Friday, October 2, 2015

አባትና እንጀራ አባት የጋራ ልጃቸውን በአንድነት ሆነው ዳሩ


ወዳጄ እዚህ እኛ ሀገር፤ በባህል ወግ ልማዳችን መሰረት፤ ሶስት ጉልቻ መስርተው በአንድ ጣራ ስር ለመኖር የወሰኑ ፍቅረኛሞች እንደው ድል ያለ ሰርግ ደግሰውም ይሁን እንደ አቅሚቲ አነስ ያለች ድግስ አሰናድተው ሲሞሸሩ የትዳር ህይወታቸው የተባረከና የሰመረ እንዲሆን የወላጆቻቸውን ጉልበት ስመው ተመርቀው መውጣታቸው የተለመደ ነገር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ታዲያ በተለያየ ምክንያት ከወላጆቻቸው የተለያዩ ሙሽሮች ጉልበት ተስሞ ምርቃት በሚዥጎደጎድበት ሰአት እንባ ሲቀድማቸው ማየትም ብርቅ አይደለም፡፡
በፈረንጆቹ አለም የሰርግ ልማድ ጥንዶች በሰርጋቸው እለት ልክ እዚህ እኛ ጋር እንዳለው የሰርግ ስነ ስርአት ሙሽራው አናስገባም ሰርገኛ እየተዘፈነለት፤ እገባለሁ ብሎ ተጋፍቶ አይደለም ሙሽሪትን ከቤቷ ይዟት የሚሄደው፡፡ ይልቁንም ሙሽራው የሰርጉ ስነስርአት በተሰናዳበት ቦታ ቀድሞ ይቆምና የሙሽሪት አባት ልጁን በእድምተኛው መካከል ይዟት ይመጣና ነው ሙሽሪትን ለሙሽራው የሚያስረክበው፡፡ እናልዎት ወዳጄ ከሰሞኑ ድል ባለ ሰርግ የተዳረችው የ21 አመቷ አሜሪካዊት ብሪታኒ ፔክ በሰርጓ እለት ለየት ያለ ክስተት አስተናግዳለች፡፡ 
አሜሪካ ኦሃዮ ግዛት ውስጥ በሁለት አባቶች ያደገችው ሙሽሪት ብሪታኒ በሰርጓ እለት በእድምተኛው መሀል እጇን ይዞ ወደ ሙሽራው ዘንድ የሚያደርሳትን፤ የወላጅ አባቷን፤ እጅ ይዛ እየሄደች እንዳለ ነበር አስገራሚውና፤ ሙሽሮቹን ጨምሮ የሰርጉን ታዳሚዎችና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አውታሮች ወሬውን የሰሙትን ሁሉ እንባ ያስቀረረው ክስተት የተፈጠረው፡፡ 
የብሪታኒ ወላጅ አባት የ43 አመቱ ጎልማሳ አቶ ቶድ ባችማን ባልተጠበቀ መልኩ ጉዞውን ገታ አድርጎ ቀጥ ብሎ ሲቆም ሁሉም ግራ ተጋባ፤ ለሰው ግራ መጋባት ምላሽ ይሆን ዘንድም አቶ ቶድ ባችማን ከሰርጉ እድምተኛ መሀል የብሪታኒን እንጀራ አባት፤ የ45 አመት ጎልማሳውን አቶ ቶድ ሴንድሮስኪን ከተቀመጠበት ወንበር ላይ አስነስቶት “ብሪታኒ የሁለታችንም ልጅ ናትና ይህንን ክብር ልንጋራው የሚገባው አብረን ነው፤ ለሙሽራው አስረክበናት የምንመጣውም በጋራ ነው” ብሎ እጁን እየጎተተ ይዞት ወጥቶ ነው ሰርገኛውን እንዳለእና ሌሎች ብዙዎችን እንባ ያራጨ ድረጊት የፈጸመው፡፡
ይህንን ክስተት በያዘቸው ካሜራ ልቅም አድርጋ ፎቶ ያነሳችው ደሊያ ዲ ብላክበርን፤ “እነሆ የአባትነት ፍቅር” ስትል ነው ለአለም ያጋራችው፡፡ “እጅግ በጣም ስሜትን የሚነካ አጋጣሚ ነበር” ያለችው ደሊያ፤ “ሙሽሪትን ጨምሮ በርካታ የሰርጉ እድምተኛ እንባውን መቆጣጠር አልቻለም ነበር” ስትል ነው አጋጣሚውን ያስረዳችው፡፡
አቶ ቶድ ባችማን የፈጸመው ነገር ስሜቱን እንደነካው የተናገረው የሙሽሪት እንጀራ አባት አቶ ቶድ ሴንድሮስኪ፤ “ባችማን መጥቶ እጄን ይዞ ‘እኔ የለፋሁትን ያክል አንተም ለፍተሃል እናም ልጃችንን ለመዳር በእድምተኛው መሃል ይዘናት የምንሄደውም አብረን ነው’ ሲለኝ እግሬ ነው የከዳኝ… በህይወቴ ትልቅ ነገር የሚያሳድር ድርጊት ነበር ከምንም በላይ ትልቅ ነገር!!” ሲል ነው ነገሩን ወደ ኋላ መለስ ብሎ አስታውሶ የተናገረው፡፡
ስለሁኔታው የተጠየቀው የብሪታኒ ወላጅ አባት ቶድ ባችማን “በእርግጥ ከሴድሮስኪ ጋር ያን ያክል ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንደሌላቸው ባይደብቅም ልጃችንን ለማሳደግ ሴድሮስኪ ላደረገው የአመታት ልፋት ምስጋና ማቅረብ ብቻ ያንስበታል… እናም ልጃችንን ጎን ለጎን ሆነን አብረን ከመዳር የተሸለ ማመስገኛ ያለ አልመሰለኝም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ልጁ ብሪታኒ ከሰርጓ 2 ሳምንት ቀደም ብላ በሰርጓ እለት አባቷ ወይስ እንጀራ አባቷ እጇን ይዘው እንደሚሄዱ ግራ እንደገባት እያለቀሰች እንዳማከረችውና በዚህም ምክንያት ለልጁ ጭንቀት ምላሽ የሚሰጥ ድርጊት መፈጸሙን ነው ባችማን አክሎ የተናገረው፡፡
ወዳጄ መቼም በየትኛውም የአለም ክፍል ሊባል በሚችል ደረጃ፤ ምንም እንኳ ጉዳዩ ሁሉንም የሚገልጽ ባይሆንምና ምርጥ ምርጥ የሆኑ እንጀራ አባቶችና እናቶች መኖራቸው የማይታበል ሀቅ ቢሆንም ቅሉ፤ በበርካቶች ዘንድ እንጀራ አባቶችና እናቶች በመልካም ጎኑ ስማቸው ሲነሳ አይስተዋልም፡፡ ወላጆች በተለያዩ አጋጣሚዎች ከልጆቻቸው ተለያይተው ልጆቻቸውን ስላሳደጉላቸው እንጀራ አባቶችና እንጀራ እናቶች ብዙውን በጎ በጎውን ሳይሆን መጥፎ መጥፎውን ነው ሲያወሩ የሚደመጡት፡፡ ነገር ግን መጥፎ ያደረገ መወቀስ እንደሚገባው ሁሉ በጎ ስራ ለሰራ አሳዳጊ አባትና እናት ተገቢውን ክብርና ምስጋና መቸር እንደሚገባ ከሀለቱ የብሪታኒ አባቶች፤ ቶድ ባችማን እና ቶድ ሴንድሮስኪ፤ ትልቅ ትምህርት መውሰድ ይቻላል ባይ ነኝ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍኤም 96.3

No comments:

Post a Comment