Friday, October 2, 2015

አባትና እንጀራ አባት የጋራ ልጃቸውን በአንድነት ሆነው ዳሩ


ወዳጄ እዚህ እኛ ሀገር፤ በባህል ወግ ልማዳችን መሰረት፤ ሶስት ጉልቻ መስርተው በአንድ ጣራ ስር ለመኖር የወሰኑ ፍቅረኛሞች እንደው ድል ያለ ሰርግ ደግሰውም ይሁን እንደ አቅሚቲ አነስ ያለች ድግስ አሰናድተው ሲሞሸሩ የትዳር ህይወታቸው የተባረከና የሰመረ እንዲሆን የወላጆቻቸውን ጉልበት ስመው ተመርቀው መውጣታቸው የተለመደ ነገር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ታዲያ በተለያየ ምክንያት ከወላጆቻቸው የተለያዩ ሙሽሮች ጉልበት ተስሞ ምርቃት በሚዥጎደጎድበት ሰአት እንባ ሲቀድማቸው ማየትም ብርቅ አይደለም፡፡
በፈረንጆቹ አለም የሰርግ ልማድ ጥንዶች በሰርጋቸው እለት ልክ እዚህ እኛ ጋር እንዳለው የሰርግ ስነ ስርአት ሙሽራው አናስገባም ሰርገኛ እየተዘፈነለት፤ እገባለሁ ብሎ ተጋፍቶ አይደለም ሙሽሪትን ከቤቷ ይዟት የሚሄደው፡፡ ይልቁንም ሙሽራው የሰርጉ ስነስርአት በተሰናዳበት ቦታ ቀድሞ ይቆምና የሙሽሪት አባት ልጁን በእድምተኛው መካከል ይዟት ይመጣና ነው ሙሽሪትን ለሙሽራው የሚያስረክበው፡፡ እናልዎት ወዳጄ ከሰሞኑ ድል ባለ ሰርግ የተዳረችው የ21 አመቷ አሜሪካዊት ብሪታኒ ፔክ በሰርጓ እለት ለየት ያለ ክስተት አስተናግዳለች፡፡ 
አሜሪካ ኦሃዮ ግዛት ውስጥ በሁለት አባቶች ያደገችው ሙሽሪት ብሪታኒ በሰርጓ እለት በእድምተኛው መሀል እጇን ይዞ ወደ ሙሽራው ዘንድ የሚያደርሳትን፤ የወላጅ አባቷን፤ እጅ ይዛ እየሄደች እንዳለ ነበር አስገራሚውና፤ ሙሽሮቹን ጨምሮ የሰርጉን ታዳሚዎችና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አውታሮች ወሬውን የሰሙትን ሁሉ እንባ ያስቀረረው ክስተት የተፈጠረው፡፡ 
የብሪታኒ ወላጅ አባት የ43 አመቱ ጎልማሳ አቶ ቶድ ባችማን ባልተጠበቀ መልኩ ጉዞውን ገታ አድርጎ ቀጥ ብሎ ሲቆም ሁሉም ግራ ተጋባ፤ ለሰው ግራ መጋባት ምላሽ ይሆን ዘንድም አቶ ቶድ ባችማን ከሰርጉ እድምተኛ መሀል የብሪታኒን እንጀራ አባት፤ የ45 አመት ጎልማሳውን አቶ ቶድ ሴንድሮስኪን ከተቀመጠበት ወንበር ላይ አስነስቶት “ብሪታኒ የሁለታችንም ልጅ ናትና ይህንን ክብር ልንጋራው የሚገባው አብረን ነው፤ ለሙሽራው አስረክበናት የምንመጣውም በጋራ ነው” ብሎ እጁን እየጎተተ ይዞት ወጥቶ ነው ሰርገኛውን እንዳለእና ሌሎች ብዙዎችን እንባ ያራጨ ድረጊት የፈጸመው፡፡
ይህንን ክስተት በያዘቸው ካሜራ ልቅም አድርጋ ፎቶ ያነሳችው ደሊያ ዲ ብላክበርን፤ “እነሆ የአባትነት ፍቅር” ስትል ነው ለአለም ያጋራችው፡፡ “እጅግ በጣም ስሜትን የሚነካ አጋጣሚ ነበር” ያለችው ደሊያ፤ “ሙሽሪትን ጨምሮ በርካታ የሰርጉ እድምተኛ እንባውን መቆጣጠር አልቻለም ነበር” ስትል ነው አጋጣሚውን ያስረዳችው፡፡
አቶ ቶድ ባችማን የፈጸመው ነገር ስሜቱን እንደነካው የተናገረው የሙሽሪት እንጀራ አባት አቶ ቶድ ሴንድሮስኪ፤ “ባችማን መጥቶ እጄን ይዞ ‘እኔ የለፋሁትን ያክል አንተም ለፍተሃል እናም ልጃችንን ለመዳር በእድምተኛው መሃል ይዘናት የምንሄደውም አብረን ነው’ ሲለኝ እግሬ ነው የከዳኝ… በህይወቴ ትልቅ ነገር የሚያሳድር ድርጊት ነበር ከምንም በላይ ትልቅ ነገር!!” ሲል ነው ነገሩን ወደ ኋላ መለስ ብሎ አስታውሶ የተናገረው፡፡
ስለሁኔታው የተጠየቀው የብሪታኒ ወላጅ አባት ቶድ ባችማን “በእርግጥ ከሴድሮስኪ ጋር ያን ያክል ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንደሌላቸው ባይደብቅም ልጃችንን ለማሳደግ ሴድሮስኪ ላደረገው የአመታት ልፋት ምስጋና ማቅረብ ብቻ ያንስበታል… እናም ልጃችንን ጎን ለጎን ሆነን አብረን ከመዳር የተሸለ ማመስገኛ ያለ አልመሰለኝም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ልጁ ብሪታኒ ከሰርጓ 2 ሳምንት ቀደም ብላ በሰርጓ እለት አባቷ ወይስ እንጀራ አባቷ እጇን ይዘው እንደሚሄዱ ግራ እንደገባት እያለቀሰች እንዳማከረችውና በዚህም ምክንያት ለልጁ ጭንቀት ምላሽ የሚሰጥ ድርጊት መፈጸሙን ነው ባችማን አክሎ የተናገረው፡፡
ወዳጄ መቼም በየትኛውም የአለም ክፍል ሊባል በሚችል ደረጃ፤ ምንም እንኳ ጉዳዩ ሁሉንም የሚገልጽ ባይሆንምና ምርጥ ምርጥ የሆኑ እንጀራ አባቶችና እናቶች መኖራቸው የማይታበል ሀቅ ቢሆንም ቅሉ፤ በበርካቶች ዘንድ እንጀራ አባቶችና እናቶች በመልካም ጎኑ ስማቸው ሲነሳ አይስተዋልም፡፡ ወላጆች በተለያዩ አጋጣሚዎች ከልጆቻቸው ተለያይተው ልጆቻቸውን ስላሳደጉላቸው እንጀራ አባቶችና እንጀራ እናቶች ብዙውን በጎ በጎውን ሳይሆን መጥፎ መጥፎውን ነው ሲያወሩ የሚደመጡት፡፡ ነገር ግን መጥፎ ያደረገ መወቀስ እንደሚገባው ሁሉ በጎ ስራ ለሰራ አሳዳጊ አባትና እናት ተገቢውን ክብርና ምስጋና መቸር እንደሚገባ ከሀለቱ የብሪታኒ አባቶች፤ ቶድ ባችማን እና ቶድ ሴንድሮስኪ፤ ትልቅ ትምህርት መውሰድ ይቻላል ባይ ነኝ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍኤም 96.3

የአለማችን ጥፍራሙ ሰው ላለፉት 63 አመታት ጥፍሮቹን ምላጭ ነክቷቸው አያውቅም



ወዳጄ መቼም የጥፍር ነገር ቢወራ ያሳከከን ቦታ ምላሽ ለመስጠት ካለው ግብር አንስቶ እስከ ጌጥነት፤ አለፍ ሲልም በጥርስ እየነከሱት ለመቆዘሚያነትና እንዲሁም ደግሞ ለምሳሌያዊ አነጋገር ግብአትነት እንደ ‘እከክ የሰጠ ፈጣሪ ጥፍር አይነሳም’ አይነት ተረቶችን መፍጠሪያ ሆኖ ስለማገልገሉ ብዙ ብዙ ማውራት ይቻላል፡፡ እንደው ታዲያ ምናልባት በሆነ አጋጣሚ እርስዎ ወዳጄ ሀገረ ህንድ ላይ ተከስተው ወዲያ ወዲህ ሲሉ አንድ እድሜያቸው ገፋ ያሉ ሰው፤ ከወደ ጣቶቻቸው አካባቢ ተጠመዛዘው ቁልቁል የወረዱ ገመድ መሳይ ነገሮችን ይዘው ሲጓዙ ቢመለከቱና “ሰውዬው ቃጫ ገመድ ይዘው ይሆን ወይስ ጅራፍ ነገር ነው፤ ነው ወይስ ሰውዬው ድሮ ድሮ እዚህ እኛ ሀገር ከቆዳ የምትሰራዋንና ‘አሳመነች’ የምትባለዋን አለንጋ የሚነግዱ ሰው ናቸው” የሚሉ የተምታቱ ሀሳቦች በጭንቅላትዎ ቢመላለሱ አይፈረድብዎትም፡፡ ምክንያቱም እርግጥ ነው ጋሼ ሽሪድሃር ቺላል እጃቸው ሲታይ ገመዶችን አንጠልጥለው የያዙ ነው የሚመስሉት፡፡
ህንዳዊው ጋሼ ሽሪድሃር ቺላል ወደር የሌላቸው የአለማችን ጥፍራም ሰው ሆነው በአለም ክብረወሰን መዝጋቢ ድርጅት እውቅና የተሰጣቸው የ78 አመት አዛውንት ናቸው፡፡ ምንም እንኳ አለቅጥ የረዘሙ ጥፍሮችን በአንድ እጃቸው ላይ ብቻ የያዙ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ እናልዎት ወዳጄ ጋሼ ሽሪድሃር ላለፉት 63 አመታት ጥፍራቸው ከሽግሬ ጋር ተያይቶ አያውቅም፡፡ ያው እንግዲህ ድሮ ድሮ ጥፍርን በሽግሬ(ምላጭ) መቁረጥ የተለመደ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እናም ዘመነ ሽግሬ አልፎ ዛሬ ላይ እጅግ የዘመኑ ጥፍር መቁረጫዎች እየተመረቱ ቢሆንም ጋሼ ሽሪድሃር ግን “ጥፍርን የመቁረጥ ነገር ደህና ሰንብት” ካሉ እነሆ 63 አመታት ተቆጠሩ፡፡ ተማሪ ቤት ሳሉ ነበር ለመጨረሻ ጊዜ ጥፍራቸውን የቆረጡት፡፡ እናም ዛሬ ላይ በአንድ እጃቸው ላይ አለቅጥ የረዘሙ ጥፍሮች ያሏቸው ግለሰብ በሚል ዘርፍ ከአለም አንደኛ ሆነው ተመዝግበዋል፡፡ የአውራ ጣት ጥፍራቸው 2 ሜትር ያክል የሚረዝም ሲሆን የመሃል ጣታቸው ጥፍር ደግሞ ሁለት ሜትር ለመሙላት የሚጎድለው ጥቂት ሳንቲ ሜትሮች ብቻ ነው፡፡
እንዴት ጥፍራቸውን ማሳደግ እንደጀመሩ ተጠይቀው ሲናገሩም፤ “ያኔ ተማሪ ሳለን ነበር… የአንድ መምህራችንን ጥፍር ጓደኞቼ በአጋጣሚ ሰበሩበትና እንዳይሆኑ አድርጎ እስኪወጣለትና እኛም እስኪበቃን ድረስ ገረፈን” ሲሉ ነገሩን አስታውሰው፤ “ከዚያም ግን ‘ለምንድነው ጥፍርን ታክል ነገር ሰበራችሁ ብለህ ይህን ያክል ዱላ ያወረድክብን?’ ብለን መምህራችንን ስንጠይቀው… ‘ለምን እንደሆነ እናንተ ጥፍራችሁን አሳድጋችሁ ስላላያችሁት ልትረዱት አትችሉም፤ ጥፍርን አሳድገው ካልሞከሩት በስተቀር ጥፍር እንዳይሰበር ምን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ መረዳት አይቻልም’ ሲል አብራርቶ ምላሽ ሰጠን፡፡ እናም ከዛ በኋላ እኔም ‘ለምን?’ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጥፍሬን ማሳደግ ጀመርኩ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ጥፍርን ማሳደግ አንዲሁ ቀላል ነገር ሆኖ እንዳላገኙት የሚናገሩት ጋሼ ሽሪድሃር ጥፍርን ማሳደግንና የእለት ህይወትን መምራትን አብረው ማስኬድ እንደከበዳቸው፤ ቤተሰቦቻቸውም ቢሆኑ ይህን የጥፍር ማሳደግ ነገር ፈጽሞ እንዳልወደዱላቸው፤ ሌላው ቀርቶ ልብሶቻቸውን እንኳ ማንም ለማጠብ ፍቃደኛ እንዳልሆነላቸውና እራሳቸው ለማጠብ ተገደው እንደ ነበር ነው የሚያወሱት፡፡ ስራ የመቀጠር ነገርም ቢሆን በዚሁ በጥፍራቸው መዘዝ የማይታሰብ ነገር ሆኖባቸው እንደኖሩና የትኛውም መስሪያ ቤት እሳቸውን የመቅጠር ፍላጎት እንዳልነበረውም ነው የሚናገሩት፡፡

የፍቅር ህይወትም አስቸጋሪ እንደነበር የሚያስታውሱት ጋሼ ሽሪድሃር “እንደ ሰው አግብቼ ትዳር ልመስርት ብዬ ተነስቼ ነበር አንድም የሚያገባኝ አጣሁ እንጂ! አንድ 12 ገደማ ከሚሆኑ ሴቶች ጋር ግንኙነት መስርቼ ነበር… ግን ልጂት ልታገባኝ ብትፈቅድ እንኳን ወላጇቿ ‘እሱን ታገቢና ውርድ ከራስሸ… አንቆ ነው የሚገልሽ’” በሚል ማስፈራሪያ የትዳር ውጥናቸውን ሲያኮላሹት እንደኖሩም ይናገራሉ፡፡ 
እንደ እድል ሆኖ ጋሼ ጥፍራቸው አንድ እጃቸው ላይ ብቻ ነውና በጣም የሚወዱትን ፎቶ የማንሳት ስራ በአንድ እጃቸው እየከወኑ ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ እናም ዛሬ ላይ ጥፍሮቻቸው ከእድሜ መግፋት የተነሳ ሳስተው ሳስተው በቀላሉ የሚሰበሩበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው በቅርቡ አንገታቸውን የምላጭ ሲሳይ ለማድረግ እንደሚገደዱና ከስልሳ አመት በላይ አብረው ከኖሩት ከጋሼ ሽሪድሃር ጣት ሊለያዩ መሆኑን ነው ሜትሮ ድረገጽ ተደንቄበታለሁ በሚለው አምዱ ያሰፈረው፡፡
ወዳጄ በእርግጥ የጋሼ ሽሪድሃር ነገር ትንግርት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ጥፍር ውለታ የሚኖረውም፣ ውበት የሚሆነውም በመጠኑ ከፍ ሲል ነው እንጂ እንዲህ አለቅጥ መርዘሙ እጅን ያክል ነገር ከጥቅም ውጪ አድርጎ ምንም የማያሰራ ደንቃራ ከመሆን የዘለለ ጥቅሙ አይታየኝምና እንዲህ ባለው መልኩ ጥፍርዎትን ማሳደግ አይደለም፤ የማሳደግ ሀሳቡም እራሱ እንዳያድርብዎት ለማለት እወዳለሁ፡፡
ዳንኤል ቢሠጥ
ለአዲስ ቴሌቪዥን እና ለኤፍኤም 96.3