይ መነቀሴ ዘመናትን ላስቆጠረው የቦሎቄ ፍቅሬ መግለጫ አንድ እርምጃ ጭማሪ ነው” የሚለው ካፕቴን “በዚያ ላይ ደግሞ የትም ቦታ ስሄድ ንቅሳቴን እየተመለከቱ ሰዎች ቦሎቄ መውደዴን ብቻ ሳይሆን በቦሎቄ እንደተሞላሁም ማየት ይችላሉ” ማለቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ አስነብቧል፡፡

‘ካፕቴን ቦሎቄ’ እንዲህ ማድረጉ ግን እውቅናን ለማትረፍ ብቻ አይደለም፡፡ ከ30 አመት በፊት የራሱ የብቻው ፈጠራ በሆነው ድርጊት የአለምን ክብረ ወሰን ለመስበር ሲነሳ ጎን ለጎን ለበጎ አድራጎት የሚውል ገንዘብ የማሰባሰብ አላማንም ሰንቆ ነበር የተነሳው፡፡ በወቅቱ ስኬታማ መሆንኑ ተከትሎም ከዛን ጊዜ ጀምሮ ስራውን በፍቃዱ በመልቀቅ ለሰናይ ምግባር የሚውል ገንዘብ የማሰባስብ ስራ በመስራት ነው ህይወቱን ሲመራ የኖረው፡፡

እናም ስልሳኛ አመቱን ለማክበር በተሰናዳበት ወቅት ታዲያ አንድ ሀሳብ መጣለት አናቱ ላይ የሚነቀሳቸውን 60 የቦሎቄ ፍሬዎች ለአንዷ ቦሎቄ 2 ሺ ብር የሚጠጋ ዋጋ ቆርጦላት የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ሰፖንሰር እንዲያደርጉት በምትኩም የስማቸውን መጀመሪያ ፊደሎች በቦሎቄዎቹ ላይ እንደሚያሰፍር ጠቅሶ ገንዘብ ማሰባሰብ ይጀምራል፡፡ ማሰባሰብ የቻለውን 115 ሺ ብር ገደማ በወሊድ ወቅት በሚከሰት የአንጎል መጎዳት የሚፈጠር ጡንቻዎችን ማዘዝ ያለመቻል ህመም ሴሬብራል ፓልሲ ለተጠቃችው የ3 አመት ህጻን መታከሚያ ይውል ዘንድ ለግሷል፡፡
የህጻኗ አያቶች ጋሼ አለንና እትዬ ሮበርትስም ጥቂት ቦሎቄዎችን ስፖንሰር አድርገው ስማቸውን በ’ካፓቴን ቦሎቄ’ አናት ላይ ያሰፈሩ ሲሆን “ካፕቴን እኛ ጋር መጥቶ ይህን የእብደት የመሰለ ሀሳቡን ነገረንና እኛም ተስማማንበት” ያሉት እትዬ ሮበርትስ “አሁን ላይ ካፕቴን ቦሎቄን ልክ እንደ ቤተሰባችን ነው፤ የምንቆጥረው በጣም ገራሚ ሰው ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡


ወዳጄ ‘ካፕቴን ቦሎቄ’ እንግዲህ ለቦሎቄ ያለው ፍቅር እንዳለ ሆኖ ይህን ፍቅሩን ለበጎ ምግባርም እያዋለው ይገኛል፡፡ እንግዲህ ይህ የጤና መጓደል ነገር እዚህ እኛም ሀገር አለና በመሰል መልኩ ታክሞ ለመዳን አቅም ያነሳቸውን ወገኖች ለመርዳት መኪናውን ለሽያጭ ካቀረበው አርቲስት ሰለሞን ቦጋለም ከ‘ካፕቴን ቦሎቄም’ መልካምነትን ተምረን የተቸገሩን ለመርዳት አቅም በፈቀደ መጠን የቻልነውን እናደርግ ዘንድ መልእክቴን  አስተላልፋለሁ፡፡ 

ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

“ጫካ ለምኔ” ያለችው አንበሳዋ ኤልሳ ብርድ ልብስ ለብሳ አልጋ ላይ መተኛትን መርጣለች

“የእንስሳቶች ንጉስ፤ በሚያስገመግም ድምጹ አራዊትን የሚያሸብር፤ በፈርጣማ ክንዱ ደቁሶ ከአፈር የሚደባልቅ፤ በዱር በጫካ የሚኖር… ይህ እንስሳ ማነው?” ቢባሉ እርስዎ ወዳጄ ካለምንም ማቅማማት “እንዴ… አንበሳ ነዋ!” ብለው በፍጥነት እንደሚመልሱ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ “እርግጥ ነው መልስዎት ላይ ምንም ስህተት ባይኖርበት ለኔ ግን አልተመቸኝም” የምትልዎት ኤልሳ፤ የሞቀ የደመቀ ቤትና ምቹ አልጋ እያለ እንዴት ሲባል በዱር በገደሉ ይታደራል ብላ ብድር ልብስ እየለበሰች አልጋ ላይ መተኛትን መርጣለች፡፡


ኤልሳ አንበሳ ነች፡፡ “በየጫካው እያደኑ መኖር የሚያዋጣ አልመሰለኝም… ልክ እንደነ ውርዬ እቤት ውስጥ ከትሞ ጓዳና ሳሎን እየተመላለሱ መኖር ነው ብልህነት” ያለች የምትመስለው ኤልሳ መኖሪያዋን በደቡብ አፍሪካ ከአሳዳጊዋ ሚኪ ቫን ቶንደር ጋር በሚኪ ቤት ውስጥ አድርጋለች፡፡

አይደለም ቀርበው ሊዳብሷቸውና አብረው ሊተኙ ቀርቶ እዚህ ስድስት ኪሎ አንበሳ ግቢ ከፍርግርግ ብረት ጀርባ ሆነው ይጎበኙ ከነበሩት አንበሶች ጋር ቀረብ ብሎ ፎቶ መነሳት በብዙዎች ላይ ምን ያክል መሳቀቅና ፍራቻ ይፈጥር እንደነበር እራሳችን ገጥሞን አሊያም ፎቶ ለመነሳት የቆሙ ሰዎች በአንበሶቹ ድምጽ ደንግጠው ለመሮጥ ሲዳዳቸው አይተን ታዝበን ይሆናል፡፡ አንበሳን እንደ ቤት እንስሳ አላምዳ እየኖረች ያለችው ሚኪ ግን አንበሳ መፍራት ሲያልፍም አይነካካኝ ብላለች ይላል ሜትሮ ድረገጽ ያስነበበው ዘገባ፡፡

በህጻንነቷ ከእናቷ የተለያየቸውን ኤልሳ በማደጎነት ተቀብላ እንደ እናት ተንከባክባ ያሳደገቻት ሚኪ ለኤልሳ ልዩ ፍቅር አላት፡፡ ስለኤልሳ ተጠይቃም “አብረን ነው የምንተኛው፤ ብርድ ልብስ ለብሰን ተቃቅፈን ነው የምናድረው… ከአንበሳ ጋር መተኛት በጣም ገራሚ ነው” ስትል ነው ምላሽ የሰጠችው፡፡ ኤልሳን ልክ እንደ ልጇ አድርጋ የምትንከባከባት ሚኪ በአንድ ወቅት ኤልሳ ክፉኛ ታማባት ህይወቷን ለማዳን የቀዶ ጥገና ህክምና ማድረግ ነበረባትና ለህክምናዋ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ ሚኪ አንበሳ የሚያስመስላትን ልብስ ለብሳ በየቀኑ በመንገድ ዳር ቆማ ገንዘብ ታሰባስብ ነበር፡፡ ይህ ተግባሯም በአካባቢዋ ሰዎች ዘንድ ታዋቂነትን አትርፎላት ነበር፡፡

ወዳጄ የኤልሳና የሚኪን የእናትና ልጅ ፍቅር እንዴት አዩት ታዲያ፡፡ እርግጥ ነገሩን ማድነቅዎትና መገረምዎት እንዳለ ሆኖ፤ “አሄሄ… ምን ቢያለምዱት አንድ ቀን አንበሳ አንበሳነቱ ትዝ ሳይለው አይቀርምና ሚኪም የኤልሳን አንበሳነት መዘንጋት አይኖርባትም” ሳይሉ እንደማይቀሩ እገምታለሁ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

Sunday, August 30, 2015

አዋጪ የሆነ፤ መቶ ብር በማይሞላ ካፒታል የሚጀምሩት ስራ፡- የድንች ደብዳቤ

ወዳጄ መቼም በግልዎት ስራ የመጀመር ሀሳብ ይኖርዎታል፡፡ ጀምረውም ከሆነ በደንብ አዋጪ የሆነ ካገኙ ገልበጥ ለማለት ሳያማትሩ እንደማይቀሩ እርግጥ ነው፡፡ ይበሉ እንግዲህ በወር 200 ሺ ብር ገደማ የተጣራ ትርፍ የሚያስገኝ አዋጪ የሆነ የስራ ሃሳብ ልነግርዎት ነውና እስኪቢርቶና ወረቀት ቢጤ ያሰናዱ፡፡

ግን ከዚያ በፊት አሜሪካዊውን ስራ ፈጣሪ ላስተዋውቅዎት፡፡ አሌክስ ክሬክ መኖሪያውን በአሜሪካ ቴክሳስ ያደረገ ስራ ፈጣሪ ነው፡፡ እንደ አብዛኛው ሰው የራሱን ስራ ጀምሮ ተፍ ተፍ እያለ መኖር ህልሙ ነበር እናም ከለታት በአንዱ ቀን የሆነች የስራ ሀሳብ ብልጭ ስትልለት ቀድሞ ጉዳዩን ያማከራት ለፍቅረኛው ነበር፡፡ አሌክስ ሊሰራ ያሰበውን ነገር የሰማችው ፍቅረኛው ሀሳብ ከማዋጣት ይልቅ ሳቅ ነበር የቀደማት፡፡ ፍርፍር እስክትል ሳቀች፤ በፍቅረኛዋ አዲስ የስራ ፈጠራ ሀሳብ፡፡

የፍቅረኛውን ሳቅ ከቁብ ያልቆጠረው አሌክስ ከሀሳቡ ማፈግፈግ አልመረጠም፡፡ ይልቁንም ወደፊት ተራምዶ ህልሙን እውን ለማድረግ ነበር የወሰነው፡፡ እናም በስራው ስኬታማ መሆን ችሎ ዛሬ ላይ አሌክስ ሳቅ ከፍቅረኛው ላይ ተረክቦ በሳቅ ፍርፍር እያለ ወደ ባንክ የሚያመራው እሱ ሆኗል፡፡ የአሌክስ ሥራ ፈጠራ ቀላል፤ እርሰዎ ወዳጄ ‘ደግሞ ይሄም ስራ ነው!?’ ሊሉት የሚችሉ ግን ደግሞ እሱን ስኬታማ ያደረገውና በወር እስከ 200መቶ ሺ ብር እያሳፈሰው የሚገኝ ስራ ነው፡፡ እናልዎት ስራው ምን መሰልዎት የድንች ደብዳቤ ብለን ብንሰይመው የሚያስኬድ ሳይሆን አይቀርም፡፡

እንዴት መሰልዎት የ24 አመቱ ወጣት ስራ ፈጣሪ አሌክስ “ለሚፈልጉት ሰው የሚፈልጉትን አጠር ያለ መልእክት ማንነትዎት ሳይገለጽ በድንች ላይ ጽፌ እሰድልዎታለሁ; እንደ ድንቹ መጠንም አስከፍልዎታለሁ” የሚል የስራ ሀሳብ ይዞ ነበር የተነሳው፡፡ ይህን ሀሳቡንም ነበር ለፍቅረኛው እራት እየበሉ ያማከራት፤ ምንም እንኳ ከት ብላ ስቃ “አንተ?… ብለህ ብለህ ደግሞ ምኑን ሀሳብ አመጣህው ባክህ? እኔ እዲህ ያለ የቄለ ሀሳብ ከዚህ ቀደም በህልሜም በእውኔም ሰምቼ አላውቅም!.. እንደው አንተ ተሳክቶሎህ አንድ የድንች ደብዳቤ ከላክ ከምላሴ ድንች ይነቀል…!” ስትል ሀሳቡን ብታጣጥልበትም፡፡

የስራ ሀሳቡን በመረጃ መረብ ላይ ያንሸራሸረው አሌክስ ገና በሁለተኛው ቀን ነበር “መልእክት አለን በድንች ደብዳቤ ላክልን” ከሚሉ ሰዎች የ40 ሺ ብር ውል መዋዋል የቻለው፡፡ “ይህ እንደሚሆን አውቅ ነበር” ያለው አሌክስ እስካሁን ድረስ 2000 ያክል የደንበኞቹን የድንች መልእክቶችን መስደዱን ይናገራል፡፡ በዚህም በወር የተጣራ 200 ሺ ብር ማግኘት እንደቻለም ጭምር፡፡ “በመላው አሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ የድንች ደብዳቤዎችን ልከናል፡፡ ምናልባትም ባልተለመደ በልኩ!... እናም ደግሞ በበርካቶች ህይወት ላይ በበጎ መልኩ የሆነ ተጽእኖ ነገር አሳድረናል ለሽራፊ ሰከንድ እንኳ ቢሆንም ማለት ነው፡፡”  የሚለው አሌክስ ለወጣት ስራ ፈጣሪዎች መልእክት አለኝ እሱም… “ሰዎች በህይወታቸው ወደ ኋላ የሚጎትቷቸው ሁለት ነገሮች አሉ እነሱም ፍርሀትና ጥርጣሬ ናቸው፡፡ እወድቃለሁ! ጊዜዬን በከንቱ ነው የማባክነው የሚል ፍርሀትና ‘ይሳካልኝ ይሆን?’ የሚል ጥርጣሬ፡፡ እነዚህ መወገድ አለባቸው ብሏል፡፡”

100 ፊደላትን በሚይዙ መጠነኛ ድንቾች ላይ መልእክት እንዲሰፍርልዎት ከፈለጉ አሌክስ 160 ብር ገደማ ያስከፍልዎታል፡፡ “አይ መልእክቴ በዛ ያለ ነው… ትልቅ ድንች ቢሆንልኝ እመርጣለሁ” ካሉ ደግሞ 140 ፊደላትን ሰድሮ ለሚይዝ ትልቅ ድንች 200 ብር ገደማ ለአሌክስ መክፈል ይጠበቅብዎታል፡፡ እሱም የሰጡትን መልእክት በጥቁር መጻፊያ ፓርከር ድንች ላይ ጽፎ ስምዎት ሳይጠቀስ ለፈለጉት ሰው ያደርስልዎታል፡፡ እስካሁን ከተላኩ መልእክቶች መካከልም… “መልካም የአባቶች ቀን” ሲል ልጅ ለአባቱ እንዲሁም የስራ እድገት ላገኘች እህቱ… “ኬሊ ለትልቁ ድንች እንኳን ደስ ያለሽ በጣም ተደንቸናል” የሚሉ አዝናኝም ቁምነገር አዘልም መልእክቶች ይገኙበታል፡፡

እናም ወዳጄ… ምንም እንኳ ዛሬ ዛሬ መልእክትን በደብዳቤ የመላላክ ልምዳችን እምብዛም እየሆነ ቢመጣም ምናልባት እርስዎ የደብዳቤ ተጠቃሚ ከሆኑና የሆነች ጽሁፍ ያረፈችባት ድንች በፖስታ ሳጥንዎት ውስጥ ገብታ ቢያገኙ አንድ ወዳጅዎት በአሌክስ በኩል “ድንች በፖስታ ልኬልሃለሁ መልሱን በድንች እጠብቃለሁ…” ብሎ እያንጎራጎረ መልእክቱን እንደሰደደልዎት ልብ ይበሉ፡፡ ቅድም ያሰናዷት እስኪቢርቶና ወረቀት ላይም ‘አዲስ የስራ ሀሳብ… የድንች ደብዳቤ… መነሻ ካፒታል 20 ብር… መድረሻ ካፒታል በወር መጨረሻ 200 ሺ ብር!!!’ ብለው ይጻፉና አሁኑኑ ስራ ይጀምሩ፡፡


ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

እንደ ሰው መኖር አንገሸገሸኝ ያለው ግለሰብ ህይወትን እንደ ፍየል እየኖርኩ ልሞክራት ብሎ ለሶስት ቀናት ፍየል ሆነ

ወዳጄ “እንደው ይቺ የኛ የሰው ልጆች ህይወት በእንስሳትኛ ብትቃኝ ምን ትመስላለች?” የሚል ሀሳብ ሽው ብሎብዎት ያውቅ ይሆን፡፡ ማለት ሰው መሆንዎት ቀርቶ በግ፣ ፍየል፣ ዶሮ አሊያም ላም ወይ ደግሞ ነብር፤ አንበሳም ብቻ ሌላ “የዱርም ይሁን የቤት እንስሳ ሆኜ ብኖር ህይወት ምን ትመስል ይሆን?” ብለው አስበው ያውቃሉ፡፡

“ኧረ ምኑን አመጣኸው ደግሞ!.. ምን ያለው የሞኝ ሀሳብ ነው ደግሞ ሰው መሆኔ ቀርቶ በሬ ሆኜ ልኑር የሚያስብል ሀሳብ” ብለው አግራሞት አዘል ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ ቶማስ ትዌትስ ሊቀየምዎት ይችላልና ይተውት፡፡ “ደግሞ ቶማስ ትዌትስ ማነው?” የሚል ጥያቄ ካነሱ… “እንዴዴ… ቶማስን እስካሁን አላወቅኩትም እንዳይሉና እሱ ካስደመመኝ በላይ እንዳያስገርሙኝ የሚልዎት ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ቶማስ ፍየሉን አሁኑኑ ይወቁት በኋላ ደግሞ ምናልባት በአጋጣሚ አግኝተውት ለአመት በአል እንዳያስቡት ይልዎታል፡፡”

ቶማስ ትዌትስ እንግሊዛዊ ተመራማሪ ነው፡፡ የሚመራመረው ደግሞ ‘የሰው ልጆች የልባቸውን ፍላጎት እንዴት በቀላል ማሳካት ይችላሉ?’.. ‘ምን አይነት የቴክኖሎጂ ውጤቶችንስ ተጠቅመው የልባቸውን ማድረስ ይችላሉ?’ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ እናልዎት ወዳጄ ቶማስ ፍየል ሆኖ፤ በሰውኛ ማውራትን ትቶ በ ኧ ኧ ኧ እያለ መኖር ምን እንደሚመስል የማወቅ ልዩ ፍላጎት ነበረው፡፡ ይህን ህልሙን እውን ለማድረግ ሲልም የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን በመጠቀም እንደ ፍየል በአራት እግሩ እየሄደ፤ ሳር የሚፈጭለትን ሰው ሰራሽ ጨጓራ እላዩ ላይ በመግጠምም እንደፍየል ሳር እየጋጠ በስዊዘርላንድ ተራራዎች ላይ ከፍየል መንጋ ጋር አብሮ ለሶስት ቀናት ያክል ፍየል ሆኖ በመኖር የልቡን ፍላጎት አሳክቷል፡፡

“ትናንትን እያስታወሰ ከሚጸጸት፤ ነገን እያሰበ ከሚጨነቅ ሰው ከተሰኘ ፍጡርነት ተገላግዬ፤ የቤት ወይ የዱር እንስሳ ሆኜ አመት በአልን ማሳለፍ ነበር አላማዬ…” ያለው ቶማስ የተረጋጋና ቀላል ነው ብሎ የሚያምነውንና ተቀጽላ የሆነ ስጋት የሌለበት ነው የሚለውን  የእንስሳነት ህይወት ለምን መኖር እንደፈለገ ተናግሯል፡፡ ምንም እንኳ ቶማስ ይህን ያስብ እንጂ ታዲያ የፍየልነት ህይወትን እንዳሰበው ቀላልና በግድ የለሽነት የሚኖሩት ሆኖ አላገኘውም፡፡ ምክንያቱም የፍየሎቹን መንጋ ሊቀላቀል በሞከረበት ሰአት እንኳ ቶሎ ተቀባይነትን ከፍየሎቹ ዘንድ አላገኘም፡፡ ፍየል ነው ብለው አምነው ከተቀበሉት በኋላም እንኳ ከፍየሎቹ እኩል እየወጣ እየወረደ አብሯቸው መጓዝ አልተሳካለትም ነበር፡፡

“የሆነ ሰአት ላይ እኔ ብቻዬን የተራራው አናት ላይ ቆሜ ዞር ስል ለካስ ሌሎቹ ፍየሎች እታች ቅጠላጠል እየቀጣጠፉ ሲመገቡ ቀርተው እኔን ይመለከቱኛል፤ መጀመሪያ ላይ ምንም አልፈራሁም ነበር በኋላ ላይ ነው ሹልና ቀጥ ቀጥ ያሉ ቀንዶች እንዳሏቸው ያስተዋልኩት ሲል…” በፍየልነቱ ወቅት የገጠመውን የሚናገረው ቶማስ “እርግጥ ነገሩን በሰውኛ አስቤው ሊሆን ቢችልም… አንድ ብዙውን ጊዜ አብሬው አሳልፍ የነበረ ፍየል ጓደኛዬ ነገሩን አረጋግቶታል መሰለኝ” ብሏል፡፡ ቶማስ አሁን ላይ የፍየልነት ህይወቱን የሚያስቃኝ የፎቶግራፍ አውደርዕይ ሊያዘጋጅ እየተሰናዳ ሲሆን ይህንኑ ህይወቱን የሚያስቃኝ መጽሀፍም እያዘጋጀ ነው፤ ‘ፍየሉ ሰው’ በሚል ርእስ፡፡

ወዳጄ የቶማስ ነገር “ወይ ጉ…ድ” ሳይስብልዎት እንደማይቀር አልጠራጠርም፡፡ ግን እንደው ግርምትዎት እንዳለ ሆኖ እርስዎም የቶማስ ነገር ሽው ቢልብዎት የትኛውን እንስሳ ሆነው ነው ህይወትን በእንስሳኛ ሊያጣጥሟት የሚፈልጉት? የሆነው ሆኖ የፈለጉትን እንስሳ መስለው ለመኖር ቢሞክሩ ለመምሰል መሞከርዎት በራሱ እንስሳኛ ሳይሆን ሰውኛ እንደሆነ ግን ልብ ይሏል፡፡ 

ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

“ይሳሙኝ ስኒ” ለገበያ ሊቀርብ ነው

“ያልታደለ ከንፈር ሳይሳም አረጀ” ይላል የኛ ሰው ሲተርት፡፡ “ኧረ ምን በወጣው ሳይሳም ያረጃል” ያሉ የሚመስሉት ኮሪያውያን “እንደ ልብዎት የሚስሙት ባለከንፈር የቡና ስኒ እያለልዎት… ምን ቁርጥ አድርጎት ነው ከንፈር ሳይሳም የሚያረጀው ብለዋል፡፡”
መቼም ቡና ለኛ ለኢትዮጵያውያን ያለው ትርጉም ለየት ያለ እንደሆነና ሌላው ቀርቶ የትውልድ ቦታው እራሱ እዚሁ እኛው ጋር ስለመሆኑ እርስዎ ወዳጄ ጠንቅቀው የሚያውቁት ጉዳይ እንደሆነ አልጠራጠርም፡፡ የቡና አፈላል ባህላችን እራሱ ልዩ ከሚያደርጉን መለያዎቻችን መካከል አንዱ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡

እናልዎት ወዳጄ ጠዋት… “ከእንቅልፍዎት እንደተነሱ ከሁሉ ነገር ቀድሞ ውልብ የሚልብዎት ቡና ከሆነና የ‘ሳይሳም አረጀ’ ተረት ነገር ሆድ ሆድዎትን እየበላዎት አስቸግሮዎት እንደሁ ጥሩ መላ ዘይጄልዎታለሁ” የሚለው ከሪያዊ ጠበብት “አዲሱ ፈጠራዬ ባለከንፈር የቡና መጠጫ ነው፤ ቡናዎትን ብቻ ሳይሆን ከንፈርም እንዲያጣጥሙ የሚያሰችልዎት ስኒ እነሆ ልልዎት ነው ብሏል፡፡”






ኮሪያዊው ጃንግ ውሲዎክ የሰራው አዲሱ የቡና መጠጫ ስኒ በሰው ከንፈር ቅርጽ የተሰሩ ከናፍርቶች ያሉት ሲሆን ስሙንም በግርድፉ ወደ አማርኛችን ስንመልሰው ‘ይሳሙኝ ስኒ’ ብሎ ሰይሞታል፡፡ በእርግጥ ስኒው አሁን ላይ ለገበያ የቀረበ ባይንሆንም ወደ ገበያው እንደተቀላቀለ ግን ትላልቅ ቡና መሸጫ ድርጅቶች እንደሚረባረቡበት ከወዲሁ ተገምቷል እንደ ዴይሊሜል ድረገጽ ዘገባ፡፡

አዲሱ ፈጠራውን አስመልክቶ ጃንግ ሲናገርም… “እንዲሁ ዝም ብሎ እንደ ሌሎች የቡና መጠጫዎች አይደለም… ይሳሙኝ ስኒ ልክ በሰው ፊት ቅርጽ የተሰራ ነው ከቡና መጠጫነቱ በተጨማሪ የሚያዝናናም ነው… ቡናውን የሚጠጣው ግለሰብ አይኑ በሚመለከተው ነገር ዘና እያለ መንፈሱን በማደስ ከወትሮ ለየት ያለ ቡናን ማጣጣም ይችላል” ሲል ነው ስለ ‘ይሳሙኝ ስኒ’ ፈጠራው ያስረዳው፡፡ “እርግጥ ነው ሁሌ ቡና መጠጣት ይቻል ይሆናል መሳምም ሆነ መሳም ግን እንደ ልብ ስለማይገኝ ‘ይሳሙኝ ስኒ’ ለዚህ ትልቅ መላ አለው ወይም አላት ሲልም ቀልድ ቢጤ አከል አድርጓል፡፡”

ወዳጄ ታዲያ የጃንግ የፈጠራ ውጤት ገበያውን ሲቀላቀል እሱ እንዳለው እንደ ልብ የማይገኘውን ከንፈር በየካፌውና በየጀበና ቡና መሸጫው ሁሉም በየፊናው እየኮመኮመው ‘ያልታደለ ከንፈር’ የሚለውን ተረት ከጨዋታ ውጪ ያደርገው ይሆን? ማን ያውቃል አንግዲህ ‘ይሳሙኝ ስኒ’ ለገበያ ሲቀርብ  አብረን የምንታዘበው ጉዳይ ይሆናል፡፡

ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3

Friday, August 28, 2015

“እድሜ ሌላ መዘነጥ ሌላ…” ጋሽ ገንተር ክራቤንሆፍት

“እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ
እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ…” (ሀይሌ ሩትስ)
 
ድምጻዊው እንዲህ ብሎ ማንጎራጎሩ አያ እርጅና ሲመጣ እንዲሁ ብቻውን ሳይሆን ብዙ ግሳንግሶቹን አስከትሎ፤ በልጅነትና በወጣትነት እንደልብ ሲከወኑ ከነበሩ ድርጊቶች ሊያቆራርጥ መሆኑን ተረድቶት… “እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ…” ማለቱም የአፍላነት አለም፣ የወጣትነት ጊዜ የብዙ ብዙ ነገሮች ማስተናገጃ በመሆኑ ምክንያት ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

እድሜ ገፍቶ ገፍቶ ወደ ማምሻው ሲጠጋ አስቀርቶ ከሚያልፋቸው ብዙ ነገሮች መካከል ዘመን አፈራሽ በሆኑ ልብሶች ተሸቀርቅሮ በየጎዳናው መንፈላሰስ አንዱ እንደሆነ… መቼም የያኔ ወጣቶች የዛሬ አዛውንቶች ምስክርነታቸውን… “እንዴታ!... መጣ የተባለ ፋሽን አይቀረንም ነበር እኮ… እምር ድምቅ ብለን ለመታየት ማን ብሎን!.. ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍራችን አጊጠን በየመንገዱ እንነጎማለል ነበር… የዛሬን አያድርገውና!! እያሉ በትዝታ ወደ ኋላ ተጉዘው የድሮውን እያስታወሱ እንደሚመሰክሩ በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል፡፡

“እድሜ የቁጥር ጉዳይ ነው… ዛሬም ቢሆን እሽቀረቀራለሁ… እርጅና ከነግሳንግሳህ ዘወር በል” ያሉ የሚመስሉት አዛውንቱ ጀርመናዊ አቶ ገንተር ክራቤንሆፍት ሽክ በልክ እያሉ የፋሽኑን አለም ቀልብ ስበውታል፡፡ “ፋሽንን ለወጣት ብቻ ያለው ማነው?.. እኛም እኮ አንድ ሰሞን ወጣት ነበርን… ትተን አልፈንው ነው እንጂ”… በሚል ወኔም ጋሽ ገንተር በተለያዩ አልባሳት አሸብርቀው እየተንጎማለሉ ነው የሚገኙት፡፡

የእድሜያቸው ጉዳይ በተለያዩ ድረገጾች ተለያይቶ 104ም 77 ነው እየተባለ በመገለጽ ላይ የሚገኘው ጋሽ ገንተር ቀለልና ጸዳ ያሉ ልብሶቻቸው ከከለር አመራረጣቸው ጋር ተዳምረው የፋሽኑን አለም ሰው “ኧረ በለውውው…” እያስባሉ የሚገኙ ሲሆን ጅንስ ሱሪ ጃኬትና ኮፍያ እንዲሁም ቦቲ በመባል የሚታወቁትን ከረባቶች አንገታቸው ላይ ሸብ አድርገው ቡትስ ጫማዎችን ነው የሚጫሙት፡፡ ጋሽ ገንተር የዘመኑ ልጆች በመሰል መለኩ ለማጌጥ ጥረው ያልተሳካላቸውን እሳቸው ተዋጥሎቸዋል፡፡

“አለባበሴ ምንም ልዩ ነገር የለውም… ሁሌም እንዲሁ ነው” የሚሉት ጋሼ “ወደ ስራ ስሄድ፣ ስፖርት ስሰራ ብቻ ማንኛውንም ነገር ሳደርግ እራሴን ደስተኛ ሆኜ  ማግኘት ነው የምፈልገው… ለዛም ነው ሁሌ እንዲህ ሽቅርቅር ብዬ የምለብሰው፤ ከውጭ ምትመለከቱት የውስጤ ነጸብራቅ ነው” ሲሉ አለባበሳቸው የውሳጣቸው ደስተኝነት አካል መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ እንዲህ አምረውና ደምቀው መታየታቸው ታዲያ ለአዛውቱ ጋሼ ገንተር ከፋሽኑ አለም ሰዎች ዘንድ የሞዴሊንግ ስራ አስገኝቶላቸዋል፡፡ ሌላ ደስታ ይሏል ደግሞ ይሄ ነው፡፡

ወዳጄ ምናልባት እርስዎም ወጣትነትን ሻገር ያሉ ከሆነና “እንዲህ ነበር እንጂ!.. እንደ ጋሽ ገንተር…” የሚል ምኞት ነገር ነሸጥ ካደረግዎት ምንም ሳያቅማሙ “ምነው በስተርጅና አንቱ… ወደ ፈጣሪ በመቅረቢያ እድሜዎት እንደገና እንደ አንድ ፍሬ ልጅ ፋሽን ፋሽን ይላሉ?” ለሚሉ አስተያቶች ጆሮዎትን ሳይሰጡ አምረውና ደምቀው እርጅናን ያጊጡበት ብያለሁ፡፡ ዋናውና ትልቁ ነገር ግን ጋሽ ገንተር እንዳሉት ውጫዊው ውበት የውስጣችን ነጸብራቅ ነውና በቻሉት መጠን እራስዎትን ደስተኛ ያድርጉት፡፡

ዳንኤል ቢሠጥ

ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍ ኤም 96.3